የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዮሐንስ 4:43-54

ዮሐንስ 4:43-54 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከሁለቱ ቀናት በኋላም ወደ ገሊላ ሄደ፤ ነቢይ በገዛ አገሩ እንደማይከበር ኢየሱስ ራሱ ተናግሮ ነበርና። ገሊላ እንደ ደረሰም የገሊላ ሰዎች በደስታ ተቀበሉት፤ ምክንያቱም፣ እነርሱም በፋሲካ በዓል ኢየሩሳሌም ስለ ነበሩና በዚያ ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ነው። ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገበት፣ በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ቃና ከተማ ዳግመኛ መጣ፤ በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት አንድ የቤተ መንግሥት ሹም ነበረ፤ ይህም ሰው ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መምጣቱን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እርሱ ሄደና በሞት አፋፍ ላይ የነበረውን ልጁን መጥቶ እንዲፈውስለት ለመነው። ኢየሱስም፣ “መቼውንም እናንተ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን ካላያችሁ አታምኑም” አለው። ሹሙም፣ “ጌታዬ፤ ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ ድረስልኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ልጅህ በሕይወት ይኖራልና ሂድ” አለው። ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ሄደ፤ በመንገድ ላይ እንዳለም፣ አገልጋዮቹ አግኝተውት ልጁ በሕይወት መኖሩን ነገሩት። እርሱም ልጁ በስንት ሰዓት እንደ ተሻለው ሲጠይቃቸው፣ “ትኵሳቱ የለቀቀው ትናንት በሰባት ሰዓት ላይ ነው” አሉት። አባትየውም ሰዓቱ ኢየሱስ፣ “ልጅህ በሕይወት ይኖራል” ያለበት ሰዓት መሆኑን ተገነዘበ፤ እርሱና ቤተ ሰቡም ሁሉ አመኑ። ይህም፣ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ታምራዊ ምልክት ነው።

ዮሐንስ 4:43-54 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከሁ​ለት ቀንም በኋላ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ። ነቢይ በገዛ ሀገሩ እን​ደ​ማ​ይ​ከ​ብር እርሱ ራሱ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ መሰ​ከረ። ወደ ገሊ​ላም ደግሞ በገባ ጊዜ ገሊ​ላ​ው​ያን ሁሉ ተቀ​በ​ሉት፤ እነ​ርሱ ለበ​ዓል ሄደው ስለ ነበር በበ​ዓሉ ቀን በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ያደ​ረ​ገ​ውን ተአ​ምር አይ​ተው ነበ​ርና። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ውኃ​ውን የወ​ይን ጠጅ ወደ አደ​ረ​ገ​በት የገ​ሊላ ክፍል ወደ​ም​ት​ሆን ወደ ቃና ዳግ​መኛ ሄደ። በቅ​ፍ​ር​ና​ሆም ልጁ የታ​መ​መ​በት የን​ጉሥ ወገን የሆነ አንድ ሰው ነበረ፤ እር​ሱም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ከይ​ሁዳ ወደ ገሊላ እንደ መጣ በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ ሄደ፤ ሊሞት ቀርቦ ነበ​ርና ወርዶ ልጁን ያድ​ን​ለት ዘንድ ለመ​ነው፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ምል​ክ​ት​ንና ድንቅ ሥራን ካላ​ያ​ችሁ አታ​ም​ኑም” አለው። ያም የን​ጉሥ ወገን የሆነ ሰው፥ “አቤቱ፥ ልጄ ሳይ​ሞት ፈጥ​ነህ ውረድ” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ሂድ፤ ልጅ​ህስ ድኖ​አል” አለው፤ ያም ሰው፦ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ በነ​ገ​ረው ቃል አምኖ ሄደ። ሲወ​ር​ድም አገ​ል​ጋ​ዮቹ ተቀ​በ​ሉ​ትና፥ “ልጅ​ህስ ድኖ​አል” ብለው ነገ​ሩት። የዳ​ነ​ባ​ትን ሰዓ​ቷ​ንም ጠየ​ቃ​ቸው፤ “ትና​ን​ትና በሰ​ባት ሰዓት ንዳዱ ተወው” አሉት። አባ​ቱም፥ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ፥ “ልጅህ ድኖ​አል” ባለ​በት ሰዓት እንደ ሆነች ዐወቀ፤ እር​ሱም፥ ቤተ ሰቦ​ቹም ሁሉ አመኑ። ዳግ​መ​ኛም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ከይ​ሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደ​ረ​ገው ሁለ​ተ​ኛው ተአ​ምር ይህ ነው።

ዮሐንስ 4:43-54 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ። ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና። ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች ራሳቸው ደግሞ ለበዓል መጥተው ነበርና በበዓል በኢየሩሳሌም ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ተቀበሉት። ኢየሱስም ውኃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ። በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት ከንጉሥ ቤት አንድ ሹም ነበረ። እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደ መጣ ሰምቶ ልጁ ሊሞት ስላለው ወደ እርሱ ሄደ ወርዶም እንዲፈውስለት ለመነው። ስለዚህም ኢየሱስ፦ ምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም አለው። ሹሙም፦ ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ አለው። ኢየሱስም፦ ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት አለ አለው። ሰውዬውም ኢየሱስ የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ። እርሱም ሲወርድ ሳለ ባሮቹ ተገናኙትና፦ ብላቴናህ በሕይወት አለ ብለው ነገሩት። እርሱም በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው፤ እነርሱም፦ ትናንት በሰባት ሰዓት ንዳዱ ለቀቀው አሉት። አባቱም ኢየሱስ፦ ልጅህ በሕይወት አለ ባለው በዚያ ሰዓት እንደ ሆነ አወቀ፤ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር አመነ። ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛ ምልክት ነው።

ዮሐንስ 4:43-54 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ በሰማርያ ሁለት ቀን ከቈየ በኋላ ወደ ገሊላ ሄደ። እርሱ ራሱ “ነቢይ በገዛ አገሩ አይከበርም” ብሎ ተናግሮ ነበር። ነገር ግን ወደ ገሊላ በደረሰ ጊዜ የገሊላ ሰዎች በመልካም ሁኔታ ተቀበሉት፤ ይህም የሆነው ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው በነበረበት ጊዜ እርሱ በዚያ ያደረገውን ሁሉ አይተው ስለ ነበር ነው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ውሃውን የወይን ጠጅ ወደ ለወጠባት በገሊላ ምድር ወደምትገኘው ወደ ቃና ከተማ እንደገና ተመለሰ፤ በዚያን ጊዜ በቅፍርናሆም ልጁ የታመመበት አንድ የቤተ መንግሥት ሹም ነበረ። እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ምድር ወደ ገሊላ መምጣቱን ሰምቶ ወደ እርሱ ሄደ፤ ወደ ቅፍርናሆም እንዲወርድና በጠና ታሞ ሊሞት የተቃረበውን ልጁን እንዲፈውስለት ኢየሱስን ለመነው። ኢየሱስም “እናንተ ተአምራትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ በቀር ምንም አታምኑም!” አለው። ሹሙም “ጌታ ሆይ! ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ ቶሎ ውረድ” አለው። ኢየሱስም “ወደ ቤትህ ሂድ! ልጅህ በሕይወት ይኖራል” አለው። ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ወደ ቤቱ ሄደ። ሲሄድም አገልጋዮቹ በመንገድ አገኙትና “ልጅህ ድኖአል” ብለው ነገሩት። እርሱም ልጁ በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው። እነርሱም “ትናንትና በሰባት ሰዓት ላይ ትኲሳቱ ለቀቀው” አሉት። አባትየውም ኢየሱስ “ልጅህ በሕይወት ይኖራል” ያለው በዚያኑ ሰዓት እንደ ሆነ ዐወቀ፤ ስለዚህ ከዚያን ቀን ጀምሮ እርሱና ቤተ ሰቡ ሁሉ በኢየሱስ አመኑ። ይህ ተአምር ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ተአምር ነው።

ዮሐንስ 4:43-54 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ። ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና። ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች፥ እራሳቸውም ለበዓል መጥተው ነበርና፥ በበዓል በኢየሩሳሌም ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ተቀበሉት። ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ። በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት ከንጉሥ ቤት አንድ ሹም ነበረ። እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደመጣ ሰምቶ፥ ልጁ ሊሞት ስለ ቀረበ፥ ወደ እርሱ ሄደ፤ ወርዶም እንዲፈውስለት ለመነው። ስለዚህም ኢየሱስ “ምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም፤” አለው። ሹሙም “ጌታ ሆይ! ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ፤” አለው። ኢየሱስም “ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት አለ፤” አለው። ሰውዬውም ኢየሱስ የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ። እርሱም ሲወርድ ሳለ አገልጋዮቹ ተገናኙትና “ብላቴናህ በሕይወት አለ፤” ብለው ነገሩት። እርሱም በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው፤ እነርሱም “ትናንት በሰባት ሰዓት ትኩሳቱ ለቀቀው፤” አሉት። አባቱም፥ ኢየሱስ “ልጅህ በሕይወት አለ፤” ባለው በዚያ ሰዓት እንደሆነ አወቀ፤ እርሱም ከቤተ ሰቦቹ ሁሉ ጋር አመነ። ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ምልክት ነው።