ኢያሱ 10:7-14
ኢያሱ 10:7-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢያሱም ከእርሱም ጋር የነበሩ ተዋጊዎች ሁሉ፥ ጽኑዓን ኀያላኑም ሁሉ ከጌልጌላ ወጡ። እግዚአብሔርም ኢያሱን፥ “በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአቸዋለሁና አትፍራቸው፤ ከእነርሱም አንድ ሰው በፊትህ የሚተርፍ የለም፤” አለው። ኢያሱም ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ገሥግሦ በድንገት ደረሰባቸው። እግዚአብሔርም በእስራኤል ፊት አስደነገጣቸው፤ በገባዖንም ታላቅ መምታት መታቸው። ከእስራኤልም ልጆች ፊት እየሸሹ በቤትሖሮን ቍልቍለት ሲወርዱ፥ ወደ ዓዜቃና ወደ መቄዳ እስኪደርሱ ድረስ እግዚአብሔር ከሰማይ ታላላቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸውና ሞቱ፤ የእስራኤል ልጆች በሰይፍ ከገደሉአቸው ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት በለጡ። ያን ጊዜም እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆች እጅ አሞሬዎናውያንን አሳልፎ ሰጠ፤ እርሱ በገባዖን እነርሱን ባጠፋበት፥ እነርሱም ከእስራኤል ልጆች ፊት በጠፉበት ቀን ኢያሱ ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋገረ፤ እንዲህም አለ፥ “በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፤ በኢሎንም ሸለቆ ጨረቃ፤” እግዚአብሔርም ጠላቶቻቸውን እስኪያጠፋ ድረስ ፀሐይና ጨረቃ በየቦታቸው ቆሙ። ይህም እነሆ በዚህ መጽሐፍ በጊዜው ተጻፈ። ፀሐይም በሰማይ መካከል ቆመች፤ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል አልጠለቀችም። እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋ ነበርና እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም።
ኢያሱ 10:7-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ኢያሱ ምርጥ የሆኑትን ተዋጊዎች ሁሉ ጨምሮ ሰራዊቱን በሙሉ ይዞ ከጌልገላ ወጣ። እግዚአብሔርም ኢያሱን፣ “አትፍራቸው፤ ሁሉንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቻቸዋለሁ፤ አንዳቸውም እንኳ ሊቋቋሙህ አይችሉም” አለው። ኢያሱ ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ሲገሠግሥ ዐድሮ ድንገት ወረራቸው። እግዚአብሔርም የአሞራውያንን ነገሥታት በእስራኤል ፊት አሸበራቸው፤ በገባዖን እጅግ መታቸው፤ ወደ ቤትሖሮን በሚያስወጣውም መንገድ ሽቅብ ተከተላቸው፤ እስከ ዓዜቅና እስከ መቄዳም ድረስ አሳድዶ መታቸው። ከቤትሖሮን ወደ ዓዜቃ ቍልቍል በሚወስደው መንገድ ላይ፣ ከእስራኤላውያን ፊት በሚሸሹበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሰማይ ትልልቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸው፤ በእስራኤላውያን ሰይፍ ካለቁት ይልቅ በወረደው የበረዶ ድንጋይ ያለቁት በልጠው ተገኙ። እግዚአብሔር አሞራውያንን ለእስራኤል አሳልፎ በሰጠባት ዕለት፣ ኢያሱ እግዚአብሔርን በእስራኤል ፊት እንዲህ አለው፤ “ፀሓይ ሆይ፤ በገባዖን ላይ ቁሚ፤ ጨረቃም ሆይ፤ በኤሎን ሸለቆ ላይ ቀጥ በዪ።” ስለዚህ ሕዝቡ ጠላቶቹን እስኪበቀል ድረስ፣ ፀሓይ ባለችበት ቆመች፤ ጨረቃም አልተንቀሳቀሰችም። ይህም በያሻር መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል። ፀሓይ በሰማዩ መካከል ቆመች፤ ለመጥለቅም ሙሉ ቀን ፈጀባት። እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ዕለት ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ አልነበረም፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ተዋግቶ ነበርና።
ኢያሱ 10:7-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢያሱም ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰልፈኞች ሁሉ ጽኑዓን ኃያላኑም ሁሉ ከጌልገላ ወጡ። እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአቸዋለሁና አትፍራቸው፥ ከእነርሱም አንድ ሰው የሚቋቋምህ የለም አለው። ኢያሱም ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ገሥግሦ በድንገት መጣባቸው። እግዚአብሔርም በእስራኤል ፊት አስደነገጣቸው፥ በገባዖንም ታላቅ መምታት መታቸው፥ በቤትሖሮንም ዐቀበት በመንገድ አሳደዳቸው፥ እስከ ዓዜቃና እስከ መቄዳ ድረስ መታቸው። ከእስራኤልም ልጆች ፊት እየሸሹ በቤትሖሮን ቁልቁለት ሲወርዱ፥ ወደ ዓዜቃ እስኪደርሱ ድረስ እግዚአብሔር ከሰማይ ታላላቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸውና ሞቱ፥ የእስራኤል ልጆች በሰይፍ ከገደሉአቸው ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት በለጡ። እግዚአብሔርም በእስራኤል ልጆች እጅ አሞራውያንን አሳልፎ በሰጠ ቀን ኢያሱ እግዚአብሔርን ተናገረ፥ በእስራኤልም ፊት እንዲህ አለ፦ በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፥ በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ፥ ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመ፥ ጨረቃም ዘገየ። ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ፀሐይም በሰማይ መካከል ዘገየ፥ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም። እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋ ነበረና እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም።
ኢያሱ 10:7-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህም ኢያሱና መላው ሠራዊት፥ ምርጥ የሆኑት ወታደሮች ጭምር ከጌልጌላ ወጥተው ሄዱ፤ እግዚአብሔርም ኢያሱን “እነርሱን አትፍራቸው፤ እኔ አንተን በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጅሃለሁ፤ ከእነርሱ አንድም የሚቋቋምህ አይኖርም” አለው። ኢያሱም ሌሊቱን ሙሉ ከጌልጌላ ወደ ገባዖን ሲገሠግሥ ዐድሮ በአሞራውያን ላይ ድንገተኛ አደጋ ጣለባቸው። እግዚአብሔርም በእስራኤል ሠራዊት ፊት አሞራውያን በድንጋጤ እንዲሸበሩ አደረገ፤ እስራኤላውያንም እነርሱን በገባዖን ዐረዱአቸው፤ የቀሩትንም በቤትሖሮን በኩል እስከ ተራራው መተላለፊያ ቊልቊለት እስከ ዐዜቃና እስከ ማቄዳ ድረስ አሳደዱአቸው። አሞራውያን በመተላለፊያው ቊልቊለት ከእስራኤላውያን ሠራዊት በሚሸሹበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር እስከ ዐዜቃ ድረስ ከሰማይ ታላላቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸው፤ ስለዚህም እስራኤላውያን ከገደሉአቸው ይልቅ በበረዶው ድንጋይ የሞቱት እጅግ ብዙዎች ነበሩ። እግዚአብሔር አሞራውያንን ለእስራኤላውያን አሳልፎ በሰጠበት ቀን ኢያሱ ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋገረ፤ እርሱም በእስራኤል ፊት እንዲህ አለ፦ “ፀሐይ በገባዖን፥ ጨረቃም በኤሎን ሸለቆ ላይ ይቁሙ” አለ። ስለዚህም የእስራኤል ሕዝብ ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመ፤ ጨረቃም ካለችበት ሳትንቀሳቀስ ቈየች፤ ይህም በያሻር መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል። ሳይንቀሳቀስ በሰማይ መካከል ቆመ፤ ቀኑንም ሙሉ ሳይጠልቅ ቈየ፤ እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት፥ እንደዚያ ያለ ቀን፥ ከዚያም በፊት ሆነ ከዚያ ወዲህ ታይቶ አይታወቅም፤ በእርግጥም እግዚአብሔር ከእስራኤል ጐን ተሰልፎ ይዋጋላቸው ነበር።
ኢያሱ 10:7-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢያሱም ከእርሱም ጋር የነበሩ ተዋጊዎች ሁሉ ጽኑዓን ኃያላኑም ሁሉ ከጌልገላ ወጡ። ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአቸዋለሁና አትፍራቸው፤ ከእነርሱም አንድም ሰው የሚቋቋምህ የለም።” ኢያሱም ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ገሥግሦ በድንገት መጣባቸው። ጌታም በእስራኤል ፊት አስደነገጣቸው፤ በገባዖንም በጽኑ ውግያ ድል አደረጓቸው፥ በቤትሖሮንም ዐቀበት በሆነው መንገድ ላይ አሳደዳቸው፥ እስከ ዓዜቃና እስከ መቄዳ ድረስ መታቸው። ከእስራኤልም ልጆች ፊት እየሸሹ የቤትሖሮንን ቁልቁለት በመውረድ ላይ ሳሉ፥ ዓዜቃ እስኪደርሱ ድረስ ጌታ ከሰማይ ታላላቅ ድንጋይ አወረደባቸውና ሞቱ፤ የእስራኤል ልጆች በሰይፍ ከገደሉአቸው ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት በለጡ። ጌታም በእስራኤል ልጆች እጅ አሞራውያንን አሳልፎ በሰጠ ቀን ኢያሱ ለጌታ እንዲህ ብሎ ተናገረ፤ የእስራኤልም ልጆች እያዩ እንዲህ አለ፦ “በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፥ በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ፤” ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመች፥ ጨረቃም ዘገየች። ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ፀሐይም በሰማይ መካከል ጸንታ ቆመች፥ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለችም። ጌታ ለእስራኤል ይዋጋ ነበረና ጌታ የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም።