ዮሐንስ 9:1-15
ዮሐንስ 9:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚያም ሲያልፍ ዕዉር ሆኖ የተወለደውን ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱም፥ “መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕዉር ሆኖ የተወለደው በማን ኀጢኣት ነው? በራሱ ነውን? ወይስ በወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “የእግዚአብሔር ሥራ ሊገለጥበት ነው እንጂ እርሱ አልበደለም፤ ወላጆቹም አልበደሉም። ነገር ግን ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ልሠራ ይገባኛል፤ ማንም ሥራ ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለችና። በዓለም ሳለሁ፤ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ።” ይህንም ብሎ በምድር ላይ ምራቁን እንትፍ አለ፤ በምራቁም ጭቃ አድርጎ የዕዉሩን ዐይኖች ቀባው። እንዲህም አለው፥ “ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” ትርጓሜውም የተላከ ማለት ነው፤ ሄዶም ታጠበና እያየ ተመለሰ። ጎረቤቶቹና ቀድሞ የሚያውቁት፥ ሲለምንም ያዩት የነበሩት ግን፥ “ይህ በመንገድ ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለም?” አሉ። “ይህ እርሱ ነው” ያሉ አሉ፤ ሌሎችም፥ “አይደለም፤ ይመስለዋል እንጂ” አሉ፤ እርሱ ራሱ ግን፥ “እኔ ነኝ” አለ። እነርሱም፥ “ዐይኖችህ እንዴት ተገለጡ?” አሉት። እርሱም መልሶ፥ “ኢየሱስ የሚባለው ሰው በምራቁ ጭቃ አድርጎ ዐይኖችን ቀባኝና ሂደህ በሰሊሆም ውኃ ታጠብ አለኝ፤ ሄጄም ታጠብሁና አየሁ” አላቸው። አይሁድም፥ “ሰውየው የት አለ?” አሉት፤ እርሱም፥ “አላውቅም” አላቸው። ያን ዕዉር ሆኖ የተወለደውንም ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ጌታችን ኢየሱስ በምራቁ ጭቃ አድርጎ ዐይኖቹን ያበራበት ቀኑ ሰንበት ነበርና። ፈሪሳውያንም እንዴት እንዳየ ዳግመኛ ጠየቁት፤ እርሱም፥ “በምራቁ ጭቃ አድርጎ በዐይኖች አኖረው፥ ታጥቤም አየሁ” አላቸው።
ዮሐንስ 9:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በመንገድ ሲያልፍም ከተወለደ ጀምሮ ዐይነ ስውር የሆነ ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ረቢ፤ ይህ ሰው ዐይነ ስውር ሆኖ እንዲወለድ ኀጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ራሱ ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እርሱ ወይም ወላጆቹ ኀጢአት አልሠሩም፤ ይህ የሆነው ግን የእግዚአብሔር ሥራ በርሱ ሕይወት እንዲገለጥ ነው። ቀን ሳለ፣ የላከኝን ሥራ መሥራት አለብን፤ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል፤ በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ።” ይህን ካለ በኋላ፣ በምድር ላይ እንትፍ ብሎ በምራቁ ጭቃ አበጀ፤ የሰውየውንም ዐይን ቀባና፣ “ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው፤ ሰሊሆም ማለት “የተላከ” ማለት ነው። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ እያየም ተመልሶ መጣ። ጎረቤቶቹና ከዚህ ቀደም ብሎ ሲለምን ያዩት ሰዎች፣ “ይህ ሰው ተቀምጦ ሲለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። አንዳንዶቹም፣ “በርግጥ እርሱ ነው” አሉ። ሌሎችም፣ “ይመስለዋል እንጂ እርሱ አይደለም” አሉ። እርሱ ግን፣ “እኔው ነኝ” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም፣ “ኢየሱስ የሚሉት ሰው ጭቃ አድርጎ ዐይኔን ቀባኝ፤ ወደ ሰሊሆም ሄጄ እንድታጠብም ነገረኝ፤ ሄጄ ታጠብሁ፤ ማየትም ቻልሁ” ሲል መለሰ። እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ያ ሰው የት አለ?” አሉት። እርሱም፣ “እኔ አላውቅም” አለ። እነርሱም ዐይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ኢየሱስ ጭቃ የሠራበት፣ የሰውየውንም ዐይን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበር። ስለዚህ ፈሪሳውያንም እንዴት ማየት እንደ ቻለ ጠየቁት። ሰውየውም፣ “እርሱ ዐይኔን ጭቃ ቀባኝ፤ እኔም ታጠብሁ፤ ይኸው አያለሁ” አላቸው።
ዮሐንስ 9:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሲያልፍም ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱም፦ “መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲ ብሎ መልሰ፦ “የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም። ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች። በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ።” ይህን ብሎ ወደ መሬት እንትፍ አለ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዕውሩን ዓይኖች ቀባና፦ “ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው፤ ትርጓሜው የተላከ ነው። ስለዚህ ሄዶ ታጠበ እያየም መጣ። ጐረቤቶቹም ቀድሞም ሲለምን አይተውት የነበሩ፦ “ይህ ተቀምጦ ይለምን የነበረ አይደለምን?” አሉ። ሌሎች፦ “እሩ ነው” አሉ፤ ሌሎች፦ “አይደለም እርሱን ይመስላል እንጂ” አሉ፤ እርሱ፦ “እኔ ነኝ አለ።” ታድያ፦ “ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” አሉት። እርሱ መልሶ፦ “ኢየሱስ የሚባለው ሰው ጭቃ አድርጎ አይኖቼን ቀባና፦ ‘ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ ሄደህ ታጠብ’ አለኝ፤ ሄጄ ታጥቤም አየሁ” አለ። “ያ ሰው ወዴት ነው?” አሉት። “አላውቅም” አለ። በፊት ዕውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ኢየሱስም ጭቃ አድርጎ ዓይኖቹን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ ፈሪሳውያን ደግሞ እንዴት እንዳየ እንደ ገና ጠየቁት። እርሱም፦ “ጭቃ በዓይኖቼ አኖረ ታጠብሁም አያለሁም” አላቸውም።
ዮሐንስ 9:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ በመንገድ ሲያልፍ ዕውር ሆኖ የተወለደ ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ የተወለደው በማን ኃጢአት ነው? በራሱ ኃጢአት ነውን ወይስ በወላጆቹ?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ይህ ሰው ዕውር ሆኖ የተወለደው በእርሱ ወይም በወላጆቹ ኃጢአት ምክንያት አይደለም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው። ቀን ሆኖ ሳለ የላከኝን ሥራ መሥራት አለብኝ፤ ማንም ሰው ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል። በዓለም ላይ ሳለሁ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ።” ይህን ከተናገረ በኋላ በመሬት ላይ እንትፍ አለና በምራቁ ዐፈር ለወሰ፤ በጭቃውም የዕውሩን ዐይኖች ቀባና፥ “ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው። (ሰሊሆም “የተላከ” ማለት ነው።) ስለዚህ ሰውየው ሄዶ ታጠበና እያየ ተመለሰ። ጐረቤቶቹና ቀድሞ ሲለምን ያዩት የነበሩ ሰዎች፥ “ይህ ሰው ያ ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። አንዳንዶች “አዎ፥ እርሱ ነው!” አሉ፤ ሌሎች ደግሞ “እርሱን ይመስላል እንጂ እርሱ አይደለም!” አሉ። እርሱ ግን “እኔው ነኝ!” አለ። ሰዎቹም “ታዲያ፥ ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” አሉት። እርሱም “ኢየሱስ የተባለ ሰው ጭቃ ለውሶ ዐይኖቼን ቀባና ‘ወደ ሰሊሆም ሄደህ ታጠብ’ አለኝ፤ እኔም ሄጄ ታጠብኩና ለማየት ቻልኩ” ሲል መለሰ። እነርሱም “ሰውየው አሁን የት አለ?” አሉት። እርሱም “የት እንዳለ እኔ አላውቅም” አላቸው። ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ዕውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ኢየሱስ ጭቃ ለውሶ የሰውዬውን ዐይኖች እንዲበሩ ያደረገው በሰንበት ቀን ነበር፤ ፈሪሳውያን “እንዴት ማየት ቻልክ?” ብለው ሰውየውን እንደገና ጠየቁት። እርሱም “ዐይኖቼ ላይ ጭቃ አደረገልኝና ታጠብኩ፤ ከዚያም በኋላ ማየት ቻልኩ” አለ።
ዮሐንስ 9:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሲያልፍም ከመወለዱ ጀምሮ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱም “መምህር ሆይ! ይህ ሰው ዐይነ ስውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአትን የሠራው ማን ነው? እርሱ ነው ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም። ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች። በዓለም እስካለሁ ድረስ የዓለም ብርሃን ነኝ።” ይህንንም ብሎ ወደ መሬት እንትፍ አለ፤ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዐይነ ሥውሩን ዐይኖች ቀባና “ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ፤” አለው፤ ትርጓሜውም “የተላከ” ማለት ነው። ስለዚህም ሄዶ ታጠበ፤ እያየም መጣ። ጐረቤቶቹና ቀድሞ ሲለምን አይተውት የነበሩ “ይህ ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። ሌሎችም “እርሱ ነው፤” አሉ፤ ሌሎች ደግሞ “እርሱን ይመስላል እንጂ፥ እርሱ አይደለም፤” አሉ፤ እርሱ “እኔ ነኝ፤” አለ። ታድያ “ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” አሉት። እርሱ መልሶ “ኢየሱስ የሚባለው ሰው ጭቃ አድርጎ ዐይኖቼን ቀባና ‘ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ ሄደህ ታጠብ፤’ አለኝ፤ ሄጄ ታጥቤም አየሁ፤” አለ። “ያ ሰው ወዴት ነው?” አሉት። “አላውቅም” አለ። በፊት ዐይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ኢየሱስም ጭቃ አድርጎ ዐይኖቹን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ ፈሪሳውያን እንዴት እንዳየ እንደገና ጠየቁት። እርሱም “ጭቃ በዐይኖቼ አኖረ፤ ታጠብሁም፤ አያለሁም፤” አላቸውም።