ዮሐንስ 8:9-12
ዮሐንስ 8:9-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እነርሱ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ኅሊናቸው ወቅሶአቸው ከሽማግሌዎች ጀምሮ እስከ ኋለኞቹ ድረስ፥ አንዳንድ እያሉ ወጡ፤ ጌታችን ኢየሱስም ብቻውን ቀረ፤ ሴትዮዪቱም በመካከል ቆማ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም ቀና ብሎ ወደ እርስዋ ተመለከተና እንዲህ አላት፥ “አንቺ ሴት፥ የሚከሱሽ ወዴት አሉ?” እርስዋም፥ “ጌታ ሆይ፥ የማየው የለም” ብላ መለሰችለት፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔም አልፈርድብሽም፤ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ዳግመኛ ኀጢኣት አትሥሪ” አላት። ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ፥ “የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም” ብሎ ተናገራቸው።
ዮሐንስ 8:9-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይህን እንደ ሰሙ፣ ከሽማግሌዎች ጀምሮ አንድ በአንድ ወጡ፤ ሴትዮዋም እዚያው ፊቱ እንደ ቆመች ኢየሱስ ብቻውን ቀረ። ኢየሱስም ቀና ብሎ፣ “አንቺ ሴት፣ ሰዎቹ የት ሄዱ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት። እርሷም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድም የለም” አለች። ኢየሱስም፣ “እኔም አልፈርድብሽም፤ በይ ሂጂ፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥሪ” አላት። ኢየሱስ እንደ ገና ለሰዎቹ፣ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም” አላቸው።
ዮሐንስ 8:9-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸዋና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች። ኢየሱስም ቀና ብሎ ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ፦ “አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት። እርስዋም፦ “ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ” አለች። ኢየሱስም፦ “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ” አላት። ደግሞም ኢየሱስ፦ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሎ ተናገራቸው።
ዮሐንስ 8:9-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ ከሽማግሌዎች ጀምሮ ሁሉም አንድ በአንድ ከዚያ ሄዱ፤ ስለዚህ ኢየሱስ በመካከል ቆማ ከነበረችው ሴት ጋር ብቻውን ቀረ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ቀና ብሎ፥ “አንቺ ሴት ከሳሾችሽ የት አሉ? የፈረደብሽ ማንም የለምን?” አላት። እርስዋም “ጌታ ሆይ! ማንም የለም” አለች። ኢየሱስም “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ፤ ዳግመኛ ኃጢአት አትሥሪ” አላት። እንደገናም ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ እኔን የሚከተል ሁሉ የሕይወት ብርሃን ያገኛል፤ በጨለማም አይመላለስም” ሲል ተናገራቸው።
ዮሐንስ 8:9-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነርሱም ይህን ሲሰሙ ከሽማግሌዎች ጀምሮ አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ፤ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች። ኢየሱስም ቀና ብሎ “አንቺ ሴት! ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት። እርሷም “ጌታ ሆይ! አንድም እንኳን፤” አለች። ኢየሱስም “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ፤ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ፤” አላት። ደግሞም ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሎ ተናገራቸው።