ዮሐንስ 17:20-24
ዮሐንስ 17:20-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“የምለምንህም ስለ እነዚህ ብቻ አይደለም፤ በቃላቸው ስለሚያምኑብኝም ነው እንጂ፤ ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ አንተ አብ በእኔ እንዳለህ፥ እኔም በአንተ እንዳለሁ፥ እነርሱም እንደ እኛ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ። እኔም የሰጠኸኝን ክብር ሰጠኋቸው፤ እኛ አንድ እንደሆን እነርሱም እንደ እኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ። እኔ በእነርሱ እኖራለሁ፤ አንተም በእኔ፤ በአንድ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ፤ አንተም እንደ ላክኸኝና እንደ ወደድኸኝ እኔም እነርሱን እንደ ወደድኋቸው። አባት ሆይ፥ የሰጠኸኝ እነዚህ እኔ ባለሁበት አብረውኝ ይኖሩ ዘንድና የሰጠኸኝን ክብሬን ያዩ ዘንድ እወድዳለሁ፤ ዓለም ሳይፈጠር ወድደኸኛልና።
ዮሐንስ 17:20-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው በእኔ ለሚያምኑ ጭምር እንጂ ለእነዚህ ብቻ አልጸልይም፤ ይህም፣ አባት ሆይ፤ አንተ በእኔ፣ እኔም በአንተ እንዳለሁ ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም አንተ እኔን እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፣ እነርሱም በእኛ እንዲሆኑ ነው። እኛ አንድ እንደ ሆንን እነርሱም አንድ እንዲሆኑ፣ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። ይህም እኔ በእነርሱ፣ አንተም በእኔ መሆንህ ነው። አንተ እንደ ላክኸኝና እኔን በወደድኸኝ መጠን እነርሱንም እንደ ወደድሃቸው ዓለም ያውቅ ዘንድ፣ አንድነታቸው ፍጹም ይሁን። “አባት ሆይ፤ እነዚህ የሰጠኸኝ፣ እኔ ባለሁበት እንዲሆኑ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝንም ክብሬን እንዲያዩ እፈልጋለሁ።
ዮሐንስ 17:20-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ። እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ።
ዮሐንስ 17:20-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“በእነርሱ ቃል አማካይነት በእኔ ስለሚያምኑትም እለምናለሁ እንጂ ለእነርሱ ብቻ አለምንም። እኔም የምለምነው ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ እንዲሁም አባት ሆይ! አንተ በእኔ እንዳለህ፥ እኔም በአንተ እንዳለሁ፥ እነርሱም በእኛ እንዲኖሩ ነው፤ አንተ እንደ ላክኸኝም ዓለም እንዲያምን ነው። እኛ አንድ እንደ ሆንን እነርሱም አንድ እንዲሆኑ ለእኔ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። እኔ የምለምነው እኔ በእነርሱ አንተም በእኔ እንደ ሆንክ እነርሱም በፍጹም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ እንዲሁም እኔን እንደ ላክኸኝና እኔን በወደድከኝ መጠን እነርሱንም እንደ ወደድካቸው ዓለም እንዲያውቅ ነው። “አባት ሆይ! ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድከኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እነዚህ አንተ የሰጠኸኝም እኔ ባለሁበት ከእኔ ጋር እንዲኖሩ እወዳለሁ።
ዮሐንስ 17:20-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በእነርሱ ቃል አማካይነት በእኔ ስለሚያምኑትም ጭምር እንጂ ስለ እነርሱ ብቻ አልለምንም፤ ይህም ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፥ አንተም፥ አባት ሆይ! በእኔ እንዳለህና እኔም በአንተ እንዳለሁ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ እንዲሆኑ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ ዓለም እንዲያምን ነው። እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ፤ ይህም እኔ በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በፍጹም አንድ እንዲሆኑ፥ እንዲሁም አንተ እንደ ላክኸኝና በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ዓለም እንዲያውቅ ነው። አባት ሆይ! ዓለም ሳይፈጠር በፊት ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ፥ የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ እኔ ባለሁበት ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ።