ዮሐንስ 2:13-16
ዮሐንስ 2:13-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የአይሁድም የፋሲካቸው በዓል ቀርቦ ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በቤተ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን፥ ርግቦችንም የሚሸጡትን፥ ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ። የገመድም ጅራፍ አበጀ፤ በጎችንና በሬዎችን፥ ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣ፤ የለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ። ርግብ ሻጮችንም፥ “ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” አላቸው።
ዮሐንስ 2:13-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የአይሁድ ፋሲካም እንደ ተቃረበ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በቤተ መቅደሱ አደባባይ ከብቶችን፣ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡ እንዲሁም ተቀምጠው የገንዘብ ምንዛሪ የሚያከናውኑ ሰዎች አገኘ። የገመድ ጅራፍ አበጅቶ በጎችንና ከብቶችን ሁሉ ከቤተ መቅደሱ ግቢ አባረረ፤ የመንዛሪዎችን ገንዘብ በተነ፤ ጠረጴዞቻቸውንም ገለበጠ። ርግብ ሻጮችንም፣ “እነዚህን ከዚህ አስወጧቸው፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት!” አላቸው።
ዮሐንስ 2:13-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በመቅደስም በሬዎችንም በጎችን ግንቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፥ ርግብ ሻጪዎችንም፦ ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው።
ዮሐንስ 2:13-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የአይሁድ ፋሲካ በዓል ቀርቦ ስለ ነበር ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ በቤተ መቅደስም በሬዎችን፥ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡትንና ገንዘብ ለዋጮችን ተቀምጠው ሲገበያዩ አገኘ። በዚህ ጊዜ የገመድ ጅራፍ አበጀና ሰዎችን ሁሉ፥ ከበጎችና ከበሬዎች ጋር ከቤተ መቅደስ አስወጣቸው፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ጠረጴዛዎቻቸውንም ገለባበጠ። ርግብ የሚሸጡትንም ሰዎች “ይህን ሁሉ ወዲያ ውሰዱ! የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት!” አላቸው።