ኢያሱ 6:20-24
ኢያሱ 6:20-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፤ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ከተማዪቱ ገቡ፤ ሁሉም ወደ ፊታቸው ወደ ከተማዪቱ ሮጡ፤ ከተማዪቱንም እጅ አደረጉ። ኢያሱም ከተማዋን፥ በከተማዪቱም ውስጥ የነበሩትን ሁሉ፥ ከወንድ እስከ ሴት፥ ከሕፃን እስከ ሽማግሌ፥ ከበሬ እስከ በግና እስከ አህያ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋ። ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉ ሁለቱን ሰዎች፥ “ወደ ዘማዪቱ ቤት ግቡ፤ ከዚያም ሴቲቱንና ያላትን ሁሉ እንደማላችሁላት አውጡ” አላቸው። እነዚያም ከተማዪቱን የሰለሉ ሁለቱ ጐልማሶች ወደ ዘማዪቱ ረዓብ ቤት ገብተው ረዓብን፥ አባቷንና እናቷን፥ ወንድሞችዋንም፥ ያላትንም ሁሉ፥ ቤተ ዘመዶችዋንም ሁሉ አወጡአቸው፤ ከእስራኤልም ሰፈር በውጭ አስቀመጡአቸው። ከተማዪቱንም፥ በእርስዋም የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፤ ነገር ግን ብሩንና ወርቁን፥ የናሱንና የብረቱንም ዕቃ በእግዚአብሔር ግምጃ ቤት ውስጥ አገቡ።
ኢያሱ 6:20-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
መለከቱ ሲነፋ ሕዝቡ ጮኸ፤ የመለከቱ ድምፅ ተሰምቶ፣ ሕዝቡ በኀይል ሲጮኽ ቅጥሩ ፈረሰ፤ እያንዳንዱም ሰው ሰተት ብሎ ገባ፤ ከተማዪቱም በእጃቸው ወደቀች። በከተማዪቱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፣ ማለትም ወንዱንና ሴቱን፣ ወጣቱንና ሽማግሌውን፣ ከብቱንና በጕን እንዲሁም አህያውን በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ። ኢያሱ ምድሪቱን የሰለሉትን ሁለቱን ሰዎች፣ “ወደ ጋለሞታዪቱ ቤት ሂዱ፤ በማላችሁላትም መሠረት እርሷንና የእርሷ የሆነውን ሁሉ ከዚያ አውጡ” አላቸው። ስለዚህ ሁለቱ ወጣት ሰላዮች ገብተው ረዓብን፣ አባቷንና እናቷን፣ ወንድሞቿንና የእርሷ የሆኑትን ሁሉ ከዚያ አወጧቸው። ቤተ ዘመዶቿንም ሁሉ አውጥተው ከእስራኤል ሰፈር ውጭ አስቀመጧቸው። ከዚያም ከተማዪቱን በሙሉ፣ በውስጧ ያለውንም ሁሉ አቃጠሉ፤ ብሩንና ወርቁን፣ የናሱንና የብረቱን ዕቃ ግን በእግዚአብሔር ግምጃ ቤት አኖሩ።
ኢያሱ 6:20-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፥ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ወደ ፊቱ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ወሰዱ። በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ። ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉ ሁለቱን ሰዎች፦ ወደ ጋለሞታይቱ ቤት ግቡ፥ ከዚያም ሴቲቱንና ያላትን ሁሉ እንደ ማላችሁላት አውጡ አላቸው። ሰላዮቹም ብላቴናዎች ገብተው ረዓብን፥ አባትዋንና እናትዋን፥ ወንድሞችዋንም፥ ያላትንም ሁሉ፥ ቤተ ዘመዶችዋንም ሁሉ አወጡ፥ ከእስራኤልም ሰፈር በውጭ አስቀመጡአቸው። ከተማይቱንም በእርስዋም የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፥ ነገር ግን ብሩንና ወርቁን የናሱንና የብረቱንም ዕቃ በእግዚአብሔር ግምጃ ቤት አደረጉት።
ኢያሱ 6:20-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ እምቢልታ ተነፋ፤ ሕዝቡም የእምቢልታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ ከፍተኛ የጩኸት ድምፅ አሰሙ የከተማይቱም ቅጽሮች ፈረሱ፤ ከዚህም በኋላ ሠራዊቱ ኮረብታውን ወጥቶ ሰተት ብሎ ወደ ከተማይቱ በመግባት በቊጥጥሩ ሥር አደረጋት፤ ሰይፋቸውንም መዘው በከተማይቱ የተገኘውን ወንዱንም ሴቱንም ወጣቱንና ሽማግሌውን ሁሉ ገደሉ፤ የከብት፥ የበግና የአህያውን መንጋ ሁሉ ፈጁ። ኢያሱ ሰላዮች ሆነው የተላኩትን ሁለት ሰዎች “ወደ ጋለሞታይቱ ረዓብ ቤት ሄዳችሁ በገባችሁላት የተስፋ ቃል መሠረት እርስዋንና ቤተሰብዋን አውጡ” አላቸው። እነርሱም ሄደው ረዓብን ከአባትዋና ከእናትዋ ከወንድሞችዋና ከሌሎችም የእርስዋ ወገን ከሆኑት ሰዎች ሁሉ ጋር አውጥተው ከእስራኤላውያን ሰፈር ውጪ አኖሩአቸው። ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ዕቃ ግምጃ ቤት ካስቀመጡአቸው ከብሩና ከወርቁ እንዲሁም በነሐስና በብረት ከተሠሩት ዕቃዎች በቀር ከተማይቱንና በእርስዋ ያሉትን ነገሮች ሁሉ አቃጠሉ።
ኢያሱ 6:20-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ በቀጥታ አቅንቶ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ያዝዋት። በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ። ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉ ሁለቱን ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “ወደ አመንዝራይቱ ቤት ግቡ፥ ከዚያም ሴቲቱንና ያላትን ሁሉ እንደ ማላችሁላት አውጡ።” ሰላዮቹም ብላቴናዎች ገብተው ረዓብን፥ አባትዋንና እናትዋን፥ ወንድሞችዋንም፥ ያላትንም ሁሉ፥ ቤተ ዘመዶችዋንም ሁሉ አወጡ፤ ከእስራኤልም ሰፈር በውጭ አስቀመጡአቸው። ከተማይቱንም በእርሷም የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፤ ነገር ግን ብሩንና ወርቁን የናሱንና የብረቱንም ዕቃ ብቻ በጌታ ግምጃ ቤት አኖሩት።