ሉቃስ 11:37-42
ሉቃስ 11:37-42 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህንም ሲነግራቸው አንድ ፈሪሳዊ በእርሱ ዘንድ ምሳ እንዲበላ ለመነው፤ ገብቶም ለምሳ ተቀመጠ። ፈሪሳዊዉም አይቶ አደነቀ፤ ምሳ ለመብላት እጁን አልታጠበም ነበርና። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው፥ “እናንተ ፈሪሳውያን፥ ዛሬ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭውን ታጥቡታላችሁ፤ ታጠሩታላችሁም፤ ውስጡ ግን ቅሚያንና ክፋትን የተመላ ነው። እናንተ ሰነፎች፥ የውጭውን የፈጠረ የውስጡንስ የፈጠረ አይደለምን? ነገር ግን የሚወደደውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፤ ሁሉም ንጹሕ ይሆንላችኋል። የእንስላልና የጤና አዳም፥ ከአትክልትም ሁሉ ዐስራት የምታገቡ ፍርድንና የእግዚአብሔርን ፍቅር ቸል የምትሉ እናንተ ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ወዮላችሁ! ይህንም ልታደርጉ ይገባችኋል፥ ያንም አትተዉ።
ሉቃስ 11:37-42 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ንግግሩን እንደ ጨረሰ፣ አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምግብ እንዲበላ ጋበዘው፤ እርሱም አብሮት ገብቶ በማእድ ተቀመጠ። ፈሪሳዊውም ኢየሱስ ከምግብ በፊት እጁን እንዳልታጠበ ባየ ጊዜ ተደነቀ። ጌታም እንዲህ አለው፤ “አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጫዊ ክፍል ታጸዳላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በሥሥትና በክፋት የተሞላ ነው። እናንት ሞኞች፤ የውጭውን የፈጠረ የውስጡንም አልፈጠረምን? ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉም ንጹሕ ይሆንላችኋል። “እናንት ፈሪሳውያን ግን ወዮላችሁ፤ ከአዝሙድና ከጤና አዳም እንዲሁም ከአትክልት ሁሉ ዐሥራት ታወጣላችሁ፤ ሆኖም ፍትሕንና እግዚአብሔርን መውደድ ቸል ትላላችሁ፤ ነገር ግን ያንን ሳትተዉ ይህኛውን ማድረግ በተገባችሁ ነበር።
ሉቃስ 11:37-42 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይህንንም ሲናገር አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምሳ ይበላ ዘንድ ለመነው ገብቶም ተቀመጠ። ከምሳም በፊት አስቀድሞ እንዳልታጠበ ባየው ጊዜ ፈሪሳዊው ተደነቀ። ጌታም እንዲህ አለው፦ አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፥ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል እናንት ደንቆሮዎች፥ የውጭውን የፈጠረ የውስጡን ደግሞ አለፈጠረምን? ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፥ እነሆም፥ ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል። ነገር ግን እናንተ ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከጤና አዳም ከአትክልትም ሁሉ አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና እግዚአብሔርን መውደድ ስለምትተላለፉ፥ ወዮላችሁ፤ ነገር ግን ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉት ይገባችሁ ነበር።
ሉቃስ 11:37-42 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ይህን በሚናገርበት ጊዜ አንድ ፈሪሳዊ ምሳ ጋበዘው፤ ወደ ፈሪሳዊው ቤት ገብቶ ምሳ ለመብላት ወደ ማእድ ቀረበ። ኢየሱስ ምሳ ከመብላቱ በፊት እጁን ስላልታጠበ ፈሪሳዊው ተደነቀ። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ “እናንተ ፈሪሳውያን የብርጭቆውንና የሳሕኑን ውጪውን አጥርታችሁ ታጥባላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶባችኋል። እናንተ ሞኞች! የውጪውን የፈጠረ አምላክ የውስጡንስ አልፈጠረምን? በብርጭቋችሁና በሳሕናችሁ ውስጥ ያለውን ለድኾች ስጡ፤ ከዚህ በኋላ ሁሉ ነገር ንጹሕ ይሆንላችኋል። “እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! በአንድ በኩል ከአዝሙድና ከጤናዳም፥ ከልዩ ልዩ ጥቃቅን አትክልቶችም ዐሥራት ታወጣላችሁ፤ በሌላ በኩል ግን ትክክለኛ ፍርድንና የእግዚአብሔርን ፍቅር ትተዋላችሁ፤ ያንን ስታደርጉ ይህንን መተው አልነበረባችሁም።
ሉቃስ 11:37-42 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህንንም በመናገር ላይ በነበረ ጊዜ አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምሳ እንዲበላ ለመነው፤ ኢየሱስም ወደ እርሱ ገብቶ ተቀመጠ። ከምሳም በፊት አስቀድሞ እንዳልታጠበ በማየቱ ፈሪሳዊው ተደነቀ። ጌታም እንዲህ አለው፦ “በእርግጥ እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል። እናንተ ሞኞች! የውጭውን የፈጠረ እርሱ የውስጡንስ ደግሞ አለፈጠረምን? ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፤ እነሆም፥ ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል። “ነገር ግን እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ከአዝሙድና ከጤና አዳም ከአትክልትም ሁሉ አሥራት ታወጣላችሁ፤ ፍርድንና የእግዚአብሔርን ፍቅር ግን ቸል ትላላችሁ፤ ይልቁንስ እነዚያን ደግሞ ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ ይገባችሁ ነበር።