ኢያሱ 2:4-13
ኢያሱ 2:4-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፤ እርስዋም፥ “አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጡ፤ ከወዴት እንደ ሆኑ ግን አላወቅሁም፤ በሩም ሲዘጋ፥ ሲጨልምም ሰዎቹ ወጡ፤ ወዴት እንደ ሄዱ አላውቅም፤ ፈጥናችሁ ተከተሉአቸው፤ ምንአልባት ታገኙአቸው ይሆናል” አለቻቸው። እርስዋ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታ በተከመረ እንጨት መካከል በቀርከሃ ጠቅልላ ደብቃቸው ነበር። ሰዎቹም ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ በሚወስደው መንገድ ተከተሉአቸው፤ በሩም ተቈለፈ። እነዚህም ሳይተኙ ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው፥ “እግዚአብሔር ምድሪቱን አሳልፎ እንደ ሰጣችሁ ዐወቅሁ፤ እግዚአብሔር እናንተን መፍራትን በላያችን አምጥትዋልና፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ የተነሣ ቀልጠዋልና። ከግብፅ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት፥ እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። ይህንም ነገር ሰምተን በልባችን ደነገጥን፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ፥ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከእኛ የአንዱም እንኳን ነፍስ አልቀረም። አሁንም፥ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፤ እኔ ለእናንተ ቸርነት እንደ አደረግሁ እናንተ ደግሞ ለአባቴ ቤት ቸርነት እንድታደርጉ፥ በእውነት ምልክት ስጡኝ። የአባቴን ቤት፥ እናቴንም፥ ወንድሞቼንና ቤቴንም ሁሉ፥ ያላቸውንም ሁሉ አድኑ፤ ሰውነታችንንም ከሞት አድኑ።”
ኢያሱ 2:4-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሴቲቱ ግን ሁለቱን ሰዎች ተቀብላ ሸሽጋቸው ስለ ነበር እንዲህ አለች፤ “በርግጥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጥተዋል፤ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጡ አላውቅም። ጨልሞ የቅጥሩ በር ከመዘጋቱ በፊት ወጥተው ሄደዋል፤ በየት በኩል እንደ ሄዱ ግን እኔ አላውቅም፤ ልትደርሱባቸው ትችላላችሁና ፈጥናችሁ ተከታተሏቸው።” ነገር ግን ሰዎቹን ጣራ ላይ አውጥታ በረበረበችው የተልባ እግር ውስጥ ደብቃቸው ነበር። ሰዎቹም ሰላዮቹን በመከታተል ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ የሚወስደውን መንገድ ይዘው ሄዱ፤ አሳዳጆቹ ወጥተው እንደ ሄዱም የቅጥሩ በር ተዘጋ። ሰላዮቹ ከመተኛታቸው በፊት ሴቲቱ ወደ ጣራው ወጥታ፣ እንዲህ አለቻቸው፤ “እግዚአብሔር ይህችን ምድር እንደ ሰጣችሁ፣ እናንተንም መፍራት እንዳደረብን፣ የዚህች አገር ነዋሪዎች ሁሉ ልባቸው በፊታችሁ መቅለጡንም ዐውቃለሁ። ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ፣ እናንተም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ፈጽሞ ያጠፋችኋቸውን ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት፣ ሴዎንንና ዐግን ምን እንዳደረጋችኋቸው ሰምተናል። ይህን በሰማን ጊዜ ልባችን ቀለጠ፤ እናንተን ከመፍራት የተነሣም ያልተሸበረ ሰው አልነበረም፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ በላይም በሰማይ፣ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና። እንግዲህ እኔ በጎነትን እንዳሳየኋችሁ ሁሉ፣ እናንተም በጎነትን ለአባቴ ቤት እንድታሳዩ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፤ መተማመኛ የሚሆን ምልክትም ስጡኝ፤ የአባቴንና የእናቴን፣ የወንድሞቼንና የእኅቶቼን እንዲሁም የእነርሱ የሆነውን ነፍስ ሁሉ እንድታተርፉልኝ፤ ከሞትም አድኑን።”
ኢያሱ 2:4-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፥ እርስዋም፦ አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጡ፥ ከወዴት እንደሆኑ ግን አላወቅሁም፥ በሩም ሲዘጋ ሲጨልምም ሰዎቹ ወጡ፥ ወዴት እንደ ሄዱ አላውቅም፥ ፈጥናችሁ አሳድዱአቸው፥ ታገኙአቸውማላችሁ አለች። እርስዋ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታቸው ነበር፥ በዚያም በረበረበችው በተልባ እግር ውስጥ ሸሽጋቸው ነበር። ሰዎቹም ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ በሚወስደው መንገድ አሳደዱአቸው፥ አሳዳጆችም ከወጡ በኋላ በሩ ተቈለፈ። እነዚህም ሳይተኙ ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው፦ እግዚአብሔር ምድሪቱን እንደ ሰጣችሁ፥ እናንተንም መፍራት በላያችን እንደ ወደቀ፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ እንደ ቀለጡ አወቅሁ። ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። ይህንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከዚያ ወዲያ ለማንም ነፍስ አልቀረለትም። አሁንም፥ እባካችሁ፥ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፥ በእውነትም ምልክት ስጡኝ፥ እኔ ለእናንተ ቸርነት እንደ ሠራሁ እናንተ ደግሞ ለአባቴ ቤት ቸርነት እንድትሠሩ፥ አባቴንና እናቴንም ወንድሞቼንና እኅቶቼንም ያላቸውንም ሁሉ እንድታድኑ፥ ሰውነታችንንም ከሞት እንድታድኑ።
ኢያሱ 2:4-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፤ እርስዋም፦ “አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጡ፤ ከወዴት እንደ ሆኑ ግን አላውቅም፤ ጊዜው መሽቶ በመጨለሙ በሩ ሲዘጋ ሰዎቹ ወጥተው ሄዱ፤ ወዴት እንደ ሄዱ ግን አላውቅም፤ ፈጥናችሁ ብታሳድዱአቸው ትደርሱባቸዋላችሁ” አለች። እርስዋ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታ በዚያ በረበረበችው በተልባ እግር ውስጥ ሸሽጋቸው ነበር። የንጉሡም መልእክተኞች ከከተማይቱ ወጥተው ሄዱ፤ የቅጽር በሩም ተዘጋ፤ መልእክተኞቹም ሰላዮችን በመፈለግ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ እስከሚያልፈው ስፍራ ድረስ ሄዱ። ረዓብም ከመተኛታቸው በፊት ወዳሉበት የቤት ጣራ ወጥታ፥ እንዲህ አለቻቸው፦ “የሀገሪቱ ኗሪዎች በሙሉ በፍርሃት ተውጠው ልባቸው ቀለጠ፤ በሁላችንም ላይ ፍርሀት ስላደረብን እግዚአብሔር ምድሪቱን ለእናንተ እንደ ሰጠ ዐውቃለሁ፤ ግብጽን ለቃችሁ በወጣችሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ ሰምተናል፤ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ የነበሩትን ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት ሲሖንንና ዖግን እንዴት እንደ ገደላችሁም ሰምተናል። ስለዚህም ይህን ሁሉ ነገር በሰማን ጊዜ በፍርሃት ልባችን ቀለጠ፤ ወኔአችን ሁሉ ጠፋ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በእርግጥ የሰማይና የምድር አምላክ ነው። አሁንም እኔ ለእናንተ መልካም ነገር እንዳደረግሁላችሁ ሁሉ ቤተሰቤን ከጥፋት በማትረፍ መልካም ነገር ታደርጉልኝ ዘንድ ማሉልኝ፤ ለዚህም መተማመኛ የሚሆን ምልክት ስጡኝ። አባቴንና እናቴን፥ ወንድሞቼን፥ እኅቶቼንና የእነርሱን ቤተሰቦች ሁሉ ከሞት ለማዳን ቃል ግቡልኝ!”
ኢያሱ 2:4-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፤ እርሷም እንዲህ አለች፦ “አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጥተዋል፥ ከወዴት እንደ ሆኑ ግን አላወቅሁም፤ በሩ በሚዘጋበት ጊዜ ሲመሻሽ ሰዎቹ ወጥተው ሄደዋል፤ ወዴት እንደ ሄዱ ግን አላውቅም፤ ፈጥናችሁ አሳድዱአቸው፥ ትደርሱባቸዋላችሁ።” እርሷ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታቸው ነበር፤ በዚያም በረበረበችው በተልባ እግር ውስጥ ሸሽጋቸው ነበር። ሰዎቹም ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ እስከሚወስደው መንገድ ድረስ አሳደዱአቸው፤ አሳዳጆችም ከወጡ በኋላ በሩ ተዘጋ። እነርሱም ከመተኛታቸው በፊት ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው፦ “ጌታ ምድሪቱን እንደ ሰጣችሁ፥ ከእናንተም የተነሣ በፍርሃት መዋጣችንን፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ በፍርሃት እንደ ቀለጡ አወቅሁ። ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ ጌታ የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። ይህንንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፤ ጌታ አምላካችሁም በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከእግዲህ ወዲያ ሰው ሁሉ ሐሞተ ቢስ ሆኖአል። አሁንም፥ እባካችሁ፥ በጌታ ማሉልኝ፥ በእውነትም ምልክት ስጡኝ፥ እኔ ለእናንተ ቸርነት እንደሠራሁ እናንተ ደግሞ ለአባቴ ቤት ቸርነት ሥሩ፥ አባቴንና እናቴንም ወንድሞቼንና እኅቶቼንም ያላቸውንም ሁሉ አድኑ፥ ነፍሳችንንም ከሞት ታደጉ።”