ዮሐንስ 18:1-24
ዮሐንስ 18:1-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታችን ኢየሱስም ይህን ተናግሮ አትክልት ወደ አለበት ስፍራ ወደ ቄድሮስ ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደዚያ ገባ። አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም ያን ስፍራ ያውቀው ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደዚያ ብዙ ጊዜ ይሄድ ነበርና። ይሁዳም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን ወታደሮችን ተቀበለ፤ ሎሌዎቻቸውንም በረዳትነት ወሰደ፤ ፋኖስና የችቦ መብራት፥ የጦር መሣሪያም ይዞ ወደዚያ ሄደ። ጌታችን ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወደ እነርሱ ወደ ውጭ ወጣና፥ “ማንን ትሻላችሁ?” አላቸው። “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ” አላቸው፤ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም በዚያው አብሮአቸው ቆሞ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ፤ ወደ ኋላቸው ተመልሰው በምድር ላይ ወደቁ። ከዚህም በኋላ እንደገና፥ “ማንን ትሻላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ እነርሱም፥ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ እኔን የምትሹ ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አላቸው። ይህም፥ “ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንድ ስንኳ አልጠፋም” ያለው ቃሉ ይፈጸም ዘንድ ነው። ስምዖን ጴጥሮስም ሾተል ነበረው፤ ሾተሉንም መዝዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው፤ የዚህም አገልጋይ ስም ማልኮስ ይባል ነበር። ጌታችን ኢየሱስም ጴጥሮስን፥ “ሾተልህን ወደ አፎቷ መልስ፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ ሳልጠጣ እተወዋለሁን?” አለው። ጭፍሮችና የሺ አለቃው፥ የአይሁድም ሎሌዎች ጌታችን ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። አስቀድሞም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት የካህናት አለቃ ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና። ቀያፋም “ስለ ሕዝቡ ሁሉ አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል” ብሎ አይሁድን የመከራቸው ነበር። ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙርም ጌታችን ኢየሱስን ከሩቅ ተከተሉት፤ ያ ደቀ መዝሙር ግን በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበር፤ ከጌታችን ኢየሱስ ጋርም ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገባ። ጴጥሮስ ግን በስተውጭ በበሩ ቆሞ ነበር፤ ያም በሊቀ ካህናቱ ዘንድ ይታወቅ የነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር ወጣና ለበረኛዪቱ ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። በረኛዪቱ አገልጋይም፥ “አንተም ከዚያ ሰው ደቀ መዛሙርት ወገን አይደለህምን?” አለችው፤ እርሱም፥ “አይደለሁም” አላት። አገልጋዮችና ሎሌዎችም በዚያ ቆመው እሳት አንድደው ይሞቁ ነበር፤ የዚያች ሌሊት ብርድ ጽኑ ነበርና፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበረ። ሊቀ ካህናቱም ጌታችን ኢየሱስን፦ ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እኔ ለዓለም በግልጥ ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብም፥ በቤተ መቅደስም ሁልጊዜ አስተማርሁ፤ በስውርም የተናገርሁት አንዳች ነገር የለም። እንግዲህ እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? የተናገርሁትን የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ እኔም የተናገርሁትን እነሆ፥ እነርሱ ያውቃሉ።” ይህንም ባለጊዜ ከቆሙት ሎሌዎች አንዱ፥ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልስለታለህን?” ብሎ ጌታችን ኢየሱስን በጥፊ መታው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክርብኝ፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ለምን ትመታኛለህ?” አለው። ሐናም ጌታችን ኢየሱስን እንደ ታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው።
ዮሐንስ 18:1-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገረ፤ ማዶ ወደ ነበረውም የአትክልት ስፍራ ገቡ። ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚያ ስለሚገናኝ፣ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ቦታውን ያውቅ ነበር። ይሁዳም ወታደሮችን እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩ ሎሌዎችን እየመራ ወደ አትክልቱ ስፍራ መጣ፤ እነርሱም ችቦ፣ ፋኖስና የጦር መሣሪያ ይዘው ነበር። ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወጣና፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” አላቸው። እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” ባለ ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ። እንደ ገናም፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስም መልሶ፣ “ ‘እርሱ እኔ ነኝ’ ብያችኋለሁ እኮ፤ እኔን የምትፈልጉ ከሆነ፣ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ፤ ይህ የሆነው፣ “ከሰጠኸኝ ከእነዚህ አንድም አልጠፋብኝም” ብሎ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። ሰይፍ ይዞ የነበረው ስምዖን ጴጥሮስም፣ ሰይፉን መዝዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ቀኝ ጆሮ ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም ማልኮስ ይባል ነበር። ኢየሱስም ጴጥሮስን፣ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ! አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣምን?” አለው። ወታደሮቹም ከአዛዣቸውና ከአይሁድ ሎሌዎች ጋር በመሆን ኢየሱስን ያዙት፤ አስረውም፣ በመጀመሪያ የቀያፋ አማት ወደ ነበረው ወደ ሐና አመጡት፤ ቀያፋም የዓመቱ ሊቀ ካህናት ነበር። ቀያፋም ለሕዝቡ ሲባል አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል ብሎ አይሁድን የመከረ ነበር። ስምዖን ጴጥሮስና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉት። ይህም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ይታወቅ ስለ ነበር፣ ከኢየሱስ ጋር ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገባ፤ ጴጥሮስ ግን ከበሩ ውጭ ቀረ። በሊቀ ካህናቱ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙርም ተመለሰና በር ጠባቂዋን አነጋግሮ ጴጥሮስን ይዞት ገባ። በር ጠባቂዋም ጴጥሮስን፣ “አንተ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ። ብርድ ስለ ነበር አገልጋዮቹና ሎሌዎቹ ባያያዙት የከሰል ፍም ዙሪያ ለመሞቅ ቆመው ሳሉ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለዓለም በግልጽ ተናግሬአለሁ፤ አይሁድ በተሰበሰቡበት ምኵራብ፣ በቤተ መቅደስም ሁልጊዜ አስተምሬአለሁ፤ በስውር የተናገርሁት የለም። ለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ እነሆ፤ የተናገርሁትን እነርሱ ያውቃሉ።” ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ፣ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት ሎሌዎች አንዱ፣ “ለሊቀ ካህናቱ የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ በጥፊ መታው። ኢየሱስም፣ “ክፉ ተናግሬ ከሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ እውነት ከተናገርሁ ግን ለምን ትመታኛለህ?” አለው። ሐናም ኢየሱስ ታስሮ እንዳለ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው።
ዮሐንስ 18:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም ይህን ብሎ አትክልት ወዳለበት ስፍራ ወደ ቄድሮን ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ እነርሱም ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ገቡ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ጊዜ ወደዚያ ስለ ተሰበሰቡ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ደግሞ ስፍራውን ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይሁዳ ጭፍሮችንና ካህናት አለቆች ከፈሪሳውያንም ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና በጋሻ ጦርም ወደዚያ መጣ። ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና፦ “ማንን ትፈልጋላችሁ” አላቸው። “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት። ኢየሱስ፦ “እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። እንግዲህ፦ እኔ ነኝ ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በምድር ወደቁ። ደግሞም፦ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፦ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስ መልሶ፦ “እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ትፈልጉ እንደ ሆናችሁ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ፤ ይህም፦ “ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን ስንኳ አላጠፋሁም” ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ስምዖን ጴጥሮስም ሰይፍ ስለ ነበረው መዘዘው፥ የሊቀ ካህናቱንም ባርያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የባርያውም ስም ማልኮስ ነበረ። ኢየሱስም ጴጥሮስን፦ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተተው፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣምን?” አለው። እንግዲህ የሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት፥ አስቀድመውም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና። ቀያፋም፦ “አንድ ሰው ስለ ሕዝብ ይሞት ዘንድ ይሻላል” ብሎ ለአይሁድ የመከራቸው ነበረ። ስምዖን ጴጥሮስም ሌላውም ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀ መዝሙርት በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፥ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤ ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ ቆሞ ነበር። እንግዲህ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙር ወጣ ለበረኛይቱም ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። በረኛ የነበረችይቱም ገረድ ጴጥሮስን፦ “አንተ ደግሞ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱ፦ “አይደለሁም” አለ። ብርድ ነበረና ባሮችና ሎሌዎች የፍም እሳት አንድደው ቆሙ ይሞቁም ነበር፤ ጴጥሮስም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። ሊቀ ካህናቱም ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየስስም መልሶ፦ “እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ እኔ ሁልጊዜ አስተማርሁ፥ በስውርም ምንም አልተናገርሁም። ስለምን ትጠይቀኛለህ? ለእነርሱ የተናገርሁትን የሰሙትን ጠይቅ፤ እነሆ፥ እነዚህ እኔ የነገርሁትን ያውቃሉ” አለው። ይህንም ሲል በዚያ ቆሞ የነበረው ከሎሌዎች አንዱ፦ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። ኢየሱስም መልሶ፦ “ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ሰለ ምን ትመታኛለህ?” አለው። ስለዚህ ሐና እንደ ታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ሰደደው።
ዮሐንስ 18:1-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቄድሮን ሸለቆ ማዶ ሄደ፤ እዚያ ወደነበረውም የአትክልት ቦታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ገባ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እዚያ ቦታ ዘወትር ይሰበሰቡ ስለ ነበር አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ያን ቦታ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይሁዳ አንድ የወታደሮች ጭፍራ፥ እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩትን የዘብ ኀላፊዎችን አስከትሎ ወደዚያ ቦታ መጣ፤ እነርሱም ፋኖስና ችቦ፥ የጦር መሣሪያም ይዘው ነበር። ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወደ እነርሱ ወጣ ብሎ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ እንፈልጋለን” አሉት። እርሱም “እኔ ነኝ!” አላቸው። አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። ኢየሱስ “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈገፈጉና በምድር ላይ ወደቁ። ኢየሱስም “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ሲል እንደገና ጠየቃቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ እንፈልጋለን” አሉ። እርሱም “እኔ ነኝ ብዬአችኋለሁ፤ እንግዲህ የምትፈልጉት እኔን ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አለ። ይህም የሆነው፥ “አባት ሆይ፥ ከሰጠኸኝ ሰዎች አንዱን እንኳ አላጠፋሁም” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው። ስምዖን ጴጥሮስ ሰይፍ ይዞ ስለ ነበረ መዘዘና የካህናት አለቃውን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም “ማልኮስ” ይባል ነበር። ኢየሱስ ግን ጴጥሮስን፥ “ሰይፍህን ወደ አፎቱ ክተተው፤ አብ የሰጠኝን የመከራ ጽዋ የማልጠጣው ይመስልሃልን?” አለው። ከዚህ በኋላ ወታደሮቹና አዛዣቸው፥ የአይሁድ የዘብ ኀላፊዎችም ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። በመጀመሪያ ወደ ሐና ወሰዱት፤ ሐና በዚያ ዓመት የካህናት አለቃ ለነበረው ለቀያፋ ዐማቱ ነበር። ቀያፋ “አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት የተሻለ ነው” ሲል የአይሁድ ባለሥልጣኖችን የመከረ ነው። ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉት፤ ያ ሌላው ደቀ መዝሙር በካህናት አለቃው ዘንድ የታወቀ ነበር፤ ስለዚህ ከኢየሱስ ጋር ወደ ካህናት አለቃው ግቢ ገባ፤ ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ በካህናት አለቃው የታወቀው ደቀ መዝሙር መጣና ለበረኛይቱ ልጃገረድ ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው፤ በረኛይቱም ልጃገረድ ጴጥሮስን “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱ ግን “አይደለሁም” አለ። ጊዜው ብርድ ስለ ነበረ አገልጋዮቹና የዘብ ኀላፊዎች የከሰል እሳት አንድደው ቆመው ይሞቁ ነበር፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቃው ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለሰው ሁሉ በግልጥ ተናገርኩ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኲራብም ሆነ በቤተ መቅደስ፥ ዘወትር አስተማርኩ፤ በስውር የተናገርኩት ምንም ነገር የለም፤ ታዲያ፥ ስለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? ስናገራቸው የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ የተናገርኩትን እነርሱ ያውቃሉ።” ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ እዚያ ቆመው ከነበሩት የዘብ ኀላፊዎች አንዱ፥ “ለካህናት አለቃው የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። ኢየሱስም “ክፉ ቃል ተናግሬ እንደ ሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ የተናገርኩት ትክክል ከሆነ ግን ስለምን ትመታኛለህ?” አለው። ከዚህ በኋላ ሐና፥ ኢየሱስን እንደ ታሰረ ወደ ካህናት አለቃው ወደ ቀያፋ ሰደደው።
ዮሐንስ 18:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም ይህን ብሎ አትክልት ወዳለበት ስፍራ ወደ ቄድሮን ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ እርሱም ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ገቡ። ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ብዙ ጊዜ ወደዚያ ስለ ተሰበሰቡ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ስፍራውን ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይሁዳ ወታደሮችን፥ እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና፥ በጦር መሣርያም ታጅቦ ወደዚያ መጣ። ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት። እርሱም “እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። ኢየሱስም “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመሬት ላይ ወደቁ። ዳግመኛ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስ መልሶ “እኔ ነኝ፤ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ከሆነ የምትፈልጉት እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አለ፤ ይህም “ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን እንኳን አላጠፋሁም” ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ስምዖን ጴጥሮስም ሰይፍ ይዞ ስለ ነበር መዘዘውና የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም ማልኮስ ነበረ። ኢየሱስም ጴጥሮስን “ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተተው፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ ላልጠጣ ነውን?” አለው። እንግዲህ ወታደሮቹና አዛዣቸው፥ የአይሁድም ሎሌዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት፤ አስቀድመውም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና። ቀያፋም “ስለ ሕዝቡ ሲባል አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል” ሲል አይሁድን የመከራቸው ነበረ። ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀመዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀመዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤ ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ ቆሞ ነበር። በሊቀ ካህናቱም ዘንድ የታወቀው ሌላው ደቀመዝሙር ወጣ፤ ለበረኛይቱም ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። በር ጠባቂ አገልጋይቱም ጴጥሮስን “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱ “አይደለሁም” አለ። ይበርድ ነበረና አገልጋዮችና ሎሌዎች የከሰል እሳት አንድደው ቆመው ይሞቁ ነበር፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። ሊቀ ካህናቱም ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ ሁልጊዜ አስተማርሁ፤ በስውርም ምንም አልተናገርሁም። ስለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? ስናገር የሰሙኝን ጠይቅ፤ እነሆ፥ እነርሱ እኔ የተናገርሁትን ያውቃሉ፤” አለው። ይህንን ባለ ጊዜ በዚያ ቆመው ከነበሩት ሎሌዎች አንዱ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። ኢየሱስም መልሶ “ክፉ ተናግሬ እንደሆነ ስለ ክፉ መስክርብኝ፤ መልካም ተናግሬ እንደሆን ግን ስለምን ትመታኛለህ?” አለው። ሐናም እንደታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው።