ዮሐንስ 4:31-54

ዮሐንስ 4:31-54 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በዚ​ህም ጊዜ ደቀ መዛ​ሙ​ርቱ፥ “መም​ህር ሆይ፥ እህል ብላ” ብለው ለመ​ኑት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “እኔ የም​በ​ላው እና​ንተ የማ​ታ​ው​ቁት ምግብ አለኝ” አላ​ቸው። ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም እርስ በር​ሳ​ቸው፥ “አን​ዳች የሚ​በ​ላው ምግብ ያመ​ጣ​ለት ሰው ይኖር ይሆን?” ተባ​ባሉ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “የእ​ኔስ መብል የላ​ከ​ኝን የአ​ባ​ቴን ፈቃድ አደ​ርግ ዘንድ፥ ሥራ​ው​ንም እፈ​ጽም ዘንድ ነው። እና​ንተ እስከ አራት ወር ድረስ መከር ይሆ​ናል የም​ትሉ አይ​ደ​ለ​ምን? እነሆ፥ እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ ዐይ​ና​ች​ሁን አንሡ፤ መከ​ሩም ሊደ​ርስ እንደ ገረጣ ምድ​ሩን ተመ​ል​ከቱ። አጫ​ጅም ዋጋ​ውን ያገ​ኛል፤ የሚ​ዘ​ራና የሚ​ያ​ጭ​ድም በአ​ን​ድ​ነት ደስ እን​ዲ​ላ​ቸው ለዘ​ለ​ዓ​ለም ሕይ​ወት ፍሬን ይሰ​በ​ስ​ባል። አንዱ ይዘ​ራል፥ ሌላ​ውም ያጭ​ዳል የሚ​ለው ቃል በዚህ እው​ነት ሆኖ​አል። እኔም ያል​ደ​ከ​ማ​ች​ሁ​በ​ትን እን​ድ​ታ​ጭዱ ላክ​ኋ​ችሁ፤ ሌሎች ደከሙ፤ እና​ን​ተም በድ​ካ​ማ​ቸው ገባ​ችሁ።” “የሠ​ራ​ሁ​ትን ሁሉ ነገ​ረኝ” ብላ የመ​ሰ​ከ​ረ​ችው ሴት ስለ ነገ​ረ​ቻ​ቸ​ውም ከዚ​ያች ከሰ​ማ​ርያ ከተማ ብዙ​ዎች አመ​ኑ​በት። ሳም​ራ​ው​ያ​ንም ሁሉ ወደ እርሱ መጥ​ተው በእ​ነ​ርሱ ዘንድ እን​ዲ​ኖር ማለ​ዱት፤ ሁለት ቀንም ያህል በዚያ ተቀ​መጠ። ስለ ቃሉም እጅግ ብዙ​ዎች አመ​ኑ​በት። ሴቲ​ቱ​ንም፥ “እኛ ራሳ​ችን ይህ በእ​ው​ነት የዓ​ለም መድ​ኀ​ኒት ክር​ስ​ቶስ እንደ ሆነ ሰም​ተ​ንና ተረ​ድ​ተን ነው እንጂ በአ​ንቺ ቃል ያመ​ን​በት አይ​ደ​ለም” አሏት። ከሁ​ለት ቀንም በኋላ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ። ነቢይ በገዛ ሀገሩ እን​ደ​ማ​ይ​ከ​ብር እርሱ ራሱ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ መሰ​ከረ። ወደ ገሊ​ላም ደግሞ በገባ ጊዜ ገሊ​ላ​ው​ያን ሁሉ ተቀ​በ​ሉት፤ እነ​ርሱ ለበ​ዓል ሄደው ስለ ነበር በበ​ዓሉ ቀን በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ያደ​ረ​ገ​ውን ተአ​ምር አይ​ተው ነበ​ርና። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ውኃ​ውን የወ​ይን ጠጅ ወደ አደ​ረ​ገ​በት የገ​ሊላ ክፍል ወደ​ም​ት​ሆን ወደ ቃና ዳግ​መኛ ሄደ። በቅ​ፍ​ር​ና​ሆም ልጁ የታ​መ​መ​በት የን​ጉሥ ወገን የሆነ አንድ ሰው ነበረ፤ እር​ሱም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ከይ​ሁዳ ወደ ገሊላ እንደ መጣ በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ ሄደ፤ ሊሞት ቀርቦ ነበ​ርና ወርዶ ልጁን ያድ​ን​ለት ዘንድ ለመ​ነው፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ምል​ክ​ት​ንና ድንቅ ሥራን ካላ​ያ​ችሁ አታ​ም​ኑም” አለው። ያም የን​ጉሥ ወገን የሆነ ሰው፥ “አቤቱ፥ ልጄ ሳይ​ሞት ፈጥ​ነህ ውረድ” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ሂድ፤ ልጅ​ህስ ድኖ​አል” አለው፤ ያም ሰው፦ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ በነ​ገ​ረው ቃል አምኖ ሄደ። ሲወ​ር​ድም አገ​ል​ጋ​ዮቹ ተቀ​በ​ሉ​ትና፥ “ልጅ​ህስ ድኖ​አል” ብለው ነገ​ሩት። የዳ​ነ​ባ​ትን ሰዓ​ቷ​ንም ጠየ​ቃ​ቸው፤ “ትና​ን​ትና በሰ​ባት ሰዓት ንዳዱ ተወው” አሉት። አባ​ቱም፥ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ፥ “ልጅህ ድኖ​አል” ባለ​በት ሰዓት እንደ ሆነች ዐወቀ፤ እር​ሱም፥ ቤተ ሰቦ​ቹም ሁሉ አመኑ። ዳግ​መ​ኛም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ከይ​ሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደ​ረ​ገው ሁለ​ተ​ኛው ተአ​ምር ይህ ነው።

ዮሐንስ 4:31-54 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፣ “ረቢ፣ እህል ቅመስ እንጂ” አሉት። እርሱ ግን፣ “እናንተ የማታውቁት፣ የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሰው ምግብ አምጥቶለት ይሆን እንዴ?” ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው፤ እናንተ፣ ‘ከአራት ወር በኋላ መከር ይደርሳል’ ትሉ የለምን? እነሆ፣ አዝመራው ለመከር እንደ ደረሰ ቀና ብላችሁ ማሳውን ተመልከቱ እላችኋለሁ። ዐጫጁ አሁንም ቢሆን እንኳ ደመወዙን እየተቀበለ ነው፤ ለዘላለም ሕይወት ይሆን ዘንድ አዝመራውን ይሰበስባል፤ ይህም ዘሪውና ዐጫጁ በጋራ ደስ እንዲላቸው ነው። ስለዚህ፣ ‘አንዱ ይዘራል፤ ሌላውም ያጭዳል’ የተባለው ምሳሌ እውነት ነው። ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ አድካሚውን ሥራ ሌሎች ሠሩ፤ እናንተም የድካማቸውን ፍሬ ሰበሰባችሁ።” ሴቲቱም፣ “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ” ብላ ስለ መሰከረች፣ ከዚያች ከተማ ብዙ ሳምራውያን በርሱ አመኑ። ስለዚህ፣ ሳምራውያኑ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ ዐብሯቸው እንዲቈይ አጥብቀው ለመኑት፤ እዚያም ሁለት ቀን ቈየ። ከቃሉም የተነሣ ሌሎች ብዙዎች አመኑ። ሴትዮዋንም፣ “ከእንግዲህ የምናምነው አንቺ ስለ ነገርሽን ብቻ አይደለም፤ እኛ ራሳችን ሰምተነዋል፤ ይህ ሰው በእውነት የዓለም አዳኝ እንደ ሆነ እናውቃለን” አሏት። ከሁለቱ ቀናት በኋላም ወደ ገሊላ ሄደ፤ ነቢይ በገዛ አገሩ እንደማይከበር ኢየሱስ ራሱ ተናግሮ ነበርና። ገሊላ እንደ ደረሰም የገሊላ ሰዎች በደስታ ተቀበሉት፤ ምክንያቱም፣ እነርሱም በፋሲካ በዓል ኢየሩሳሌም ስለ ነበሩና በዚያ ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ነው። ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገበት፣ በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ቃና ከተማ ዳግመኛ መጣ፤ በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት አንድ የቤተ መንግሥት ሹም ነበረ፤ ይህም ሰው ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መምጣቱን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እርሱ ሄደና በሞት አፋፍ ላይ የነበረውን ልጁን መጥቶ እንዲፈውስለት ለመነው። ኢየሱስም፣ “መቼውንም እናንተ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን ካላያችሁ አታምኑም” አለው። ሹሙም፣ “ጌታዬ፤ ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ ድረስልኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ልጅህ በሕይወት ይኖራልና ሂድ” አለው። ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ሄደ፤ በመንገድ ላይ እንዳለም፣ ባሮቹ አግኝተውት ልጁ በሕይወት መኖሩን ነገሩት። እርሱም ልጁ በስንት ሰዓት እንደ ተሻለው ሲጠይቃቸው፣ “ትኵሳቱ የለቀቀው ትናንት በሰባት ሰዓት ላይ ነው” አሉት። አባትየውም ሰዓቱ ኢየሱስ፣ “ልጅህ በሕይወት ይኖራል” ያለበት ሰዓት መሆኑን ተገነዘበ፤ እርሱና ቤተ ሰቡም ሁሉ አመኑ። ይህም፣ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ታምራዊ ምልክት ነው።

ዮሐንስ 4:31-54 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ይህም ሲሆን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ፦ መምህር ሆይ፥ ብላ ብለው ለመኑት። እርሱ ግን፦ እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ፦ የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን? ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው። እናንተ፦ ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፥ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ። የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፥ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል። አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአልና። እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ። ሴቲቱም፦ ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ ብላ ስለ መሰከረችው ቃል ከዚያች ከተማ የሰማርያ ሰዎች ብዙ አመኑበት። የሰማርያ ሰዎችም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፤ በዚያም ሁለት ቀን ያህል ኖረ። ስለ ቃሉ ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ፤ ሴቲቱንም፦ አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር። ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ። ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና። ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች ራሳቸው ደግሞ ለበዓል መጥተው ነበርና በበዓል በኢየሩሳሌም ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ተቀበሉት። ኢየሱስም ውኃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ። በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት ከንጉሥ ቤት አንድ ሹም ነበረ። እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደ መጣ ሰምቶ ልጁ ሊሞት ስላለው ወደ እርሱ ሄደ ወርዶም እንዲፈውስለት ለመነው። ስለዚህም ኢየሱስ፦ ምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም አለው። ሹሙም፦ ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ አለው። ኢየሱስም፦ ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት አለ አለው። ሰውዬውም ኢየሱስ የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ። እርሱም ሲወርድ ሳለ ባሮቹ ተገናኙትና፦ ብላቴናህ በሕይወት አለ ብለው ነገሩት። እርሱም በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው፤ እነርሱም፦ ትናንት በሰባት ሰዓት ንዳዱ ለቀቀው አሉት። አባቱም ኢየሱስ፦ ልጅህ በሕይወት አለ ባለው በዚያ ሰዓት እንደ ሆነ አወቀ፤ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር አመነ። ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛ ምልክት ነው።

ዮሐንስ 4:31-54 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን፦ “መምህር ሆይ! አንዳች ምግብ ብላ” ሲሉ ለመኑት። እርሱ ግን፥ “እናንተ የማታውቁት እኔ የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ፥ “አንዳች ሰው ምግብ አምጥቶለት ይሆን?” ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውንም መፈጸም ነው። እናንተ ‘ገና አራት ወር ቀርቶታል፤ ከዚያም በኋላ መከር ይሆናል’ ትሉ የለምን? እኔ ግን ‘ቀና በሉና እርሻዎቹ ለመከር እንደ ደረሱ ተመልከቱ’ እላችኋለሁ። የሚያጭድ ደመወዙን ይቀበላል፤ ለዘለዓለም ሕይወት የሚሆን ፍሬም ይሰበስባል፤ ስለዚህ የሚዘራውም፥ የሚያጭደውም አብረው ይደሰታሉ። በዚህም ምክንያት ‘አንዱ ይዘራል፥ ሌላው ያጭዳል’ የተባለው አባባል እውነት ነው። እኔም ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ ሌሎች በሥራ ደከሙ፤ እናንተ ግን በድካማቸው ፍሬ ተጠቀማችሁ።” ሴትዮዋ “የሠራሁትን ነገር ሁሉ ነገረኝ” ብላ በመሰከረችው መሠረት ከዚያ ከተማ ብዙዎቹ የሰማርያ ሰዎች አመኑ። ስለዚህ የሰማርያ አገር ሰዎች ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ከእነርሱ ጋር እንዲቈይ ለመኑት፤ እርሱም ሁለት ቀን እዚያ ቈየ። በቃሉም ምክንያት ሌሎች ብዙ ሰዎችም በእርሱ አመኑ። ሴትዮዋንም “ከእንግዲህ ወዲህ እርሱን የምናምነው አንቺ በነገርሽን ቃል ብቻ ሳይሆን እኛ ራሳችን ስለ ሰማንና በእርግጥ እርሱ የዓለም አዳኝ እንደ ሆነ ስላወቅን ነው” አሉአት። ኢየሱስ በሰማርያ ሁለት ቀን ከቈየ በኋላ ወደ ገሊላ ሄደ። እርሱ ራሱ “ነቢይ በገዛ አገሩ አይከበርም” ብሎ ተናግሮ ነበር። ነገር ግን ወደ ገሊላ በደረሰ ጊዜ የገሊላ ሰዎች በመልካም ሁኔታ ተቀበሉት፤ ይህም የሆነው ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው በነበረበት ጊዜ እርሱ በዚያ ያደረገውን ሁሉ አይተው ስለ ነበር ነው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ውሃውን የወይን ጠጅ ወደ ለወጠባት በገሊላ ምድር ወደምትገኘው ወደ ቃና ከተማ እንደገና ተመለሰ፤ በዚያን ጊዜ በቅፍርናሆም ልጁ የታመመበት አንድ የቤተ መንግሥት ሹም ነበረ። እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ምድር ወደ ገሊላ መምጣቱን ሰምቶ ወደ እርሱ ሄደ፤ ወደ ቅፍርናሆም እንዲወርድና በጠና ታሞ ሊሞት የተቃረበውን ልጁን እንዲፈውስለት ኢየሱስን ለመነው። ኢየሱስም “እናንተ ተአምራትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ በቀር ምንም አታምኑም!” አለው። ሹሙም “ጌታ ሆይ! ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ ቶሎ ውረድ” አለው። ኢየሱስም “ወደ ቤትህ ሂድ! ልጅህ በሕይወት ይኖራል” አለው። ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ወደ ቤቱ ሄደ። ሲሄድም አገልጋዮቹ በመንገድ አገኙትና “ልጅህ ድኖአል” ብለው ነገሩት። እርሱም ልጁ በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው። እነርሱም “ትናንትና በሰባት ሰዓት ላይ ትኲሳቱ ለቀቀው” አሉት። አባትየውም ኢየሱስ “ልጅህ በሕይወት ይኖራል” ያለው በዚያኑ ሰዓት እንደ ሆነ ዐወቀ፤ ስለዚህ ከዚያን ቀን ጀምሮ እርሱና ቤተ ሰቡ ሁሉ በኢየሱስ አመኑ። ይህ ተአምር ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ተአምር ነው።

ዮሐንስ 4:31-54 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ይህም ሲሆን ሳለ ደቀመዛሙርቱ “መምህር ሆይ! ብላ፤” ብለው ለመኑት። እርሱ ግን “እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ፤” አላቸው። ስለዚህ ደቀመዛሙርቱ “የሚበላው አንዳች ምግብ ሰው አምጥቶለት ይሆንን?” ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ ማድረግ፥ ሥራውንም መፈጸም ነው። እናንተ ‘ገና አራት ወር ቀርቶአል፤ ከዚያም መከር ይመጣል፤’ ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፤ ዐይናችሁን አንሡ፤ እርሻው ከወዲሁ ለአዝመራ እንዴት እንደ ደረሰ ተመልከቱ። የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፤ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘለዓለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል። ‘አንዱ ይዘራል፤ አንዱም ያጭዳል፤’ የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአልና። እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ፤ እናንተም እነርሱ በደከሙበት ገባችሁ።” ሴቲቱም “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ፤” ብላ በመሰከረችው ቃል መሠረት፥ ከዚያች ከተማ፥ ብዙ የሰማርያ ሰዎች በእርሱ አመኑ። የሰማርያ ሰዎችም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፤ በዚያም ለሁለት ቀን ያህል ቆየ። በቃሉ ምክንያት ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ፤ ሴቲቱንም “አሁን የምናምነው በቃልሽ ምክንያት አይደለም፤ እኛ እራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱ በእውነት የዓለም መድኃኒት እንደሆነ እናውቃለን፤” ይሉአት ነበር። ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ። ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና። ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች፥ እራሳቸውም ለበዓል መጥተው ነበርና፥ በበዓል በኢየሩሳሌም ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ተቀበሉት። ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ። በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት ከንጉሥ ቤት አንድ ሹም ነበረ። እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደመጣ ሰምቶ፥ ልጁ ሊሞት ስለ ቀረበ፥ ወደ እርሱ ሄደ፤ ወርዶም እንዲፈውስለት ለመነው። ስለዚህም ኢየሱስ “ምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም፤” አለው። ሹሙም “ጌታ ሆይ! ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ፤” አለው። ኢየሱስም “ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት አለ፤” አለው። ሰውዬውም ኢየሱስ የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ። እርሱም ሲወርድ ሳለ አገልጋዮቹ ተገናኙትና “ብላቴናህ በሕይወት አለ፤” ብለው ነገሩት። እርሱም በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው፤ እነርሱም “ትናንት በሰባት ሰዓት ትኩሳቱ ለቀቀው፤” አሉት። አባቱም፥ ኢየሱስ “ልጅህ በሕይወት አለ፤” ባለው በዚያ ሰዓት እንደሆነ አወቀ፤ እርሱም ከቤተ ሰቦቹ ሁሉ ጋር አመነ። ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ምልክት ነው።