ሉቃስ 13:1-30
ሉቃስ 13:1-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያ ወራትም ሰዎች ወደ እርሱ መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለ ቀላቀለው ስለ ገሊላ ሰዎች ነገሩት። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ይህች መከራ ስለ አገኘቻቸው እነዚህ ገሊላውያን ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ተለይተው ኀጢኣተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን? አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ። ወይስ እነዚያ በሰሊሆም ግንብ ተጭኖ የገደላቸው ዐሥራ ስምንቱ ሰዎች ከኢየሩሳሌም ሰዎች ይልቅ ተለይተው ኀጢእታኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ።” እንዲህም ብሎ መሰለላቸው፥ “አንድ ሰው በታወቀች በወይኑ ቦታ ውስጥ በለስ ነበረችው፤ ፍሬዋን ሊወስድ ወደ እርስዋ ሄዶ አላገኘም። የወይኑን ጠባቂም፦ “የዚችን በለስ ፍሬ ልወስድ ስመላለስ እነሆ፥ ሦስት ዓመት ነው፤ አላገኘሁም፤ እንግዲህስ ምድራችንን እንዳታቦዝን ቍረጣት” አለው። እርሱም መልሶ እንዲህ አለው፥ “አቤቱ አፈር ቈፍሬ በሥሯ እስከ አስታቅፋት፥ ፍግም እስከ አፈስባት ድረስ የዘንድሮን እንኳ ተዋት። ምናልባት ለከርሞ ታፈራ እንደ ሆነ፥ ያለዚያ ግን እንቈርጣታለን።” በሰንበትም በአንድ ምኵራብ ውስጥ አስተማራቸው። ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ ጋኔን ያጐበጣት አንዲት ሴት ነበረች፤ ጐባጣም ነበረች፤ ከቶ ቀጥ ብላ መቆም አትችልም ነበር። ጌታችን ኢየሱስም አይቶ ራራላት፥ ጠርቶም፥ “ሴትዮ፥ ከደዌሽ ተፈትተሻል” አላት። እጁንም በላይዋ ጫነ፤ ያንጊዜም ፈጥና ቀጥ አለች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነችው። የምኵራቡ ሹምም ጌታ ኢየሱስ በሰንበት ፈውሶአልና፤ እየተቈጣ መልሶ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፥ “ሥራችሁን የምትሠሩባቸው ስድስት ቀኖች ያሉ አይደለምን? ያንጊዜ ኑና ተፈወሱ፤ በሰንበት ቀን ግን አይሆንም።” ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አላቸው፥ “እናንት ግብዞች፥ እናንተሳ አህያችሁን ወይም በሬአችሁን በሰንበት ቀን ገለባ ከሚበላበት አትፈቱትምን? ውኃ ልታጠጡትስ አትወስዱትምን? ይህቺ የአብርሃም ልጅ እነሆ፥ ሰይጣን ከአሰራት ዐሥራ ስምንት ዓመት ነው፤ እርስዋስ በሰንበት ቀን ከእስራቷ ልትፈታ አይገባምን?” ይህንም ባለ ጊዜ በእርሱ ላይ በጠላትነት የተነሡበት ሁሉ አፈሩ፤ ነገር ግን ሕዝቡ ሁሉ ከእርሱ ስለሚደረገው ድንቅ ነገር ሁሉ ደስ አላቸው። በዚያ ቀንም ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ “መንግሥተ ሰማያት ምን ትመስላለች? በምንስ እመስላታለሁ? ሰው ወስዶ በእርሻ ውስጥ የዘራት የሰናፍጭ ቅንጣትን ትመስላለች፤ አደገች፤ ታላቅ ዛፍም ሆነች፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ውስጥ ተጠለሉ።” ዳግመኛም እንዲህ አለ፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እመስላታለሁ? ሴት ወስዳ ሦስት መስፈሪያ ዱቄት የለወሰችበትን፥ ሁሉንም እንዲቦካ ያደረገውን እርሾ ትመስላለች”። በየከተማውና በየመንደሩ እየሄደ፥ በኢየሩሳሌምም እየተመላለሰ ያስተምር ነበር። አንድ ሰውም፥ “አቤቱ የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን?” አለው። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ጠባቡ በር ትገቡ ዘንድ በርቱ፤ እላችኋለሁ፥ ሊገቡ የሚሹ ብዙዎች ናቸው፤ ግን አይችሉም። ባለቤቱ ተነሥቶ ደጁን ይዘጋልና፤ ያንጊዜ ከደጅ ቆመው፦ ‘አቤቱ፥ አቤቱ፥ ክፈትልን’ እያሉ በር ሊመቱ ይጀምራሉ፤ መልሶም፦ ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም ይላቸዋል። ከዚህም በኋላ፦ በፊትህ በላን፥ ጠጣን፥ በአደባባያችንም አስተማርህ ልትሉ ትጀምራላችሁ። እርሱም እንዲህ ይላቸዋል፦ እናንተ ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም፤ ዐመፅን የምታደርጉ ሁላችሁ፥ ከእኔ ራቁ፤ አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን፥ ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት በአያችኋቸው ጊዜ እናንተን ወደ ውጭ ያወጡአችኋል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከደቡብ ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔርም መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ፤ ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ፤ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።”
ሉቃስ 13:1-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ መጥተው፣ ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለ ደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች ያወሩለት ሰዎች በዚያ ነበሩ። እርሱም እንዲህ መለሰላቸው፤ “ታዲያ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ሥቃይ የደረሰባቸው ከሌሎቹ የገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኀጢአተኞች ስለ ነበሩ ይመስላችኋል? አይደለም፣ እላችኋለሁ፤ ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ። ወይም ደግሞ በሰሊሆም ግንብ ተንዶባቸው የሞቱት ዐሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ በደለኞች ስለ ነበሩ ይመስላችኋል? አይደለም፣ እላችኋለሁ፤ ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።” ደግሞም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ተናገረ፤ “አንድ ሰው በወይኑ ዕርሻ ቦታ የተተከለች አንዲት የበለስ ተክል ነበረችው፤ እርሱም ፍሬ ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። የወይን አትክልት ሠራተኛውንም፣ ‘እነሆ፤ ፍሬ ለማግኘት ልፈልግባት ሦስት ዓመት ወደዚህች በለስ መጥቼ ምንም አላገኘሁም፤ ስለዚህ ቍረጣት፤ ለምን ዐፈሩን በከንቱ ታሟጥጣለች?’ አለው። “እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ‘ጌታ ሆይ፤ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፍግ እስከማደርግላት ድረስ ለዘንድሮ ብቻ ተዋት፤ ለከርሞ ካፈራች መልካም ነው፤ አለዚያ ትቈርጣታለህ።’ ” ኢየሱስ በሰንበት ቀን በአንድ ምኵራብ ያስተምር ነበር። በዚያም የድካም መንፈስ ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ አካለ ስንኩል ያደረጋት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም ከመጕበጧ የተነሣ ፈጽሞ ቀና ማለት አትችልም ነበር። ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና፣ “አንቺ ሴት፤ ከሕመምሽ ነጻ ወጥተሻል” አላት፤ እጁንም በላይዋ ጫነ፤ እርሷም ወዲያው ቀጥ ብላ ቆመች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነች። የምኵራቡ አለቃ ግን፣ ኢየሱስ በሰንበት ቀን ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ ሕዝቡን፣ “ሥራ ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ ስለዚህ በእነዚያ ቀኖች እየመጣችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት ቀን አይደለም” አላቸው። ጌታም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እናንት ግብዞች፤ ከእናንተ መካከል አንድ ሰው በሬውን ወይም አህያውን በሰንበት ቀን ከማደሪያው ፈትቶ ውሃ ሊያጠጣ ይወስደው የለምን? ታዲያ፣ ይህች ሴት የአብርሃም ልጅ ሆና ሳለች ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ በሰይጣን ታስራ ስትኖር፣ ከዚህ እስራት በሰንበት ቀን መፈታት አይገባትምን?” ይህን በተናገረ ጊዜ ተቃዋሚዎቹ ሁሉ ዐፈሩ፤ ሕዝቡ ሁሉ ግን እርሱ ባደረገው ድንቅ ሥራ ሁሉ ደስ አላቸው። ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ምን ትመስላለች? ከምንስ ጋር ላመሳስላት? አንድ ሰው ወስዶ በዕርሻው ውስጥ የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ አድጋ ዛፍ ሆነች፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎቿ ላይ ሰፈሩ።” ደግሞም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር ላመሳስላት? አንዲት ሴት ወስዳ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በዛ ካለ ዱቄት ጋር የደባለቀችውን እርሾ ትመስላለች።” ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እያመራ ሳለ፣ በሚያልፍባቸው ከተሞችና መንደሮች እያስተማረ ያልፍ ነበር። አንድ ሰውም ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚድኑት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸውን?” አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “በጠባቧ በር ለመግባት ተጣጣሩ፤ እላችኋለሁ፤ ብዙዎች ለመግባት ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አይሆንላቸውም። የቤቱ ባለቤት ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ በውጭ ቆማችሁ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ክፈትልን’ እያላችሁ በሩን ማንኳኳት ትጀምራላችሁ። “እርሱ ግን፣ ‘ማን እንደ ሆናችሁና ከየት እንደ መጣችሁ አላውቅም’ ብሎ ይመልስላችኋል። “እናንተም፣ ‘ከአንተ ጋር አብረን በልተናል፤ ጠጥተናል፤ በአደባባያችንም አስተምረሃል’ ትላላችሁ። “እርሱም፣ ‘እላችኋለሁ፤ ማን እንደ ሆናችሁና ከየት እንደ መጣችሁ አላውቅም፤ እናንት ዐመፀኞች ሁሉ ከእኔ ራቁ’ ይላል። “አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን፣ ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስታዩ፣ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ፣ በዚያን ጊዜ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ሰዎች ከምሥራቅ፣ ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ መጥተው በእግዚአብሔር መንግሥት በማእድ ይቀመጣሉ። እነሆ፤ ከኋለኞች መካከል ፊተኞች የሚሆኑ፣ ከፊተኞች መካከልም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።”
ሉቃስ 13:1-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያን ጊዜም ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች አወሩለት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን? እላችኋለሁ፥ አይደለም፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ። ወይስ በሰሌሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፥ እላችኋለሁ፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ። ይህንም ምሳሌ አለ፦ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፥ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። የወይን አትክልት ሠራተኛውንም፦ እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው። እርሱ ግን መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት። ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ አለው። በሰንበትም በአንድ ምኵራብ ያስተምር ነበር። እነሆም፥ ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ የድካም መንፈስ ያደረባት ሴት ነበረች፥ እርስዋም ጐባጣ ነበረች ቀንታም ልትቆም ከቶ አልተቻላትም። ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና፦ አንቺ ሴት፥ ከድካምሽ ተፈትተሻል አላት፥ እጁንም ጫነባት፤ ያን ጊዜም ቀጥ አለች፥ እግዚአብሔርንም አመሰገነች። የምኵራብ አለቃ ግን ኢየሱስን በሰንበት ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ መለሰና ሕዝቡን፦ ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ እንግዲህ በእነርሱ መጥታችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት አይደለም አለ። ጌታም መልሶ፦ እናንተ ግብዞች፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ ፈትቶ ውኃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን? ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። ይህንም ሲናገር ሳለ የተቃወሙት ሁሉ አፈሩ፤ ከእርሱም በተደረገው ድንቅ ሁሉ ሕዝቡ ሁሉ ደስ አላቸው። እርሱም፦ የእግዚአብሔር መንግሥት ምን ትመስላለች፥ በምንስ አስመስላታለሁ? ሰው ወስዶ በአትክልቱ የጣላትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ አደገችም ታላቅ ዛፍም ሆነች፥ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ሰፈሩ አለ። ደግሞም፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን አስመስላታለሁ? ሴት ወስዳ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች አለ። ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ከተማዎችንና መንደሮችን እያስተማረ ያልፍ ነበር። አንድ ሰውም፦ ጌታ ሆይ፥ የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን? አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፤ እላችኋለሁና፥ ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ አይችሉምም። ባለቤቱ ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ፥ እናንተ በውጭ ቆማችሁ፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን እያላችሁ በሩን ልታንኳኩ ትጀምራላችሁ እርሱም መልሶ፦ ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም ይላችኋል። በዚያን ጊዜም፦ በፊትህ በላን ጠጣንም በአደባባያችንም አስተማርህ ልትሉ ትጀምራላችሁ፤ እርሱም፦ እላችኋለሁ፥ ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላወቃችሁም፤ ሁላችሁ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ይላችኋል። አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ባያችሁ ጊዜ፥ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ፥ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ከምሥራቅና ከምዕራብም ከሰሜንና ከደቡብም ይመጣሉ፥ በእግዚአብሔርም መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ። እነሆም፥ ከኋለኞች ፊተኞች የሚሆኑ አሉ፥ ከፊተኞችም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።
ሉቃስ 13:1-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያን ጊዜ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መጥተው፥ “የገሊላ ሰዎች መሥዋዕት በሚያቀርቡበት ጊዜ ጲላጦስ ገደላቸው፤ ደማቸውም ከመሥዋዕታቸው ጋር አደባለቀ” ሲሉ ነገሩት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ታዲያ፥ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ጥፋት የደረሰባቸው ከሌሎቹ የገሊላ ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ኃጢአተኞች ስለ ነበሩ ይመስላችኋልን? ‘አይደለም፤ ንስሓ ባትገቡ እናንተም እንደእነርሱ ትጠፋላችሁ’ እላችኋለሁ። በሰሊሆም ግንብ ተደርምሶባቸው ስለሞቱት ዐሥራ ስምንት ሰዎች ምን ታስባላችሁ? እነርሱ በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ የባሱ ኃጢአተኞች የነበሩ ይመስሉአችኋልን? አይደለም! ንስሓ ባትገቡ እናንተም እንደእነርሱ ትጠፋላችሁ እላችኋለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “አንድ ሰው በወይን ተክሉ ቦታ ውስጥ የተተከለች አንዲት የበለስ ዛፍ ነበረችው፤ ከዚያች የበለስ ዛፍ ፍሬ አገኛለሁ ብሎ ቢሄድ ምንም ሳያገኝ ቀረ። ስለዚህ አትክልተኛውን ‘እነሆ፥ ከዚህች የበለስ ዛፍ ፍሬ ለማግኘት ሦስት ዓመት ሙሉ ተመላለስኩ፤ ግን ምንም ፍሬ አላገኘሁባትም፤ አሁንስ ቊረጣት! ስለምንስ መሬቱን ታበላሻለች?’ አለው። አትክልተኛው ግን እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ‘ጌታዬ ሆይ! እስቲ ለዚህ ዓመት ደግሞ ተዋት፤ ዙሪያዋን ኰትኲቼ ማዳበሪያ አደርግላታለሁ፤ ለመጪው ዓመት ፍሬ ብትሰጥ መልካም ነው፤ አለበለዚያ ግን ትቈረጣለች።’ ” ኢየሱስ በሰንበት ቀን ከምኲራቦቹ በአንዱ ያስተምር ነበር፤ ከዚያም ከዐሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ርኩስ መንፈስ ጀርባዋን ያጐበጣት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርስዋ ወገብዋ በመጒበጡ ቀና ለማለት በፍጹም አትችልም ነበር። ኢየሱስ ባያት ጊዜ ጠራትና “አንቺ ሴት ከበሽታሽ ተፈውሰሻል!” አላት። እጆቹን ጫነባት፤ ወዲያውም ቀጥ ብላ ቆመች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነች። ኢየሱስ በሰንበት ቀን ስለ ፈወሰ የምኲራቡ አለቃ ተቈጣና ለሕዝቡ፦ “በሳምንት ውስጥ ሥራ የሚሠራባቸው ስድስት ቀኖች አሉ፤ በእነዚህ ቀኖች እየመጣችሁ ተፈወሱ፤ በሰንበት ቀን ግን አይሆንም” ብሎ ተናገረ። ጌታ ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እናንተ ግብዞች፥ ከእናንተስ እያንዳንዱ በሰንበት ቀን በሬውን ከተዘጋበት አውጥቶ፥ ወይም አህያውን ከታሰረበት ፈቶ ውሃ ወደሚያጠጣበት ቦታ ይወስደው የለምን? እነሆ፥ የአብርሃም ዘር የሆነች ይህች ሴት ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ በሰይጣን ታስራ ስትሠቃይ ኖራለች፤ ታዲያ፥ እርስዋ ታስራ ከምትሠቃይበት በሽታ በሰንበት ቀን መፈታት አይገባትምን?” በዚህም ንግግሩ ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን ሁሉ አሳፈራቸው፤ ሕዝቡ ግን ኢየሱስ ባደረገው ድንቅ ነገር ሁሉ ተደሰተ። ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት በምን ትመሰላለች? ወይስ ከምን ጋር አነጻጽራታለሁ? አንድ ሰው በአትክልቱ ውስጥ የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች፤ እርስዋ አድጋ ዛፍ ሆነች፤ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ላይ ጎጆአቸውን ሠሩ።” ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር አነጻጽራታለሁ? የእግዚአብሔር መንግሥት፥ አንዲት ሴት ሊጡ በሙሉ እንዲቦካ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ የለወሰችውን እርሾ ትመስላለች።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ሳለ በየከተማውና በየገጠሩ እያስተማረ ያልፍ ነበር። በዚያን ጊዜ አንድ ሰው፥ “ጌታ ሆይ፥ የሚድኑ ጥቂቶች ሰዎች ናቸውን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በጠባብዋ በር ለመግባት ተጣጣሩ፤ በዚህች በር መግባት የሚፈልጉ ብዙዎች ናቸው፤ ነገር ግን መግባት አይችሉም እላችኋለሁ። የቤቱ ጌታ ተነሥቶ በሩን ይዘጋዋል፤ እናንተም በደጅ ቆማችሁ በሩን በማንኳኳት፥ ‘ጌታ ሆይ! እባክህ ክፈትልን!’ ማለት ትጀምራላችሁ፤ እርሱም ‘ከየት እንደ መጣችሁ አላውቅም!’ ሲል ይመልስላችኋል። በዚያን ጊዜ እናንተ፥ ‘ከአንተ ጋር አብረን በልተናል፤ አብረን ጠጥተናል፤ በአደባባያችንም አስተምረሃል’ ትሉታላችሁ። እርሱም እንደገና ‘ከየት እንደ መጣችሁ አላውቅም፤ እናንተ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ከእኔ ራቁ!’ ይላችኋል። አብርሃምን፥ ይስሐቅን፥ ያዕቆብን ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ታዩአቸዋላችሁ፤ እናንተ ግን በውጪ ተጥላችሁ ስትቀሩ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይደርስባችኋል። ብዙ ሰዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከደቡብ ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔር መንግሥትም በማእድ ይቀመጣሉ። ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ፤ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።”
ሉቃስ 13:1-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያን ጊዜም ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች አወሩለት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በእነዚህ የገሊላ ሰዎች ላይ ይህ የደረሰው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኀጢአተኞች ስለ ሆኑ ይመስላችኋልን?” “አይደለም”፤ እላችኋለሁ፥ “ነገር ግን ንስሓ ባትገቡ ሁላችሁም እንዲሁ ትጠፋላችሁ። ወይንስ በሰሊሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ ዐሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፥ እላችኋለሁ፤ ነገር ግን ንስሓ ባትገቡ ሁላችሁም እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።” ይህንንም ምሳሌ ነገራቸው፦ “አንድ ሰው በወይን አትክልቱ ቦታ የተተከለች በለስ ነበረችው፤ በእርሷም ፍሬ ፈልጎ ቢመጣ ምንም አላገኘም። የወይን አትክልት ሠራተኛውንም ‘እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ፈልጌ ለሦስት ዓመት ብመላለስ ምንም አላገኘሁም፤ ቁረጣት፤ ስለምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቁላለች?’ አለው። እርሱ ግን መልሶ፥ ጌታ ሆይ! ዙሪያዋን እስክኰተኩትላትና ፍግ እስካፈስላት ድረስ ይህችን ዓመት ደግሞ ተዋት። ወደፊትም ብታፈራ፥ መልካም ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ” አለው። በሰንበት ቀንም ከምኵራቦቹ በአንዱ ያስተምር ነበር። እነሆም፥ ከዐሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ርኩስ መንፈስ በሽተኛ ያደረጋት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም ጎባጣ ነበረች፤ ቀጥ ብላ መቆምም በፍጹም አልተቻላትም። ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና “አንቺ ሴት! ከበሽታሽ ተፈውሰሻል፤” አላት፤ እጁንም ጫነባት፤ ያን ጊዜም ቀጥ አለች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነች። የምኵራብ አለቃው ግን ኢየሱስ በሰንበት ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ ሕዝቡን “ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ እንግዲህ በእነርሱ መጥታችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት አይሆንም፤” አለ። ጌታም መልሶ እናንተ ግብዞች! ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ ፈትቶ ውሃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን? ይህች ለዐሥራ ስምንት ዓመት ሰይጣን ያሠራት የአብርሃም ልጅ በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። ይህንንም ሲናገር የተቃወሙት ሁሉ አፈሩ፤ በእርሱም በተደረጉት ድንቅ ነገሮች ሁሉ ሕዝቡ በሙሉ ደስ አለው። እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ምንን ትመስላለች? በምንስ እመስላታለሁ? ሰው ወስዶ በአትክልቱ የጣላትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤እርሷም አደገች፤ ታላቅ ዛፍም ሆነች፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ሰፈሩ፤”። ደግሞም እንዲህ አለ፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እመስላታለሁ? አንዲት ሴት ወስዳ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች፤” አለ። ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ ከተማዎችንና መንደሮችን እያስተማረ ያልፍ ነበር። አንድ ሰውም “ጌታ ሆይ! የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን?” አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፤ ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ፥ አይችሉምም እላችኋለሁ። ባለቤቱ ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ፥ እናንተ በውጭ ቆማችሁ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ክፈትልን’ እያላችሁ በሩን ማንኳኳት ትጀምራላችሁ፤ እርሱም መልሶ ‘ከየት እንደ ሆናችሁ አላውቅም’ ይላችኋል። በዚያን ጊዜም ‘በፊትህ በላን፤ ጠጣንም፤ በአደባባያችንም አስተማርህ፤’ ማለት ትጀምራላችሁ፤ እርሱም ‘እላችኋለሁ፥ ከየት እንደ ሆናችሁ አላወቅም፤ ዐመፀኞች በሙሉ፥ ከእኔ ራቁ፤’ ይላችኋል። አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን፥ ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት እያያችሁ፥ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ፥ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ከምሥራቅና ከምዕራብም ከሰሜንና ከደቡብም ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔርም መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ። እነሆም፥ ከኋለኞች ፊተኞች የሚሆኑ አሉ፤ ከፊተኞችም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።”