ዮሐንስ 4:3-7
ዮሐንስ 4:3-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የይሁዳንም ምድር ትቶ ዳግመኛ ወደ ገሊላ ሄደ። በሰማርያ በኩልም ሲያልፍ ሳለ፥ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው በወይን ቦታ አቅራቢያ ወደ አለችው ሲካር ወደምትባለው የሰማርያ ከተማ ደረሰ። በዚያም የያዕቆብ የውኃ ጕድጓድ ነበረ። ጌታችን ኢየሱስም መንገድ በመሄድ ደክሞ በዚያ ጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበር። እነሆ፥ ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “ውኃ አጠጪኝ” አላት።
ዮሐንስ 4:3-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጌታም ይህን እንዳወቀ ይሁዳን ለቅቆ ወደ ገሊላ ተመልሶ ሄደ። በሰማርያም በኩል ማለፍ ነበረበት። ስለዚህ በሰማርያ፣ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ቦታ አጠገብ ወደ ነበረች፣ ሲካር ወደምትባል ከተማ መጣ። በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጕድጓድ ነበረ፤ ኢየሱስም ከጕዞው የተነሣ ደክሞት ስለ ነበር በውሃው ጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ነበር። አንዲት ሳምራዊት ሴት ውሃ ለመቅዳት ስትመጣ ኢየሱስ፣ “እባክሽ የምጠጣው ስጪኝ” አላት፤
ዮሐንስ 4:2-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይሁዳን ትቶ ወደ ገሊላ ደግሞ ሄደ፤ ዳሩ ግን ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም። በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት። ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትሆን ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤ በዚያም የያዕቆብ ጕድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጕድጓድ አጠገብ እንዲህ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ። ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም፦ ውኃ አጠጪኝ አላት፤
ዮሐንስ 4:3-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለ እርሱ የተባለውን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ባወቀ ጊዜ ኢየሱስ የይሁዳን ምድር ትቶ ወደ ገሊላ ተመልሶ ሄደ። ወደዚያም ሲሄድ በሰማርያ በኩል ማለፍ ነበረበት። ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ቦታ አጠገብ ወደምትገኝ፥ ሲካር ተብላ ወደምትጠራ የሰማርያ ከተማ መጣ። በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጒድጓድ ነበረ፤ ኢየሱስ መንገድ ከመሄድ የተነሣ ስለ ደከመው በጒድጓዱ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ወደ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበረ። በዚያን ጊዜ አንዲት የሰማርያ አገር ሴት ውሃ ልትቀዳ ወደ ጒድጓዱ መጣች፤ ኢየሱስም “ውሃ አጠጪኝ!” አላት።
ዮሐንስ 4:3-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የይሁዳን ምድር ትቶ ወደ ገሊላ እንደገና ሄደ። በሰማርያም ማለፍ ግድ ሆነበት። ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትገኝ ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤ በዚያም የያዕቆብ ጉድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ። አንዲት የሰማርያ ሴት ውሃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም “ውሃ አጠጪኝ” አላት፤