ዮሐንስ 6:1-15
ዮሐንስ 6:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ወደ ጥብርያዶስ ሄደ። በበሽተኞችም ላይ ያደረገውን ተአምራት ስለ አዩ ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር በዚያ ተቀመጠ። የአይሁድ የፋሲካ በዓልም ቀርቦ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም ዐይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ሲመጡ አየና ፊልጶስን፥ “ለእነዚህ ሰዎች የምናበላቸው እንጀራ ከወዴት እንግዛ?” አለው። ሲፈትነው ይህን አለ እንጂ፥ እርሱስ የሚያደርገውን ያውቅ ነበር። ፊልጶስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “ከእነርሱ ለእያንዳንዱ ጥቂት ጥቂት ይወስዱ ዘንድ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም።” ከደቀ መዛሙርቱም አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ እንዲህ አለው፥ “አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን እነዚህ ይህን ለሚያህል ሰው ምን ይበቃሉ?” ጌታችን ኢየሱስም፥ “ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ” አለ፤ የዚያ ቦታም ሣሩ ብዙ ነበር፤ ወንዶቹም በመስኩ ላይ ተቀመጡ፤ ቍጥራቸውም አምስት ሺህ ያህል ነበር። ጌታችን ኢየሱስም ያን እንጀራ ይዞ አመሰገነ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው፤ ከዓሣውም እንዲሁ የፈለጉትን ያህል ሰጡአቸው። ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፥ “ከቍርስራሹ ምንም የሚወድቅ እንዳይኖር የተረፈውን ቍርስራሽ አንሡ፤” አላቸው። እነርሱም ሰበሰቡ፥ በልተው ከጠገቡ በኋላም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈው ቍርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሞላ። ሕዝቡም ጌታችን ኢየሱስ ያደረገውን ተአምራት አይተው፥ “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው” አሉ። ጌታችን ኢየሱስም መጥተው ነጥቀው ሊያነግሡት እንደሚሹ ዐወቀባቸውና ብቻውን ወደ ተራራ ሄደ።
ዮሐንስ 6:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ጥብርያዶስ የተባለውን የገሊላ ባሕር ተሻግሮ ራቅ ወዳለው የባሕሩ ዳርቻ ሄደ። ብዙ ሰዎችም በሽተኞችን በመፈወስ ያደረጋቸውን ታምራዊ ምልክቶች ስላዩ ተከተሉት። ከዚያም ኢየሱስ ወደ ተራራ ወጥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። የአይሁድ የፋሲካ በዓልም ተቃርቦ ነበር። ኢየሱስም ቀና ብሎ ሲመለከት፣ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየ፤ ፊልጶስንም፣ “እነዚህ ሰዎች እንዲበሉ እንጀራ ከየት እንግዛ?” አለው። ይህን የጠየቀው ሊፈትነው እንጂ ራሱ ሊያደርግ ያሰበውን ያውቅ ነበር። ፊልጶስም፣ “እያንዳንዱ ሰው ትንሽ ትንሽ እንዲቃመስ ለማድረግ፣ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ እንኳ አይበቃም” ሲል መለሰ። ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስም፣ እንዲህ አለ፤ “አምስት ትንንሽ የገብስ እንጀራና ሁለት ትንንሽ ዓሣ የያዘ አንድ ልጅ እዚህ አለ፤ ይህ ግን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ እንዴት ይዳረሳል?” ኢየሱስም፣ “ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉ” አለ። በዚያ ቦታ ብዙ ሣር ነበረ፤ አምስት ሺሕ ያህል ወንዶችም ተቀመጡ። ኢየሱስ አምስቱን እንጀራ አንሥቶ አመሰገነ፤ ለተቀመጡትም የሚፈልጉትን ያህል ዐደለ፤ ዓሣውንም እንዲሁ። ሁሉም በልተው ከጠገቡ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ከተረፈው ቍርስራሽ ምንም እንዳይባክን ሰብስቡ” አላቸው። እነርሱም፣ ከተበላው አምስት የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቍርስራሽ ሰብስበው ዐሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ። ሰዎቹም ኢየሱስ ያደረገውን ታምራዊ ምልክት ካዩ በኋላ፣ “ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ በርግጥ ይህ ነው” አሉ። ኢየሱስም ሰዎቹ መጥተው በግድ ሊያነግሡት እንዳሰቡ ዐውቆ እንደ ገና ብቻውን ወደ ተራራ ገለል አለ።
ዮሐንስ 6:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ፤ እርሱም የጥብርያዶስ ባሕር ነው። በበሽተኞችም ያደረገውን ምልክቶች ስላዩ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። የአይሁድ በዓልም ፋሲካ ቀርቦ ነበር። ኢየሱስም ዓይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን፦ እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን? አለው። ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ሊፈትነው ይህን ተናገረ። ፊልጶስ፦ እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲቀበሉ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም ብሎ መለሰለት። ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ፦ አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል? አለው። ኢየሱስም፦ ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ አለ። በዚያም ስፍራ ብዙ ሣር ነበረበት። ወንዶችም ተቀመጡ ቍጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር። ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ፥ አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው እንዲሁም ከዓሣው በፈለጉት መጠን። ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፦ አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ የተረፈውን ቍርስራሽ አከማቹ አላቸው። ሰለዚህ አከማቹ፥ ከበሉትም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቍርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሞላ። ከዚህ የተነሣ ሰዎቹ ኢየሱስ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ፦ ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው አሉ። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ያነግሡት ዘንድ ሊመጡና ሊነጥቁት እንዳላቸው አውቆ ደግሞ ወደ ተራራ ብቻውን ፈቀቅ አለ።
ዮሐንስ 6:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ጥብርያዶስ ወደሚባለው ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ። ብዙ ሰዎች ኢየሱስ በሽተኞችን በመፈወስ ያደረገውን ተአምር ስላዩ ተከተሉት። ኢየሱስ ወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። የአይሁድ ፋሲካ በዓል ቀርቦ ነበር። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ ቀና ብሎ አየና ፊልጶስን፦ “ለዚህ ሁሉ ሰው የሚበቃ ምግብ ከየት መግዛት እንችላለን?” አለው። ኢየሱስ ይህን የተናገረው ፊልጶስን ለመፈተን ነበር እንጂ፥ የሚያደርገውንስ እርሱ ራሱ ያውቅ ነበር። ፊልጶስም “ለእያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ ቊራሽ እንኳ እንዲሰጣቸው የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም” ሲል መለሰለት። ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ እንዲህ አለ፦ “አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ አንድ ልጅ እዚህ አለ፤ ነገር ግን ይህ ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምን ይበቃል?” ኢየሱስም “ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉአቸው” አለ። በዚያ ቦታ ብዙ ሣር ነበረ፤ ሰዎቹም ተቀመጡ፤ ቊጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያኽል ነበር። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንጀራውን አንሥቶ ምስጋና ካቀረበ በኋላ ለተቀመጡት ሰዎች ዐደላቸው። እንዲሁም ዓሣዎቹን አከፋፈላቸው፤ ሁሉም የሚያስፈልጋቸውን ያኽል አገኙ። ሁሉም በልተው ከጠገቡ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፥ “አንድም ነገር እንዳይባክን የተረፈውንም ፍርፋሪ ሰብስቡ” አላቸው። እነርሱም ሰዎቹ በልተው ከተረፈው ከአምስቱ የገብስ እንጀራ ፍርፋሪውን ሰብስበው በዐሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ። ሰዎቹም ኢየሱስ ያደረገውን ተአምር ባዩ ጊዜ፥ “በእርግጥ ይህ ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው!” አሉ። ሰዎቹ ግን በግድ ወስደው ሊያነግሡት እንዳሰቡ ባወቀ ጊዜ ኢየሱስ ብቻውን እንደገና ራቅ ብሎ ወደ ኮረብታ ሄደ።
ዮሐንስ 6:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ፤ እርሱም የጥብርያዶስ ባሕር ነው። በበሽተኞችም ያደረገውን ምልክቶች ስላዩ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። የአይሁድ በዓል ፋሲካም ቀርቦ ነበር። ኢየሱስም ዐይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን “እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን?” አለው። ሊፈትነው ይህን ተናገረ፤ እራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና። ፊልጶስ “እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲቀበሉ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም፤” ብሎ መለሰለት። ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ እንዲህ አለው፦ “አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን ለዚህ ሁሉ ሰው ምን ይሆናል?” ኢየሱስም “ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ፤” አለ። በዚያም ስፍራ ብዙ ሣር ነበረበት። ወንዶችም ተቀመጡ፤ ቁጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር። ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ፤ አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው፤ እንዲሁም ከዓሣው በፈለጉት መጠን። ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “አንድም እንኳን እንዳይጠፋ የተረፈውን ቁርስራሽ አከማቹ፤” አላቸው። ሰለዚህም አከማቹ፤ ከበሉትም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ። ከዚህ የተነሣ ሰዎቹ ኢየሱስ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው፤” አሉ። ኢየሱስም መጥተው በጉልበት ሊያነግሡት መሆናቸውን አውቆ በድጋሚ ወደ ተራራ ለብቻው ርቆ ሄደ።