ዮሐንስ 5:1-7
ዮሐንስ 5:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ይሉአታል፤ አምስት እርከኖችም ነበሩአት። በዚያም ዕውሮችና አንካሶች፥ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃዉን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር። የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያዉ ወርዶ ውኃዉን በሚያናውጠው ጊዜ፥ ከውኃዉ መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበርና። በዚያም ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበር። ጌታችን ኢየሱስም ያን ሰው በአልጋዉ ተኝቶ ባየ ጊዜ በደዌ ብዙ ዘመን እንደ ቈየ ዐውቆ፥ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው። ድውዩም መልሶ፥ “አዎን ጌታዬ ሆይ፥ ነገር ግን ውኃዉ በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያዉ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው።
ዮሐንስ 5:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌም፣ በበጎች በር አጠገብ፣ አምስት ባለ መጠለያ መመላለሻዎች የነበሯት፣ በአራማይክ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ የተባለች አንዲት መጠመቂያ አለች። በእነዚህም መመላለሻዎች ውስጥ ብዙ አካለ ስንኩላን፣ ዐይነ ስውሮች፣ ዐንካሶችና ሽባዎች ይተኙ ነበር። [የውሃውንም መንቀሳቀስ እየተጠባበቁ፣ ዐልፎ ዐልፎ የጌታ መልአክ ወርዶ ውሃውን በሚያናውጥበት ጊዜ፣ ቀድሞ ወደ መጠመቂያዪቱ የገባ ካደረበት ማንኛውም በሽታ ይፈወስ ነበር።] በዚያም ለሠላሳ ስምንት ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበር። ኢየሱስም ይህን ሰው ተኝቶ ባገኘው ጊዜ፣ ለብዙ ጊዜ በዚህ ሁኔታ እንደ ነበር ዐውቆ “ልትድን ትፈልጋለህን?” አለው። ሕመምተኛውም መልሶ፣ “ጌታዬ፣ ውሃው በሚናወጥበት ጊዜ ወደ መጠመቂያዪቱ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ ለመግባትም ስሞክር ሌላው ይቀድመኛል” አለው።
ዮሐንስ 5:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ፦ ልትድን ትወዳለህን? አለው። ድውዩም፦ ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።
ዮሐንስ 5:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ስለ ነበረ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ፥ በዕብራይስጥ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ የሚባል አንድ የምንጭ ኲሬ ነበረ፤ በዙሪያውም አምስት ከላይ ክዳን ያላቸው መተላለፊያዎች ነበሩ። [በጣም ብዙ በሽተኞች፥ ዕውሮች አንካሶችና ሽባዎች በመተላለፊያዎቹ ተኝተው ነበር። እነዚህ የውሃውን መንቀሳቀስ ይጠባበቁ ነበር፤ አልፎ አልፎ የጌታ መልአክ ወደ ኲሬው ወርዶ ውሃውን ያናውጥ ነበር፤ ከውሃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ ወደ ኲሬው የሚገባ ካደረበት ከማንኛውም በሽታ ይፈወስ ነበር።] በዚያም ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ የታመመ አንድ ሰው ነበረ። ኢየሱስ ይህን ሰው እዚያ ተኝቶ አየውና ከብዙ ጊዜ ጀምሮ መታመሙን ዐውቆ፥ “መዳን ትፈልጋለህን?” አለው። በሽተኛውም “ጌታ ሆይ! ውሃው በሚንቀሳቀስበት ጊዜ እኔን ወስዶ ወደ ኲሬው የሚያስገባኝ ሰው የለኝም፤ እኔ ልሄድ ስል ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው።
ዮሐንስ 5:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። በእነዚህም ውስጥ ብዙ ድኩማን፥ ዐይነ ሥውሮች፥ አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሰዎች ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውሃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውሃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ይፈወስ ይሆን ነበር። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው። ሕመምተኛውም “ጌታ ሆይ! ውሃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን እኔ በመምጣት ላይ እያለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል፤” ብሎ መለሰለት።