ኢያሱ 4:1-9
ኢያሱ 4:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም ሆነ፤ ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ከሕዝቡ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ውሰድ፦ በዮርዳኖስ መካከል የካህናት እግር ከቆመበት ስፍራ ዐሥራ ሁለት ቀላል ድንጋዮችን እንዲያነሡ እዘዛቸው፤ ከእናንተም ጋር ውሰዱአቸው፤ ከዚያም ሌሊት በምታድሩበት ቦታ በየነገዳችሁ ጠብቋቸው።” ኢያሱም ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ ከእስራኤል ልጆች የታወቁትን ዐሥራ ሁለት ሰዎች ጠራ። ኢያሱም አላቸው፥ “በእኔና በእግዚአብሔር ፊት ወደ ዮርዳኖስ መካከል ዕለፉ፤ እያንዳንዱ ሰው በዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ቍጥር በትከሻው ላይ አንድ አንድ ድንጋይ ከዚያ ይሸከም። እነዚህም ምልክት ይሆኑላችኋል፤ ልጅህ ነገ፦ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው?’ ብሎ በጠየቀህ ጊዜ፥ ልጅህን እንዲህ ትለዋለህ፦ አንተ በምድር ሁሉ ጌታ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ስንሻገር የዮርዳኖስ ወንዝ ስለ ደረቀ ነው፤ እነዚህ ድንጋዮችም ለእስራኤል ልጆች ለዘለዓለም መታሰቢያ ይሆናሉ።” የእስራኤልም ልጆች ኢያሱ እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ የእስራኤልም ልጆች ዮርዳኖስን አካትተው በተሻገሩ ጊዜ እግዚአብሔር ኢያሱን እንደ አዘዘው በእስራኤል ነገድ ቍጥር ከዮርዳኖስ መካከል ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሥተው ወደ ሰፈራቸው ወሰዱ፤ በዚያም አኖሩአቸው። ኢያሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግሮች በቆሙበት ስፍራ በዮርዳኖስ መካከል ሌሎች ዐሥራ ሁለት ድንጋዮችን አቆመ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ።
ኢያሱ 4:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳኖስን ከተሻገረ በኋላ፣ እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ከሕዝቡ መካከል ከየነገዱ አንዳንድ ሰው፣ በድምሩ ዐሥራ ሁለት ሰው ምረጥ፤ እንዲሁም ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ልክ ካህናቱ ከቆሙበት ስፍራ ዐሥራ ሁለት ድንጋይ አንሥተው በመሸከም ከእናንተ ጋር እንዲሻገሩና ዛሬ በምታድሩበት ቦታ እንዲያኖሯቸው ንገራቸው።” ስለዚህ ኢያሱ ከእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ የሾማቸውን ዐሥራ ሁለት ሰዎች ጠራ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ከአምላካችሁ ከእግዚአብሔር ታቦት ፊት ቀድማችሁ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ዕለፉ፤ እያንዳንዳችሁም በእስራኤል ነገድ ቍጥር አንዳንድ ድንጋይ በትከሻችሁ ተሸከሙ፤ ይህም በመካከላችሁ ምልክት እንዲሆናችሁ ነው። ወደ ፊት ልጆቻችሁ፣ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው?’ ብለው ቢጠይቋችሁ፣ የዮርዳኖስ ወንዝ በእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት መቆሙን፣ እንዲሁም ታቦቱ ዮርዳኖስን በሚሻገርበት ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ መቆሙን፣ እነዚህ ድንጋዮች ለእስራኤል ሕዝብ የዘላለም መታሰቢያ መሆናቸውን ንገሯቸው።” እስራኤላውያንም ኢያሱ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔር ለኢያሱ በነገረውም መሠረት፣ በእስራኤል ነገዶች ቍጥር ልክ ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል አነሡ፤ ወደ ሰፈራቸውም ይዘው በመሻገር በዚያ አኖሯቸው። ኢያሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ቆመውበት በነበረው በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ሌሎች ዐሥራ ሁለት ድንጋዮችን አቆመ፤ እነዚህም ድንጋዮች እስከ ዛሬ ድረስ በዚሁ ስፍራ ይገኛሉ።
ኢያሱ 4:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም ሆነ፥ ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ ከሕዝቡ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ አሥራ ሁለት ሰዎች ምረጥና፦ በዮርዳኖስ መካከል የካህናት እግር ከቆመበት ስፍራ አሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሡ፥ ተሸክማችሁም በዚህ ሌሊት በምታድሩበት ስፍራ አኑሩአቸው ብለህ እዘዛቸው አለው። ኢያሱም ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ ከእስራኤል ልጆች ያዘጋጃቸውን አሥራ ሁለት ሰዎች ጠራ። ኢያሱም አላቸው፦ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ወደ ዮርዳኖስ መካከል እለፉ፥ ከእናንተም ሰው ሁሉ በእስራኤል ልጆች ነገድ ቁጥር በጫንቃው ላይ አንድ አንድ ድንጋይ ከዚያ ይሸከም። ይህም በመካከላችሁ ምልክት ይሆናል፥ ልጆቻችሁም በሚመጣው ዘመን፦ የእነዚህ ድንጋዮች ነገር ምንድር ነው? ብለው ሲጠይቁአችሁ፥ እናንተ፦ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት የዮርዳኖስ ውኃ ስለተቋረጠ ነው፥ ዮርዳኖስን በተሻገረ ጊዜ የዮርዳኖስ ውኃ ተቋረጠ፥ እነዚህም ድንጋዮች ለእስራኤል ልጆች ለዘላለም መታሰቢያ ይሆናሉ ትሉአቸዋላችሁ። የእስራኤልም ልጆች ኢያሱ እንዳዘዘ አደረጉ፥ እግዚአብሔርም ኢያሱን እንደ ተናገረው በእስራኤል ነገድ ቁጥር ከዮርዳኖስ መካከል አሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሥተው ወደሚያድሩበት ስፍራ ወሰዱ፥ በዚያም አኖሩአቸው። ኢያሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግሮች በቆሙበት ስፍራ በዮርዳኖስ መካከል ሌሎችን አሥራ ሁለት ድንጋዮች ተከለ፥ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ።
ኢያሱ 4:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በመውሰድ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ምረጥ፤ በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል፥ ካህናቱ ከቆሙበት ከዚያው ስፍራ ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ይዘው እንዲወጡ እዘዛቸው፤ ድንጋዮቹንም ወስደው ዛሬ ማታ በምትሰፍሩበት ስፍራ ያቆሙአቸው ዘንድ ንገር።” ኢያሱም የመረጣቸውን ዐሥራ ሁለት ሰዎች ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በአምላካችሁ በእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቀድማችሁ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ውረዱ፤ በእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ስም፥ እያንዳንዳችሁ አንዳንድ ድንጋይ በማንሣት በትከሻችሁ ተሸከሙ። እነዚህም ድንጋዮች እግዚአብሔር ያደረገውን ነገር ሁሉ ለእስራኤል ሕዝብ የሚያስታውሱ መታሰቢያዎች ይሆናሉ፤ በሚመጡትም ዘመናት ልጆቻችሁ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድናቸው?’ ብለው በሚጠይቁአችሁ ጊዜ፥ እናንተም እንዲህ ብላችሁ ትነግሩአቸዋላችሁ፦ ‘የአምላካችሁ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት በሚሻገርበት ጊዜ፥ የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ መውረዱን አቆመ፤ ስለዚህም እነዚህ ድንጋዮች በዚህ ስፍራ የተደረገውን ሁሉ ለዘለቄታው ለእስራኤል ሕዝብ የሚያስታውሱ መታሰቢያዎች ናቸው።’ ” ሰዎቹም ኢያሱ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔር ለኢያሱ በነገረው መሠረት በእስራኤል ነገዶች ቊጥር ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ዐሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ወደ ሰፈሩበት ቦታ ወስደው አስቀመጡ፤ ኢያሱም ደግሞ ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው በቆሙበት በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ዐሥራ ሁለት የመታሰቢያ ድንጋዮችን አቆሙ፤ እነዚያም ድንጋዮች እስከ ዛሬ በዚያው ይገኛሉ፤
ኢያሱ 4:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም ሆነ፤ ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ከሕዝቡ ዐሥራ ሁለት ሰዎች፥ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው ምረጥ፤ እንዲህም ብለህ እዘዛቸው፦ ‘በዮርዳኖስ መካከል የካህናት እግር ከቆመበት ስፍራ ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሡ፤ ተሸክማችሁም በዚህ ሌሊት በምታድሩበት ስፍራ አኑሩአቸው።’” ኢያሱም ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ ከእስራኤል ልጆች የሾማቸውን ዐሥራ ሁለት ሰዎች ጠራ። ኢያሱም እንዲህ አላቸው፦ “በአምላካችሁ በጌታ ታቦት ፊት በዮርዳኖስ መካከል እለፉ፤ ከእናንተም ሰው ሁሉ በእስራኤል ልጆች ነገድ ቍጥር በትከሻው ላይ አንድ አንድ ድንጋይ ከዚያ ይሸከም። ይህም በመካከላችሁ ምልክት ይሆናል፤ ልጆቻችሁም በሚመጣው ዘመን፦ ‘ለእናንተ እነዚህ ድንጋዮች የሚሰጡት ትርጒም ምንድነው?’ ብለው ሲጠይቁአችሁ፥ እናንተ እንዲህ ትሉአቸዋላችሁ፦ በጌታ ቃል ኪዳን ታቦት ፊት የዮርዳኖስ ውኃ ስለተቋረጠ ነው፤ ዮርዳኖስን በተሻገረ ጊዜ የዮርዳኖስ ውኃ ተቋረጠ፥ እነዚህም ድንጋዮች ለእስራኤል ልጆች ለዘለዓለም መታሰቢያ የሆኑ ናቸው።” የእስራኤልም ልጆች ኢያሱ እንዳዘዘ አደረጉ፤ ጌታም ኢያሱን እንደ ተናገረው በእስራኤል ነገድ ቍጥር ከዮርዳኖስ መካከል ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሥተው ወደሚያድሩበት ስፍራ ወሰዱ፥ በዚያም አኖሩአቸው። ኢያሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግሮች በቆሙበት ስፍራ በዮርዳኖስ መካከል ሌሎችን ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች አኖረ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ።