ዮሐንስ 4:9-14
ዮሐንስ 4:9-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ያቺ የሰማርያ ሴትም፥ “አንተ አይሁዳዊ ስትሆን፥ እኔም ሳምራዊት ስሆን እንዴት ከእኔ ዘንድ ውኃ ልትጠጣ ትለምናለህ?” አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር በሥርዐት አይተባበሩም ነበርና። ጌታችን ኢየሱስም፥ “የእግዚአብሔርን ስጦታና ውኃ አጠጪኝ ብሎ የሚለምንሽ ማን እንደ ሆነ ብታውቂስ አንቺ ደግሞ በለመንሺው ነበር፤ እርሱም የሕይወትን ውኃ በሰጠሽ ነበር” ብሎ መለሰላት። ያቺ ሴትም እንዲህ አለችው፥ “ጌታዬ መቅጃ እንኳ የለህም፤ ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ? ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ አንተ ትበልጣለህን? እርሱም ልጆቹም፥ ከብቶቹም ከእርሱ ጠጥተዋል።” ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላት፥ “ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ዳግመኛ ይጠማል። እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ግን ለዘለዓለም አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆንለታል እንጂ።”
ዮሐንስ 4:9-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሳምራዊቷም፣ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ፣ እኔን ሳምራዊቷን እንዴት ውሃ አጠጪኝ ትላለህ?” አለችው፤ ይህን ማለቷ አይሁድ ከሳምራውያን ጋራ ስለማይተባበሩ ነው። ኢየሱስም፣ “የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂና ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ፣ አንቺው በጠየቅሽው፣ እርሱም የሕይወትን ውሃ በሰጠሽ ነበር” ሲል መለሰላት። ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ መቅጃ የለህም፤ ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ ይህን የሕይወት ውሃ ከየት ታገኛለህ? ለመሆኑ አንተ፣ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን፣ ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱ ራሱና ልጆቹ፣ እንስሳቱም ከዚሁ ጕድጓድ ጠጥተዋል።” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል።”
ዮሐንስ 4:9-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ ሳምራዊቲቱ፦ አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና። ኢየሱስ መልሶ፦ የእግዚአብሔርን ስጦታና፦ ወኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት። ሴቲቱ፦ ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ? በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል አለችው። ኢየሱስም መልሶ፦ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት።
ዮሐንስ 4:9-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህችም ሳምራዊት ሴት ኢየሱስን፦ “አንተ ከአይሁድ ወገን ሆነህ እንዴት እኔን ሳምራዊቷን ‘ውሃ አጠጪኝ!’ ብለህ ትጠይቀኛለህ?” አለችው፤ ይህን ማለትዋ፥ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር ስምምነት ስላልነበራቸው ነው። ኢየሱስም “የእግዚአብሔርን ስጦታና ‘ውሃ አጠጪኝ!’ የሚልሽ ማን እንደ ሆነ ብታውቂው ኖሮ፥ እርሱን መለመን የሚገባሽ አንቺ ነበርሽ፤ እርሱም የሕይወትን ውሃ ይሰጥሽ ነበር” አላት። እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰች፤ “ጌታ ሆይ! አንተ መቅጃ የለህም፤ ጒድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ፥ የሕይወት ውሃ ከየት ታገኛለህ? አንተ ይህን ጒድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱና ልጆቹ፥ ከብቶቹም ከዚህ ጒድጓድ ጠጥተዋል።” ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማዋል፤ እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ለዘለዓለም ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ፥ ለሚጠጣው ሰው ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውሃ ምንጭ ይሆናል።”
ዮሐንስ 4:9-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ ሳምራዊቲቱ “አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ?” አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና። ኢየሱስ መልሶ “የእግዚአብሔርን ስጦታና ‘ወሃ አጠጪኝ’ የሚልሽ ማን መሆኑን ብታውቂ ኖሮ፥ አንቺ በለመንሽው ነበር፤ የሕይወትም ውሃ በሰጠሽ ነበር፤” አላት። ሴቲቱ “ጌታ ሆይ! መቅጃ የለህም፤ ጉድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውሃ ከወዴት ታገኛለህ? በእውኑ አንተ ይህን ጉድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል፤” አለችው። ኢየሱስም መልሶ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘለዓለም አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በእርሱ ውስጥ ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውሃ ምንጭ ይሆናል እንጂ፤” አላት።