ዮሐንስ 8:12-19
ዮሐንስ 8:12-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ እንደ ገና ለሰዎቹ፣ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም” አላቸው። ፈሪሳውያንም፣ “አንተ ስለ ራስህ ስለምትመሰክር ምስክርነትህ ተቀባይነት የለውም” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ከየት እንደ መጣሁና ወዴት እንደምሄድ ስለማውቅ ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁ ወይም ወዴት እንደምሄድ የምታውቁት ነገር የለም። እናንተ እንደ ሰው አስተሳሰብ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም አልፈርድም፤ ብፈርድም፣ ከላከኝ ከአብ ጋር እንጂ ብቻዬን ስላልሆንሁ ፍርዴ ትክክል ነው። የሁለት ሰዎች ምስክርነት ተቀባይነት እንዳለው በሕጋችሁ ተጽፏል። ስለ ራሴ የምመሰክር አንዱ እኔ ነኝ፤ ሌላውም ምስክሬ የላከኝ አብ ነው።” ከዚያም፣ “አባትህ የት ነው?” አሉት። ኢየሱስም፣ “አባቴንም እኔንም አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ፣ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” ሲል መለሰላቸው።
ዮሐንስ 8:12-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ፥ “የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም” ብሎ ተናገራቸው። ፈሪሳውያንም፥ “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ እንግዲያስ ምስክርነትህ እውነት አይደለም” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እኔ ስለራሴ ብመሰክርም ምስክርነቴ እውነት ነው፤ ከየት እንደመጣሁ፥ ወዴት እንደምሄድም አውቃለሁና፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁ ወዴት እንደምሄድም አታውቁም። እናንተ ሥጋዊ ፍርድን ትፈርዳላችሁ፤ እኔ ግን በማንም አልፈርድም። እኔ ብፈርድም እውነትን እፈርዳለሁ፤ እኔና የላከኝ አብ ነን እንጂ አንድ ብቻዬን አይደለሁምና። የሁለት ሰዎች ምስክርነት የታመነ እንደ ሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአል። እኔ ስለ ራሴ ምስክር ነኝ፤ የላከኝ አብም ይመሰክርልኛል።” እነርሱም፥ “አባትህ የት ነው?” አሉት፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔን አታውቁም፤ አባቴንም አታውቁም፤ እኔንስ ብታውቁ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር” ብሎ መለሰላቸው።
ዮሐንስ 8:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ደግሞም ኢየሱስ፦ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሎ ተናገራቸው። ፈሪሳውያንም፦ “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም” አሉት። ኢየሱስ መለሰ አላቸውም፦ “እኔ ስለ ራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከወዴት እንደ መጣሁ ወዴትም እንድሄድ አታውቁም። እናንተ ሥጋዊ ፍርድን ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በአንድ ሰው ስንኳ አልፈርድም። የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁምና እኔ ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው። የሁለት ሰዎችም ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ በሕጋችሁ ትጽፎአል። ስለ ራሴ የምመሰክር እኔ ነኝ፥ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል።” እንግዲህ፦ “አባትህ ወዴት ነው?” አሉት። ኢየሱስ መልሶ፦ “እኔንም ወይም አባቴንም አታውቁም፤ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር” አላቸው።
ዮሐንስ 8:12-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንደገናም ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ እኔን የሚከተል ሁሉ የሕይወት ብርሃን ያገኛል፤ በጨለማም አይመላለስም” ሲል ተናገራቸው። ፈሪሳውያን “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ምንም እንኳ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ከየት እንደ መጣሁ፥ ወዴትም እንደምሄድ ስለማውቅ ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁና ወዴት እንደምሄድ አታውቁም። እናንተ በሥጋዊ አስተሳሰብ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም ላይ አልፈርድም። ብፈርድም እንኳ የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነና እኔ ብቻዬን ስለማልፈርድ ፍርዴ እውነት ነው፤ የሁለት ሰዎች ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአል። ስለዚህ እኔ ስለ ራሴ እመሰክራለሁ፤ የላከኝ አብም ስለ እኔ ይመሰክራል።” በዚያን ጊዜ እነርሱ “አባትህ የት አለ?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም “እኔንም ሆነ አባቴን አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” ሲል መለሰላቸው።
ዮሐንስ 8:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ደግሞም ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሎ ተናገራቸው። ፈሪሳውያንም “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም፤” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ ስለ እራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድምሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንደምሄድ አታውቁም። እናንተ በሥጋዊ መንገድ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በአንድ ሰው ላይ እንኳ አልፈርድም። የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነውና፥ ብቻዬንም አይደለሁምና፥ እኔ ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው። የሁለት ሰዎችም ምስክርነት እውነት እንደሆነ በሕጋችሁ ትጽፎአል። ስለ እራሴ የምመሰክረው እኔ ነኝ፤ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል።” ስለዚህም “አባትህ ወዴት ነው?” አሉት። ኢየሱስ መልሶ “እኔንም ሆነ አባቴንም አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ደግሞ ባወቃችሁ ነበር፤” አላቸው።