ሉቃስ 14:1-14
ሉቃስ 14:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ ሄዶ ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት በሰንበት ቀን እህል ሊበላ ገባ፤ እነርሱ ግን ይጠባበቁት ነበር። እነሆም፥ ሆዱ የተነፋ አንድ ሰው በፊቱ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ሕግ ዐዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን፥ “በሰንበት ድውይ መፈወስ ይገባልን? ወይስ አይገባም?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም ዝም አሉ፤ ይዞም ፈወሰውና ሰደደው። “ከእናንተ በሬው ወይም አህያው በጕድጓድ ውስጥ የወደቀበት አንድ ሰው ቢኖር ዕለቱን በሰንበት ቀን ያነሣው የለምን?” አላቸው። ስለዚህም ነገር ሊመልሱለት አልተቻላቸውም። በምሳ ላይ ለነበሩትም ወደ ላይኛው ወንበር ሲሽቀዳደሙ ባያቸው ጊዜ ምሳሌ መስሎ አስተማራቸው። እንዲህም አለ፥ “ለምሳ የጠራህ ሰው ቢኖርና ብትሄድ በላይኛው መቀመጫ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ የሚበልጥ ይመጣ ይሆናል። በኋላ ያ አንተንም እርሱንም የጠራ መጥቶ፦ ይህን ቦታ ለእርሱ ተውለት ይልሃልና፤ ያንጊዜም አፍረህ ትመለሳለህ፤ ወደ ዝቅተኛ ቦታም ትወርዳለህ። የጠራህ ሰው ቢኖርና ብትሄድ ግን የጠራህ በመጣ ጊዜ ወዳጄ ወደ ላይኛው መቀመጫ ውጣ ይልህ ዘንድ በታችኛው መቀመጫ ተቀመጥ፤ ያንጊዜም ከአንተ ጋር ለማዕድ በተቀመጡት ሰዎች ፊት ክብር ይሆንልሃል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም ያሚያዋርድ ከፍ ይላልና።” የጠራውንም እንዲህ አለው፥ “በበዓል ምሳ ወይም ራት በምታደርግበት ጊዜ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን፥ ዘመዶችህንና ጎረቤቶችህን፥ ባለጸጎች ባልንጀሮችህንም አትጥራ፤ እነርሱም ይጠሩሃልና፤ ብድርም ይሆንብሃልና። ነገር ግን በበዓል ምሳ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፥ ዕውሮችን፥ እጅና እግርም የሌላቸውን ጥራ። አንተም ብፁዕ ትሆናለህ፤ የሚከፍሉህ የላቸውምና፤ ነገር ግን ጻድቃን በሚነሡበት ጊዜ ዋጋህን ታገኛለህ።”
ሉቃስ 14:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንድ ሰንበት ቀን፣ ኢየሱስ ምግብ ሊበላ ከፈሪሳውያን አለቆች አንዱ ወደ ነበረ ሰው ቤት በገባ ጊዜ፣ ሰዎች በዐይን ይከታተሉት ነበር። በዚያም በአካል ዕብጠት የሚሠቃይ አንድ ሰው ከፊት ለፊቱ ነበር። ኢየሱስም ሕግ ዐዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን፣ “በሰንበት ቀን ሕመምተኞችን መፈወስ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም?” ሲል ጠየቃቸው፤ እነርሱ ግን ዝም አሉ። እርሱም ሰውየውን ይዞ ፈወሰውና አሰናበተው። ደግሞም፣ “ከእናንተ አንዱ፣ ልጁ ወይም በሬው በሰንበት ቀን ጕድጓድ ቢገባበት ፈጥኖ የማያወጣው ማን ነው?” አላቸው። እነርሱም ለዚህ አንዳች መልስ ሊያገኙ አልቻሉም። ኢየሱስ ተጋባዦቹ የክብር ስፍራ ሲመርጡ ተመልክቶ፣ እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ለእነርሱ ነገራቸው፤ “አንድ ሰው ሰርግ ቢጠራህ፣ በክብር ስፍራ አትቀመጥ፤ በክብር ከአንተ የሚበልጥ ሰው ተጠርቶ ከሆነ፣ ሁለታችሁንም የጋበዘው መጥቶ፣ ስፍራውን ‘ለዚህ ሰው ልቀቅለት’ ይልሃል፤ አንተም እያፈርህ ወደ ዝቅተኛው ስፍራ ትሄዳለህ። ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ ዝቅተኛውን ስፍራ አይተህ ተቀመጥ፤ ጋባዥህም ሲመጣ፣ ወዳጄ ሆይ፤ ወደ ላይ ከፍ በል ይልሃል፤ አንተም በዚያን ጊዜ አብረውህ በማእድ በተቀመጡ ሰዎች ሁሉ ፊት ትከበራለህ። ምክንያቱም ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ራሱንም ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ከፍ ይላል።” ኢየሱስም የጋበዘውን ሰው ደግሞ እንዲህ አለው፤ “የምሳ ወይም የእራት ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ፣ በዐጸፋው እንዳይጋብዙህና ብድራትን እንዳይመልሱልህ፣ ወዳጆችህን ወይም ወንድሞችህን ወይም ዘመዶችህን ወይም ከበርቴ ጎረቤቶችህን አትጋብዝ። ነገር ግን ግብዣ ባዘጋጀህ ጊዜ ድኾችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ሽባዎችንና ዐይነ ስውሮችን ጥራ፤ ትባረካለህም። እነዚህ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ፣ በጻድቃንም ትንሣኤ ብድራትህ ይመለስልሃል።”
ሉቃስ 14:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሰንበትም ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት እንጀራ ሊበላ በገባ ጊዜ እነርሱ ይጠባበቁት ነበር። እነሆም፥ ሆዱ የተነፋ ሰው በፊቱ ነበረ። ኢየሱስም መልሶ፦ በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? ብሎ ለሕግ አዋቂዎችና ለፈሪሳውያን ተናገረ። እነርሱ ግን ዝም አሉ። ይዞም ፈወሰውና አሰናበተው። ከእናንተ አህያው ወይስ በሬው በጕድጓድ ቢወድቅ በሰንበት ወዲያው የማያወጣው ማን ነው? አላቸው። ስለዚህ ነገርም ሊመልሱለት አልተቻላቸውም። የታደሙትንም የከበሬታ ስፍራ እንደ መረጡ ተመልክቶ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል፦ ማንም ለሰርግ ቢጠራህ በከበሬታ ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የከበረ ተጠርቶ ይሆናልና አንተን እርሱንም የጠራ መጥቶ፦ ለዚህ ስፍራ ተውለት ይልሃል፥ በዚያን ጊዜም እያፈርህ በዝቅተኛው ስፍራ ልትሆን ትጀምራለህ። ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ፥ የጠራህ መጥቶ፦ ወዳጄ ሆይ፥ ወደ ላይ ውጣ እንዲልህ፥ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ ያን ጊዜም ከአንተ ጋር በተቀመጡት ሁሉ ፊት ክብር ይሆንልሃል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል። የጠራውንም ደግሞ እንዲህ አለው፦ ምሳ ወይም እራት ባደረግህ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ምናልባት እንዳይጠሩህ ብድራትም እንዳይመልሱልህ፥ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ባለ ጠጎች ጎረቤቶችህንም አትጥራ። ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤ የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና።
ሉቃስ 14:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በሰንበት ቀን፥ ኢየሱስ ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት ምሳ ሊበላ ገባ፤ ፈሪሳውያን እርሱ የሚያደርገውን ለማየት ይጠባበቁት ነበር። በዚያን ጊዜ በሕመም ምክንያት መላ ሰውነቱ ያበጠበት አንድ ሰው በኢየሱስ ፊት ነበር። ኢየሱስም የሕግ መምህራንንና ፈሪሳውያንን “በሰንበት ቀን መፈወስ በሕግ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱ ግን ምንም ሳይመልሱ ዝም አሉ፤ ኢየሱስ የታመመውን ሰው ይዞ ፈወሰውና አሰናበተው። ቀጥሎም ኢየሱስ፦ “ከእናንተ በሰንበት ቀን ልጁ ወይም በሬው በጒድጓድ ውስጥ ቢወድቅበት ወዲያውኑ የማያወጣው ማን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱ ግን ምንም መልስ መስጠት አልቻሉም። ኢየሱስ ለግብዣ የተጠሩ ሰዎች የክብር ስፍራ ለመያዝ ሲሽቀዳደሙ አየ፤ ስለዚህ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ሰው ለሠርግ ግብዣ ሲጠራህ በክብር ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ የበለጠ ክብር ያለው ሰው ተጠርቶ ይሆናል፤ ታዲያ፥ ሁለታችሁንም የጋበዛችሁ ሰው ወደ አንተ መጥቶ፦ ‘ይህን ስፍራ ለዚህ ሰው ልቀቅለት’ ይልሃል፤ ያን ጊዜ በታላቅ ኀፍረት ወደ ዝቅተኛው ቦታ ወርደህ ትቀመጣለህ። ነገር ግን ለግብዣ ስትጠራ ሄደህ በዝቅተኛ ስፍራ ተቀመጥ፤ በዚያን ጊዜ የጠራህ ሰው ወደ አንተ መጥቶ፦ ‘ወዳጄ ሆይ! ወደ ከፍተኛው ስፍራ ወጥተህ ተቀመጥ’ ይልሃል፤ ያን ጊዜም በሌሎች ተጋባዦች ሁሉ ፊት ክብር ታገኛለህ። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ይዋረዳል፤ ራሱን የሚያዋርድ ግን ከፍ ይላል።” ኢየሱስ ጋባዡን ሰው ደግሞ እንዲህ አለው፦ “የምሳ ወይም የእራት ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ብድራቸውን ለመመለስ በተራቸው የሚጋብዙህን ወዳጆችህን፥ ወንድሞችህን፥ ዘመዶችህን፥ ሀብታሞች ጐረቤቶችህንም አትጥራ፤ ነገር ግን ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድኾችን፥ አካለ ስንኩሎችን፥ ሽባዎችን፥ ዕውሮችንም ሰዎች ጥራ። ይህን ብታደርግ እነርሱ ውለታ ለመክፈል ስለማይችሉ የተባረክህ ትሆናለህ። በጻድቃን ትንሣኤ ጊዜም እግዚአብሔር ይከፍልሃል።”
ሉቃስ 14:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በሰንበትም ቀን ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት ምግብ ሊበላ በገባ ጊዜ እነርሱ ይጠባበቁት ነበር። እነሆም፥ ሰውነቱ በሙሉ ያበጠበት ሰው በፊቱ ነበረ። ኢየሱስም መልሶ “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም?” ብሎ ሕግ አዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን ጠየቀ። እነርሱ ግን ዝም አሉ። ይዞም ፈወሰውና አሰናበተው። “ከእናንተ አህያው ወይስ በሬው በጉድጓድ ቢወድቅ በሰንበት ወዲያው የማያወጣው ማን ነው?” አላቸው። ስለዚህ ነገርም ሊመልሱለት አልተቻላቸውም። የታደሙትንም የከበሬታ ስፍራ እንደ መረጡ ተመልክቶ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል “ማንም ለሰርግ ቢጠራህ በከበሬታ ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የከበረ ተጠርቶ ይሆናልና፥ አንተንና እርሱን የጠራ መጥቶ ‘ለዚህ ሰው ስፍራ ተውለት’ ይልሃል፤ በዚያን ጊዜም እያፈርህ ዝቅተኛውን ስፍራ መያዝ ትጀምራለህ። ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ፥ የጠራህ መጥቶ ‘ወዳጄ ሆይ! ወደ ላይ ውጣ’ እንዲልህ፥ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ ያን ጊዜም ከአንተ ጋር በተቀመጡት ሁሉ ፊት ክብር ይሆንልሃል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል።” የጠራውንም ደግሞ እንዲህ አለው “ምሳ ወይም እራት ባሰናዳህ ጊዜ፥ ምናልባት እነርሱም በተራቸው እንዳይጠሩህ፥ እንዳይክሱህም፥ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ሀብታም ጎረቤቶችህንም አትጥራ። ነገር ግን ግብዣ ባሰናዳህ ጊዜ ድሆችንና ጉንድሾችን አንካሶችንም ዐይነ ስውሮችንም ጥራ፤ የሚመልሱት አጸፋ የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና።”