ዮሐንስ 19:5-16
ዮሐንስ 19:5-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታችን ኢየሱስም የእሾህ አክሊል ደፍቶ፥ የቀይ ሐር መጐናጸፊያም ለብሶ ወደ ውጭ ወጣ፤ ጲላጦስም፥ “እነሆ፥ ሰውዬው” አላቸው። ሊቃነ ካህናትና ሎሌዎቻቸውም ባዩት ጊዜ፥ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮሁ፤ ጲላጦስም፥ “እናንተ ራሳችሁ ውሰዱና ስቀሉት፤ እኔስ በእርሱ ላይ በደል አላገኘሁበትም” አላቸው። አይሁድም መልሰው፥ “እኛ ሕግ አለን፤ እንደ ሕጋችንም ሊሞት ይገባል፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና” አሉት። ጲላጦስም ይህን ነገር ሰምቶ እጅግ ፈራ። ደግሞም ወደ ፍርድ አደባባይ ገባና ጌታችን ኢየሱስን፥ “አንተ ከወዴት ነህ?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም። ጲላጦስም፥ “ለእኔም አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንደ አለኝ፥ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ፥ አታውቅምን?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ከሰማይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ አንዳች ሥልጣን የለህም፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው ታላቅ ኀጢኣት አለበት” አለው። ስለዚህም ጲላጦስ ሊፈታው ወድዶ ነበር፤ አይሁድ ግን፥ “ይህን ከፈታኸው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሰው ሁሉ በቄሣር ላይ የሚያምፅ ነውና” ብለው ጮሁ። ጲላጦስም ይህን ሰምቶ ጌታችን ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፤ በዕብራይስጥም ገበታ ተብሎ በሚጠራው “ጸፍጸፍ” በሚሉት ቦታ ላይ በወንበር ተቀመጠ። የፋሲካም የመዘጋጀት ቀን ነበር፤ ጊዜዉም ስድስት ሰዓት ያህል ነበር፤ ጲላጦስም አይሁድን፥ “እነሆ፥ ንጉሣችሁ” አላቸው፤ እነርሱ ግን፥ “አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮሁ። ጲላጦስም፥ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አላቸው፤ ሊቃነ ካህናቱም፥ “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱ። ከዚህ በኋላ ሊሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ጌታችን ኢየሱስንም ተቀብለው ወሰዱት።
ዮሐንስ 19:5-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ የእሾኽ አክሊል ደፍቶ ሐምራዊ ልብስም ለብሶ ወጣ፤ ጲላጦስም፣ “እነሆ፤ ሰውየው!” አላቸው። የካህናት አለቆችና አገልጋዮቻቸውም ባዩት ጊዜ፣ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስ ግን፣ “እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት፤ በእኔ በኩል ለክስ የሚያደርስ ወንጀል አላገኘሁበትም” አላቸው። አይሁድም፣ “እኛ ሕግ አለን፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ስላደረገ በሕጋችን መሠረት መሞት አለበት” አሉ። ጲላጦስ ይህን ሲሰማ የባሰውኑ ፈራ፤ ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን፣ “ከየት ነው የመጣኸው?” በማለት ጠየቀው፤ ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም። ጲላጦስም፣ “አታናግረኝምን? ልፈታህ ወይም ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅም?” አለው። ኢየሱስም፣ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው የባሰ ኀጢአት አለበት” አለው። ከዚያ በኋላ ጲላጦስ ኢየሱስን ሊፈታው ፈለገ፤ አይሁድ ግን፣ “ይህን ሰው ብትፈታው የቄሳር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ የቄሳር ተቃዋሚ ነው” በማለት ጩኸታቸውን ቀጠሉ። ጲላጦስም ይህን ሲሰማ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፤ “የድንጋይ ንጣፍ” በተባለ፣ በአራማይክ ቋንቋ “ገበታ” ብለው በሚጠሩት ስፍራ፣ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠ። ቀኑ የፋሲካ በዓል መዘጋጃ፣ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ያህል ነበር። ጲላጦስም አይሁድን፣ “እነሆ፤ ንጉሣችሁ” አላቸው። እነርሱ ግን፣ “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፣ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አለ። የካህናት አለቆችም፣ “ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱለት። በመጨረሻም ጲላጦስ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው።
ዮሐንስ 19:5-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም የእሾህ አክሊል ደፍቶ ቀይ ልብስም ለብሶ ወደ ውጭ ወጣ። ጲላጦስም፦ “እነሆ ሰውዬው” አላቸው። የካህናት አለቆችና ሎሌዎች ባዩትም ጊዜ፦ “ስቀለው ስቀለው” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፦ “እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትምና እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት” አላቸው። አይሁድም መልሰው፦ “እኛ ሕግ አለን፥ እንደ ሕጋችንም ሊሞት ይገባዋል፥ ራሱን የእግዚአብሔርን ልጅ አድርጎአልና” አሉት። ስለዚህ ጲላጦስ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እግጅ ፈራ፤ ተመልሶም ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን፦ “አንተ ከወዴት ነህ?” አለው። ኢየሱስ ግን አንድ እንኳ አልመለሰለትም። ስለዚህ ጲላጦስ፦ “አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ “ከላይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልነበረህም፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ኃጢአቱ የባሰ ነው።” አለው። ከዚህ በኋላ ጲላጦስ ሊፈታው ፈለገ፤ ነገር ግን አይሁድ፦ “ይህንስ ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የቄሣር ተቃዋሚ ነው” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም ይህን ነገር ሰምቶ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፥ በዕብራይስጥም ገብታ በተባለው ጸፍጸፍ በሚሉት ስፍራ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ። ለፋሲካም የማዘጋጀት ቀን ነበረ፤ ስድስት ሰዓትም የሚያህል ነበረ፤ አይሁድንም፦ “እነሆ ንጉሣችሁ” አላቸው። እነርሱ ግን፦ “አስወግደው፥ አስወግደው፥ ስቀለው” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፦ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አላቸው። የካህናት አለቆችም፦ “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱለት ስለዚህ በዚህን ጊዜ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው።
ዮሐንስ 19:5-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ ኢየሱስ የእሾኽ አክሊል ደፍቶና ቀይ ልብስ ለብሶ ወደ ውጪ ወጣ፤ ጲላጦስም “እነሆ፥ ሰውየው!” አላቸው። የካህናት አለቆችና የዘብ ኀላፊዎች ኢየሱስን ባዩት ጊዜ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስ ግን “እኔ በበኩሌ ምንም በደል አላገኘሁበትም፤ ብትፈልጉ እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት” አላቸው። አይሁድም “እኛ ሕግ አለን፤ ይህ ሰው ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ስላደረገ በሕጋችን መሠረት መሞት ይገባዋል” አሉ። ይህን ሁሉ ነገር በሰማ ጊዜ ጲላጦስ በይበልጥ ፈራ፤ ወደ ግቢው ገባና ኢየሱስን “አንተ ከየት ነህ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም። ስለዚህ ጲላጦስ “አትነግረኝምን? እኔ ልፈታህ ወይም ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን?” አለው፤ ኢየሱስም “ከእግዚአብሔር ሥልጣን ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ሆኖም ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ የባሰ ኃጢአት አለበት” አለው። ጲላጦስ ይህን የኢየሱስን አነጋገር በሰማ ጊዜ ፈቶ ሊለቀው ፈልጎ ነበር፤ አይሁድ ግን “ይህን ሰው ከፈታኸው አንተ የሮም ንጉሠ ነገሥት ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የንጉሠ ነገሥቱ ጠላት ነው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስ ይህን በሰማ ጊዜ ኢየሱስን ወደ ውጪ አውጥቶ “ጠፍጣፋ ድንጋይ” በተባለው ስፍራ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ፤ ይህ ስፍራ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ገበታ” ይባላል። የፋሲካ በዓል የዝግጅት ቀን ነበረ፤ ጊዜውም ወደ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበረ፤ በዚያን ጊዜ ጲላጦስ አይሁድን “እነሆ ንጉሣችሁ!” አላቸው። እነርሱ ግን “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አላቸው። የካህናት አለቆችም “ከሮማው ንጉሠ ነገሥት በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም!” ሲሉ መለሱለት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲሰቀል ጲላጦስ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት።
ዮሐንስ 19:5-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም የእሾህ አክሊል ደፍቶ፥ ቀይ ልብስም ለብሶ፥ ወደ ውጭ ወጣ። ጲላጦስም “እነሆ ሰውዬው፤” አላቸው። የካህናት አለቆችና ሎሌዎችም ባዩት ጊዜ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “እኔስ አንዲት በደል እንኳን አላገኘሁበትምና እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት” አላቸው። አይሁድም መልሰው “እኛ ሕግ አለን፤ በሕጋችን መሠረት ሊሞት ይገባዋል፤ ራሱን የእግዚአብሔርን ልጅ አድርጎአልና” አሉት። ጲላጦስም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እግጅ ፈራ፤ ተመልሶም ወደ ገዢው ግቢ ገባና ኢየሱስን “አንተ ከየት ነህ?” አለው። ኢየሱስ ግን ምንም መልስ አልሰጠውም። ስለዚህም ጲላጦስ “አታናግረኝምን? ልፈታህም ሆነ ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው ኀጢአቱ የባሰ ነው” አለው። ከዚህ በኋላ ጲላጦስ ሊፈታው ፈለገ፤ ነገር ግን አይሁድ “ይህን ሰው ከፈታኸው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የቄሣር ተቃዋሚ ነው” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም ይህን ነገር ሰምቶ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፤ በዕብራይስጥም ገበታ በተባለው “ጠፍጣፋ ድንጋይ” በሚሉት ስፍራ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ። የፋሲካም በዓል የሚዘጋጅበት ቀን ነበረ፤ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበረ፤ አይሁድንም “እነሆ ንጉሣችሁ!” አላቸው። እነርሱ ግን “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አላቸው። የካህናት አለቆችም “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱለት እንግዲህ በዚህ ጊዜ ነው እንዲሰቀል አሳልፎ የሰጣቸው።