የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዮሐንስ 18:15-27

ዮሐንስ 18:15-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ስም​ዖን ጴጥ​ሮ​ስና ሌላው ደቀ መዝ​ሙ​ርም ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን ከሩቅ ተከ​ተ​ሉት፤ ያ ደቀ መዝ​ሙር ግን በሊቀ ካህ​ናቱ ዘንድ የታ​ወቀ ነበር፤ ከጌ​ታ​ችን ኢየ​ሱስ ጋርም ወደ ሊቀ ካህ​ናቱ ግቢ ገባ። ጴጥ​ሮስ ግን በስ​ተ​ውጭ በበሩ ቆሞ ነበር፤ ያም በሊቀ ካህ​ናቱ ዘንድ ይታ​ወቅ የነ​በ​ረው ሌላው ደቀ መዝ​ሙር ወጣና ለበ​ረ​ኛ​ዪቱ ነግሮ ጴጥ​ሮ​ስን አስ​ገ​ባው። በረ​ኛ​ዪቱ አገ​ል​ጋ​ይም፥ “አን​ተም ከዚያ ሰው ደቀ መዛ​ሙ​ርት ወገን አይ​ደ​ለ​ህ​ምን?” አለ​ችው፤ እር​ሱም፥ “አይ​ደ​ለ​ሁም” አላት። አገ​ል​ጋ​ዮ​ችና ሎሌ​ዎ​ችም በዚያ ቆመው እሳት አን​ድ​ደው ይሞቁ ነበር፤ የዚ​ያች ሌሊት ብርድ ጽኑ ነበ​ርና፤ ጴጥ​ሮ​ስም ከእ​ነ​ርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበረ። ሊቀ ካህ​ና​ቱም ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን፦ ስለ ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱና ስለ ትም​ህ​ርቱ ጠየ​ቀው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ እን​ዲህ አለው፥ “እኔ ለዓ​ለም በግ​ልጥ ተና​ገ​ርሁ፤ አይ​ሁድ ሁሉ በሚ​ሰ​በ​ሰ​ቡ​በት በም​ኵ​ራ​ብም፥ በቤተ መቅ​ደ​ስም ሁል​ጊዜ አስ​ተ​ማ​ርሁ፤ በስ​ው​ርም የተ​ና​ገ​ር​ሁት አን​ዳች ነገር የለም። እን​ግ​ዲህ እኔን ለምን ትጠ​ይ​ቀ​ኛ​ለህ? የተ​ና​ገ​ር​ሁ​ትን የሰ​ሙ​ኝን ጠይ​ቃ​ቸው፤ እኔም የተ​ና​ገ​ር​ሁ​ትን እነሆ፥ እነ​ርሱ ያው​ቃሉ።” ይህ​ንም ባለ​ጊዜ ከቆ​ሙት ሎሌ​ዎች አንዱ፥ “ለሊቀ ካህ​ናቱ እን​ዲህ ትመ​ል​ስ​ለ​ታ​ለ​ህን?” ብሎ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን በጥፊ መታው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ፥ “ክፉ ተና​ግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስ​ክ​ር​ብኝ፤ መል​ካም ተና​ግሬ እንደ ሆንሁ ግን ለምን ትመ​ታ​ኛ​ለህ?” አለው። ሐናም ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን እንደ ታሰረ ወደ ሊቀ ካህ​ናቱ ወደ ቀያፋ ላከው። ስም​ዖን ጴጥ​ሮ​ስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር፤ “አን​ተስ ከእ​ርሱ ደቀ መዛ​ሙ​ርት ወገን አይ​ደ​ለ​ህ​ምን?” አሉት፤ እር​ሱም፥ “አይ​ደ​ለ​ሁም” ብሎ ካደ። ጴጥ​ሮስ ጆሮ​ውን ከቈ​ረ​ጠው ሰው ዘመ​ዶች ወገን የሆነ ከሊቀ ካህ​ናቱ አገ​ል​ጋ​ዮ​ችም አንድ ሰው፥ “እኔ በአ​ት​ክ​ልት ቦታ ውስጥ ከእ​ርሱ ጋር አይ​ችህ አል​ነ​በ​ረ​ምን?” አለው። ጴጥ​ሮ​ስም ደግሞ ካደ፤ ያን​ጊ​ዜም ዶሮ ጮኸ።

ዮሐንስ 18:15-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ስምዖን ጴጥሮስና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉት። ይህም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ይታወቅ ስለ ነበር፣ ከኢየሱስ ጋር ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገባ፤ ጴጥሮስ ግን ከበሩ ውጭ ቀረ። በሊቀ ካህናቱ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙርም ተመለሰና በር ጠባቂዋን አነጋግሮ ጴጥሮስን ይዞት ገባ። በር ጠባቂዋም ጴጥሮስን፣ “አንተ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ። ብርድ ስለ ነበር አገልጋዮቹና ሎሌዎቹ ባያያዙት የከሰል ፍም ዙሪያ ለመሞቅ ቆመው ሳሉ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለዓለም በግልጽ ተናግሬአለሁ፤ አይሁድ በተሰበሰቡበት ምኵራብ፣ በቤተ መቅደስም ሁልጊዜ አስተምሬአለሁ፤ በስውር የተናገርሁት የለም። ለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ እነሆ፤ የተናገርሁትን እነርሱ ያውቃሉ።” ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ፣ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት ሎሌዎች አንዱ፣ “ለሊቀ ካህናቱ የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ በጥፊ መታው። ኢየሱስም፣ “ክፉ ተናግሬ ከሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ እውነት ከተናገርሁ ግን ለምን ትመታኛለህ?” አለው። ሐናም ኢየሱስ ታስሮ እንዳለ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው። ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ሲሞቅ፣ “አንተ ከእርሱ ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አሉት። እርሱም፣ “አይደለሁም” ሲል ካደ። ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮች አንዱ ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመድ፣ “በአትክልቱ ስፍራ አንተን ከእርሱ ጋር አላየሁህም?” ሲል ጠየቀው። ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፤ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።

ዮሐንስ 18:15-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ስምዖን ጴጥሮስም ሌላውም ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀ መዝሙርት በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፥ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤ ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ ቆሞ ነበር። እንግዲህ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙር ወጣ ለበረኛይቱም ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። በረኛ የነበረችይቱም ገረድ ጴጥሮስን፦ “አንተ ደግሞ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱ፦ “አይደለሁም” አለ። ብርድ ነበረና ባሮችና ሎሌዎች የፍም እሳት አንድደው ቆሙ ይሞቁም ነበር፤ ጴጥሮስም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። ሊቀ ካህናቱም ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየስስም መልሶ፦ “እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ እኔ ሁልጊዜ አስተማርሁ፥ በስውርም ምንም አልተናገርሁም። ስለምን ትጠይቀኛለህ? ለእነርሱ የተናገርሁትን የሰሙትን ጠይቅ፤ እነሆ፥ እነዚህ እኔ የነገርሁትን ያውቃሉ” አለው። ይህንም ሲል በዚያ ቆሞ የነበረው ከሎሌዎች አንዱ፦ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። ኢየሱስም መልሶ፦ “ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ሰለ ምን ትመታኛለህ?” አለው። ስለዚህ ሐና እንደ ታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ሰደደው። ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። እንግዲህ፦ “አንተ ደግሞ ከደቀ መዛሙርቱ አይደለህምን?” አሉት። እርሱም፦ “አይደለሁም” ብሎ ካደ። ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ዘመድ የሆነ ከሊቀ ካህናቱ ባሮች አንዱ፦ “በአትክልቱ ከእርሱ ጋር እኔ አይቼህ አልነበረምን?” አለው። ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፥ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።

ዮሐንስ 18:15-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉት፤ ያ ሌላው ደቀ መዝሙር በካህናት አለቃው ዘንድ የታወቀ ነበር፤ ስለዚህ ከኢየሱስ ጋር ወደ ካህናት አለቃው ግቢ ገባ፤ ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ በካህናት አለቃው የታወቀው ደቀ መዝሙር መጣና ለበረኛይቱ ልጃገረድ ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው፤ በረኛይቱም ልጃገረድ ጴጥሮስን “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱ ግን “አይደለሁም” አለ። ጊዜው ብርድ ስለ ነበረ አገልጋዮቹና የዘብ ኀላፊዎች የከሰል እሳት አንድደው ቆመው ይሞቁ ነበር፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቃው ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለሰው ሁሉ በግልጥ ተናገርኩ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኲራብም ሆነ በቤተ መቅደስ፥ ዘወትር አስተማርኩ፤ በስውር የተናገርኩት ምንም ነገር የለም፤ ታዲያ፥ ስለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? ስናገራቸው የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ የተናገርኩትን እነርሱ ያውቃሉ።” ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ እዚያ ቆመው ከነበሩት የዘብ ኀላፊዎች አንዱ፥ “ለካህናት አለቃው የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። ኢየሱስም “ክፉ ቃል ተናግሬ እንደ ሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ የተናገርኩት ትክክል ከሆነ ግን ስለምን ትመታኛለህ?” አለው። ከዚህ በኋላ ሐና፥ ኢየሱስን እንደ ታሰረ ወደ ካህናት አለቃው ወደ ቀያፋ ሰደደው። የዚያን ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር፤ ሌሎች ሰዎችም “አንተስ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አሉት። እርሱም “አይደለሁም” ብሎ ካደ። ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመዱ የሆነው ከካህናት አለቃው ሎሌዎች አንዱ “በአትክልቱ ቦታ ከእነርሱ ጋር አይቼህ አልነበረምን?” አለው። ጴጥሮስም እንደገና ካደ፤ ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ።

ዮሐንስ 18:15-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀመዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀመዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤ ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ ቆሞ ነበር። በሊቀ ካህናቱም ዘንድ የታወቀው ሌላው ደቀመዝሙር ወጣ፤ ለበረኛይቱም ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። በር ጠባቂ አገልጋይቱም ጴጥሮስን “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱ “አይደለሁም” አለ። ይበርድ ነበረና አገልጋዮችና ሎሌዎች የከሰል እሳት አንድደው ቆመው ይሞቁ ነበር፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። ሊቀ ካህናቱም ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ ሁልጊዜ አስተማርሁ፤ በስውርም ምንም አልተናገርሁም። ስለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? ስናገር የሰሙኝን ጠይቅ፤ እነሆ፥ እነርሱ እኔ የተናገርሁትን ያውቃሉ፤” አለው። ይህንን ባለ ጊዜ በዚያ ቆመው ከነበሩት ሎሌዎች አንዱ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። ኢየሱስም መልሶ “ክፉ ተናግሬ እንደሆነ ስለ ክፉ መስክርብኝ፤ መልካም ተናግሬ እንደሆን ግን ስለምን ትመታኛለህ?” አለው። ሐናም እንደታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው። ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። “አንተስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አይደለህምን?” አሉት። እርሱም “አይደለሁም፤” ብሎ ካደ። ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮች መካከል አንዱ፥ ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመድ፥ “በአትክልቱ ስፍራ ከእርሱ ጋር አይቼህ አልነበረምን?” አለው። ጴጥሮስም በድጋሚ ካደ፤ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።