ኢያሱ 6:1-20
ኢያሱ 6:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢያሪኮም በግንብ ታጥራ ተዘግታ ነበር፤ ወደ እርስዋ የሚገባ፥ ከእርስዋም የሚወጣ አልነበረም። እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፥ “እነሆ፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን ጽኑዓን፥ ኀያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼአለሁ። አንተም ተዋጊዎችን ሁሉ በዙሪያው አሰልፋቸው። ተዋጊዎቻችሁም ሁሉ በከተማዪቱ ዙሪያ አንድ ጊዜ ይዙሩ፤ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ። ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይያዙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፤ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ። ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱን ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማዪቱም ቅጥር ይወድቃል፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ፊት ለፊት እየሮጠ ይገባባታል።” የነዌም ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ፥ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፤ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ወስደው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ” አላቸው። ሕዝቡንም፥ “ሂዱ፤ ከተማዪቱንም ዙሩ፤ ተዋጊዎችም ከጦር መሣሪያዎቻቸው ጋር በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ ብላችሁ እዘዙአቸው” አላቸው። በእግዚአብሔርም ፊት ይሄዱ ዘንድ ኢያሱ እንደ ነገራቸው ሰባቱ ካህናት የተቀደሱ ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው ሄዱ፤ በሄዱም ጊዜ አሰምተው በምልክት ነፉ፤ የእግዚአብሔርም የሕጉ ታቦት ትከተላቸው ነበር። ሰልፈኞችም ፊት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ካህናቱም ነጋሪት ይመቱ ነበር፤ ከታቦቱ በኋላ ይከተሉ የነበሩትም ቀንደ መለከቱን እየነፉ ይሄዱ ነበር። ኢያሱም ሕዝቡን፦ እንዳይጮኹ ማንም ድምፃቸውን እንዳይሰማ፥ እንዲጮኹ እስኪያዛቸውም ድረስ ከአፋቸው ቃል እንዳይወጣ አዘዛቸው። የእግዚአብሔርም የቃል ኪዳኑ ታቦት ሄደች፤ ከተማዪቱንም ዞረች፤ ወደ ሰፈርም ተመልሳ በዚያ አደረች። ኢያሱም በማግሥቱ ማለዳ ተነሣ፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን የሕጉን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱም ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፤ ተዋጊዎችም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፤ የቀሩትም ሕዝብ ከእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት በኋላ ይሄዱ ነበር፤ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። በሁለተኛውም ቀን የቀረው ሕዝብ ሁሉ ከተማዪቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ። በሰባተኛውም ቀን በነጋ ጊዜ ማልደው ተነሡ፤ እንደዚህም ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያም ቀን ብቻ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። እንዲህም ሆነ፤ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ በዞሩና ካህናቱ ቀንደ መለከቱን በነፉ ጊዜ፤ ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች አለ፥ “እግዚአብሔር ከተማዪቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። ከተማዪቱም በእርስዋም ያለው ሁሉ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልእክተኞች ስለ ሸሸገች ዘማዊቱ ረዓብ፥ ከእርስዋም ጋር በቤቷ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። እናንተ ግን እርም ብለን ከተውነው እንዳትወስዱ ተጠንቀቁ፤ ከእርሱም ተመኝታችሁ አትውሰዱ፤ ብትወስዱ ግን የእስራኤልን ሰፈር የተረገመች ታደርጓታላችሁ፤ እኛንም ታጠፉናላችሁ። ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ፥ የናስና የብረትም ዕቃ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ እግዚአብሔርም ግምጃ ቤት ይግባ።” ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፤ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ከተማዪቱ ገቡ፤ ሁሉም ወደ ፊታቸው ወደ ከተማዪቱ ሮጡ፤ ከተማዪቱንም እጅ አደረጉ።
ኢያሱ 6:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ እስራኤላውያንን ከመፍራት የተነሣ፣ ኢያሪኮ ፈጽማ ተዘግታ ነበር፤ ወደ ውጭ የሚወጣም ሆነ ወደ ውስጥ የሚገባ አልነበረም። እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ኢያሪኮን ከንጉሥዋና ከተዋጊዎቿ ጋር አሳልፌ በእጅህ ሰጥቻለሁ። ከተማዪቱን ከተዋጊዎቻችሁ ጋር አንድ ጊዜ ዙሩ፤ ይህንም ስድስት ቀን አድርጉ። ሰባት ካህናት፣ ሰባት ቀንደ መለከት ተሸክመው በታቦቱ ፊት ይውጡ፤ በሰባተኛውም ቀን ካህናቱ መለከት እየነፉ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ይዙሩ። የማያቋርጥ የመለከት ድምፅ ሲነፋ በምትሰሙበት ጊዜ፣ ሕዝቡ ሁሉ ከፍ ያለ ጩኸት ያሰማ፤ ከዚያም የከተማዪቱ ቅጥር ይፈርሳል፤ ሕዝቡም ወደ ላይ ይወጣል፤ እያንዳንዱም ሰው በቀጥታ ይገባል።” ስለዚህ የነዌ ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ፣ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፤ ሰባት ካህናትም ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ” አላቸው። ሕዝቡንም፣ “ወደ ፊት ሂዱ፤ ከተማዋን ዙሩ፤ የታጠቁ ተዋጊዎችም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ቀድመው ይሂዱ፤ ከተማዪቱንም ዙሩ” ሲል አዘዛቸው። ኢያሱም ለሕዝቡ ከተናገረ በኋላ፣ ሰባቱ ካህናት በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው መለከታቸውን እየነፉ ወደ ፊት ቀደሙ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦትም ተከተላቸው። የታጠቁ ተዋጊዎችም መለከት ከሚነፉት ካህናት ፊት ቀድመው ሲሄዱ፣ ደጀን የሆኑት ጠባቂዎች ደግሞ ታቦቱን ተከተሉ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ መለከቶቹ ባለማቋረጥ ይነፉ ነበር። ኢያሱ ሕዝቡን፣ “የማሸበሪያ ጩኸት አታሰሙ፤ ድምፃችሁ ከፍ ብሎ አይሰማ፤ ጩኹ እስከምላችሁም ቀን ድረስ ከአፋችሁ አንዲት ቃል አትውጣ፤ የምትጮኹት ከዚያ በኋላ ነው” ሲል አዘዛቸው። ስለዚህ ኢያሱ የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸክመው፣ ከተማዪቱን አንድ ጊዜ እንዲዞሩ አደረገ። ከዚያም ሕዝቡ ወደ ሰፈር ተመልሰው ዐደሩ። ኢያሱ በማግስቱም ማልዶ ተነሣ፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እየሄዱ፣ መለከቱን ባለማቋረጥ ይነፉ ጀመር፤ የታጠቁ ተዋጊዎችም እነዚህን በመቅደም ሲሄዱ፣ የደጀን ጠባቂዎቹ ደግሞ የእግዚአብሔርን ታቦት ይከተሉ ነበር፤ ካህናቱም ሳያቋርጡ መለከት ይነፉ ነበር። በሁለተኛውም ቀን ከተማዪቱን አንድ ጊዜ ከዞሩ በኋላ ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀን ሙሉም እንዲሁ አደረጉ። በሰባተኛው ቀን ገና ጎሕ ሲቀድ ተነሡ፤ እንደ በፊቱም ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ የዞሯትም በዚያን ቀን ብቻ ነው። በሰባተኛው ዙር ላይ ካህናቱ መለከቱን ሲነፉ፣ ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ሰጥቷችኋልና ጩኹ ከተማዪቱና በውስጧ ያለው ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ስለሆነ ፈጽማችሁ ዐጥፉ እኛ የላክናቸውን ሰላዮች ስለ ሸሸገች ጋለሞታዪቱ ረዓብ ብቻና ከእርሷ ጋር በቤቷ ውስጥ ያሉት ሁሉ ይትረፉ። እናንተ ግን ዕርም ከሆኑት ነገሮች አንዳች በመውሰድ በራሳችሁ ላይ ጥፋት እንዳታመጡ እጃችሁን ሰብስቡ፤ ያለዚያ የእስራኤልን ሰፈር ለጥፋት ትዳርጋላችሁ፤ ክፉ ነገር እንዲደርስበትም ታደርጋላችሁ፤ ብሩና ወርቁ እንዲሁም የናሱና የብረቱ ዕቃ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ስለሆነ፣ ወደ እግዚአብሔር ግምጃ ቤት ይግባ።” መለከቱ ሲነፋ ሕዝቡ ጮኸ፤ የመለከቱ ድምፅ ተሰምቶ፣ ሕዝቡ በኀይል ሲጮኽ ቅጥሩ ፈረሰ፤ እያንዳንዱም ሰው ሰተት ብሎ ገባ፤ ከተማዪቱም በእጃቸው ወደቀች።
ኢያሱ 6:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢያሪኮም ከእስራኤል ልጆች የተነሣ ፈጽማ ተዘግታ ነበር፥ ወደ እርስዋ የሚገባ ከእርስዋም የሚወጣ ማንም አልነበረም። እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፦ ተመልከት፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን ጽኑዓን ኃያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼአለሁ። ሰልፈኞቻችሁ ሁሉ ከተማይቱን አንድ ጊዜ ይዙሩአት፥ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ። ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይሸከሙ፥ በሰባተኛውም ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ። ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱን ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፥ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ይገባባታል። የነዌም ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ፦ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፥ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ወስደው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ አላቸው። ሕዝቡንም፦ ሂዱ፥ ከተማይቱንም ዙሩ፥ ሰልፈኞችም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ አለ። ኢያሱም ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ፥ ሰባቱ ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ፊት ሄዱ ቀንደ መለከቱንም ነፉ፥ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ይከተላቸው ነበር። ሰልፈኞቹም ቀንደ መለከቱን በሚነፉ በካህናቱ ፊት ይሄዱ ነበር፥ የቀረውም ሕዝብ ከታቦቱ በኋላ ይሄድ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። ኢያሱም ሕዝቡን፦ እኔ፦ ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታንሡ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፥ በዚያን ጊዜ ትጮኻላችሁ ብሎ አዘዛቸው። እንዲሁ የእግዚአብሔርን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማይቱን አዞረው፥ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው አደሩ። ኢያሱም ማለዳ ተነሣ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፥ ሰልፈኞቹም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፥ የቀሩትም ሕዝብ ከእግዚአብሔር ታቦት በኋላ ይመጡ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። በሁለተኛውም ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፥ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ። በሰባተኛውም ቀን በነጋ ጊዜ ማልደው ተነሡ፥ እንደዚህም ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፥ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን አለ፦ እግዚአብሔር ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። ከተማይቱም በእርስዋም ያለው ሁሉ ለእግዚአብሔር እርም ይሆናሉ፥ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች ጋለሞታይቱ ረዓብ ከእርስዋም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፥ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደ ሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁትማላችሁ። ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን፥ ወደ እግዚአብሔርም ግምጃ ቤት ይግባ። ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፥ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ወደ ፊቱ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ወሰዱ።
ኢያሱ 6:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እስራኤላውያንን ከመፍራት የተነሣ የኢያሪኮ ቅጽር በሮች ተዘግተው ነበር፤ ወደ ከተማይቱ መግባትም ሆነ መውጣት የሚችል ማንም አልነበረም፤ እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ኢያሪኮን ከንጉሥዋና ከወታደሮችዋ ጋር በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተና ወታደሮችህ እስከ ስድስት ቀን ድረስ በቀን አንድ ጊዜ የከተማይቱን ቅጽር በሰልፍ ትዞሩአታላችሁ። እያንዳንዳቸው እምቢልታ የያዙ ሰባት ካህናት ከቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ቀድመው ይሂዱ፤ በሰባተኛው ቀን ካህናቱ እምቢልታ እየነፉ አንተና ወታደሮችህ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ትዞሩአታላችሁ፤ ከዚያን በኋላ ካህናቱ በእምቢልታቸው ከፍተኛ ድምፅ እንዲሰማ ያድርጉ፤ እርሱንም እንደ ሰማችሁ ወዲያውኑ ሰዎቹ ሁሉ በከፍተኛ ድምፅ ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጽር ይፈርሳል፤ ከዚህም በኋላ መላው ሠራዊት ወደ ከተማይቱ ሰተት ብሎ በቀጥታ ይግባ።” ኢያሱም ካህናቱን ጠርቶ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፤ ከእናንተም ሰባታችሁ እምቢልታ ይዛችሁ ከታቦቱ ፊት ቅደሙ።” ሕዝቡንም እንዲህ ሲል አዘዘ፦ “ሂዱ፤ ከተማይቱን ዙሩ፤ ወታደሮቹም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ”። ኢያሱ ሕዝቡን ባዘዘው መሠረት በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀንደ መለከት የያዙ ሰባት ካህናት ቀንደ መለከቱን እየነፉ ወደፊት ሄዱ፤ የእግዚአብሔርም የቃል ኪዳኑ ታቦት ተከተላቸው። ወታደሮቹም ቀንደ እምቢልታ ከሚነፉት ካህናት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ካህናቱ እምቢልታውን ሳያቋርጡ እየነፉ ሕዝቡ ከታቦቱ በኋላ ይከተል ነበር። ኢያሱ ግን፦ “ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ እንዳትጮኹ፤ ወይም ድምፃችሁ እንዳይሰማ፤ እንዲያውም አንዲት ቃል እንኳ እንዳትናገሩ፤ ጩኹ ስላችሁ በዚያን ጊዜ ትጮኻላችሁ” ብሎ ሕዝቡን አዘዘ። በዚህ ዐይነት የእግዚአብሔር ታቦት ከተማዋን አንድ ጊዜ እንዲዞር አደረገ፤ ከዚያ በኋላ ሕዝቡ፥ ወደ ሰፈሩ ተመልሶ በዚያ ዐዳር ሆነ። በማግስቱ ኢያሱ በማለዳ ተነሣ፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱን እምቢልታ የያዙት ሰባት ካህናት እምቢልታቸውን ሳያቋርጡ እየነፉ ከእግዚአብሔር ታቦት ፊት ለፊት ሄዱ፤ መለከቱ ሳያቋርጥ እየተነፋ ወታደሮቹ ከካህናቱ ቀድመው ሌላው ሕዝብ ደግሞ ከታቦቱ በኋላ ይከተል ነበር። በዚህም በሁለተኛው ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ እስከ ስድስት ቀንም በዚሁ ዐይነት አደረጉ። በሰባተኛው ቀን ጎሕ ሲቀድ ማልደው ተነሥተው በዚሁ ተመሳሳይ ሁኔታ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩአት፤ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ የዞሩበት ቀን ይህ ብቻ ነበር። በሰባተኛው ዙር ካህናቱ እምቢልታ ሊነፉ በሚዘጋጁበት ጊዜ ኢያሱ ሕዝቡን፦ “እግዚአብሔር ከተማይቱን ስለ ሰጣችሁ ጩኹ!” ብሎ አዘዘ። “በከተማይቱና በውስጡ ያለው ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር የተረገመ ሆኖ መደምሰስ አለበት፤ ሴትኛ ዐዳሪዋ ግን የላክናቸውን ሰላዮች ደብቃ ስላዳነች መትረፍ የሚገባቸው እርስዋና ከእርስዋ ጋር በቤትዋ ያሉት ብቻ ናቸው። እናንተ ግን በእስራኤል ሰፈር ችግርንና ጥፋትን እንዳታስከትሉ መደምሰስ ከሚገባቸው ነገሮች ማናቸውንም ጓጒታችሁ ከመውሰድ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ብርና ወርቅ፥ ከነሐስ ወይም ከብረት የተሠራ ማናቸውም ነገር ለእግዚአብሔር የተለየ ይሁን፤ እርሱም በእግዚአብሔር የዕቃ ግምጃ ቤት መቀመጥ አለበት።” ስለዚህ እምቢልታ ተነፋ፤ ሕዝቡም የእምቢልታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ ከፍተኛ የጩኸት ድምፅ አሰሙ የከተማይቱም ቅጽሮች ፈረሱ፤ ከዚህም በኋላ ሠራዊቱ ኮረብታውን ወጥቶ ሰተት ብሎ ወደ ከተማይቱ በመግባት በቊጥጥሩ ሥር አደረጋት፤
ኢያሱ 6:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢያሪኮም ከእስራኤል ልጆች የተነሣ ፈጽማ ተዘግታ ነበር፤ ወደ እርሷ የሚገባ ከእርሷም የሚወጣ ማንም አልነበረም። ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ተመልከት፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን ጽኑዓን ኃያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼአለሁ። እናንተም ከተማይቱን ትዞሩአታላችሁ፥ ተዋጊዎቻችሁም ሁሉ ከተማይቱን በቀን አንድ ጊዜ ይዙሩአት፤ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ። ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይሸከሙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ። ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱን ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ እርሷ አቅንቶ በቀጥታ ይገባል።” የነዌም ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሱ፥ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በጌታ ታቦት ፊት ይሸከሙ።” ሕዝቡንም እንዲህ አለ፦ “ሂዱ፥ ከተማይቱንም ዙሩ፥ ተዋጊዎቹም በጌታ ታቦት ፊት ይሂዱ።” ኢያሱም ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ፥ ሰባቱ ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በጌታ ፊት ሄዱ ቀንደ መለከቱንም ነፉ፤ የጌታ ቃል ኪዳን ታቦት ይከተላቸው ነበር። ተዋጊዎቹም ቀንደ መለከቱን በሚነፉ በካህናቱ ፊት ይሄዱ ነበር፥ የኋላ ደጀንም የሆነው ሕዝብ ከታቦቱ በኋላ ይሄድ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “እኔ፦ ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታሰሙ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፤ ከዚያን በኋላ ግን ትጮኻላችሁ።” እንዲሁ የጌታን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማይቱን አዞረው፤ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው በዚያ አደሩ። ከዚያም በኋላ ኢያሱ ማልዶ ተነሣ፤ ካህናቱም የጌታን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በጌታ ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፤ ተዋጊዎቹም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፤ የኋላ ደጀንም የሆነው ሕዝብ ከጌታ ታቦት በኋላ ይመጡ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። በሁለተኛውም ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ። በሰባተኛውም ቀን ጎሕ ሲቀድ ማልደው ተነሡ፥ ተመሳሳይ በሆነ ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “ጌታ ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። ከተማይቱም በእርሷም ያለው ሁሉ ለጌታ እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች አመንዝራይቱ ረዓብ ከእርሷም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፤ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁታላችሁም። ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለጌታ የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ ጌታም ግምጃ ቤት ይግባ።” ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ በቀጥታ አቅንቶ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ያዝዋት።