ዮሐንስ 4:31-38
ዮሐንስ 4:31-38 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይህም ሲሆን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ፦ መምህር ሆይ፥ ብላ ብለው ለመኑት። እርሱ ግን፦ እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ፦ የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን? ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው። እናንተ፦ ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፥ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ። የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፥ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል። አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአልና። እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ።
ዮሐንስ 4:31-38 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚህም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፥ “መምህር ሆይ፥ እህል ብላ” ብለው ለመኑት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ የምበላው እናንተ የማታውቁት ምግብ አለኝ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም እርስ በርሳቸው፥ “አንዳች የሚበላው ምግብ ያመጣለት ሰው ይኖር ይሆን?” ተባባሉ። ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “የእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፥ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው። እናንተ እስከ አራት ወር ድረስ መከር ይሆናል የምትሉ አይደለምን? እነሆ፥ እላችኋለሁ፤ ዐይናችሁን አንሡ፤ መከሩም ሊደርስ እንደ ገረጣ ምድሩን ተመልከቱ። አጫጅም ዋጋውን ያገኛል፤ የሚዘራና የሚያጭድም በአንድነት ደስ እንዲላቸው ለዘለዓለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል። አንዱ ይዘራል፥ ሌላውም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአል። እኔም ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ፤ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ።”
ዮሐንስ 4:31-38 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፣ “ረቢ፣ እህል ቅመስ እንጂ” አሉት። እርሱ ግን፣ “እናንተ የማታውቁት፣ የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሰው ምግብ አምጥቶለት ይሆን እንዴ?” ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው፤ እናንተ፣ ‘ከአራት ወር በኋላ መከር ይደርሳል’ ትሉ የለምን? እነሆ፣ አዝመራው ለመከር እንደ ደረሰ ቀና ብላችሁ ማሳውን ተመልከቱ እላችኋለሁ። ዐጫጁ አሁንም ቢሆን እንኳ ደመወዙን እየተቀበለ ነው፤ ለዘላለም ሕይወት ይሆን ዘንድ አዝመራውን ይሰበስባል፤ ይህም ዘሪውና ዐጫጁ በጋራ ደስ እንዲላቸው ነው። ስለዚህ፣ ‘አንዱ ይዘራል፤ ሌላውም ያጭዳል’ የተባለው ምሳሌ እውነት ነው። ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ አድካሚውን ሥራ ሌሎች ሠሩ፤ እናንተም የድካማቸውን ፍሬ ሰበሰባችሁ።”
ዮሐንስ 4:31-38 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን፦ “መምህር ሆይ! አንዳች ምግብ ብላ” ሲሉ ለመኑት። እርሱ ግን፥ “እናንተ የማታውቁት እኔ የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ፥ “አንዳች ሰው ምግብ አምጥቶለት ይሆን?” ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውንም መፈጸም ነው። እናንተ ‘ገና አራት ወር ቀርቶታል፤ ከዚያም በኋላ መከር ይሆናል’ ትሉ የለምን? እኔ ግን ‘ቀና በሉና እርሻዎቹ ለመከር እንደ ደረሱ ተመልከቱ’ እላችኋለሁ። የሚያጭድ ደመወዙን ይቀበላል፤ ለዘለዓለም ሕይወት የሚሆን ፍሬም ይሰበስባል፤ ስለዚህ የሚዘራውም፥ የሚያጭደውም አብረው ይደሰታሉ። በዚህም ምክንያት ‘አንዱ ይዘራል፥ ሌላው ያጭዳል’ የተባለው አባባል እውነት ነው። እኔም ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ ሌሎች በሥራ ደከሙ፤ እናንተ ግን በድካማቸው ፍሬ ተጠቀማችሁ።”
ዮሐንስ 4:31-38 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህም ሲሆን ሳለ ደቀመዛሙርቱ “መምህር ሆይ! ብላ፤” ብለው ለመኑት። እርሱ ግን “እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ፤” አላቸው። ስለዚህ ደቀመዛሙርቱ “የሚበላው አንዳች ምግብ ሰው አምጥቶለት ይሆንን?” ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ ማድረግ፥ ሥራውንም መፈጸም ነው። እናንተ ‘ገና አራት ወር ቀርቶአል፤ ከዚያም መከር ይመጣል፤’ ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፤ ዐይናችሁን አንሡ፤ እርሻው ከወዲሁ ለአዝመራ እንዴት እንደ ደረሰ ተመልከቱ። የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፤ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘለዓለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል። ‘አንዱ ይዘራል፤ አንዱም ያጭዳል፤’ የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአልና። እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ፤ እናንተም እነርሱ በደከሙበት ገባችሁ።”