ዮሐንስ 16:4-33
ዮሐንስ 16:4-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ነገርኋችሁ። አስቀድሜ ግን ይህን አልነገርክኋችሁም ነበር፤ ከእናንተ ጋር ነበርሁና። አሁን ግን ወደ ላከኝ ወደ አብ እሄዳለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እንኳ፦ ‘ወዴት ትሄዳለህ?’ ብሎ አይጠይቀኝም። ነገር ግን ይህን ስለ ነገርኋችሁ በልባችሁ ኀዘን ሞላ። “እኔ በእውነት የሚሆነውን እነግራችኋለሁ፤ እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፤ እኔ ካልሄድሁ ጰራቅሊጦስ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ከሄድሁ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱም በመጣ ጊዜ ዓለምን ስለ ኀጢአትና ስለ ጽድቅ፥ ስለ ፍርድም ይዘልፈዋል። ስለ ኀጢኣት፥ በእኔ አላመኑምና ነው፤ ስለ ጽድቅ፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፥ እንግዲህ ወዲህም አታዩኝምና ነው። ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዢ ይፈረድበታልና ነው። “የምነግራችሁ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ያ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ግን ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ እርሱ ከራሱ አይናገርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱም እኔን ያከብረኛል፤ ከእኔ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህም ከእኔ ወስዶ ይነግራችኋል አልኋችሁ። “ጥቂት ጊዜ አለ፤ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንደገናም ታዩኛላችሁ፤ ወደ አብ እሄዳለሁና።” ደቀ መዛሙርቱም እርስ በርሳቸው፥ “ጥቂት ጊዜ አለ፤ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንደገናም ታዩኛላችሁ፥ ወደ አብ እሄዳለሁና የሚለን ይህ ነገር ምንድነው?” ተባባሉ። “ይህ ጥቂት የሚለን ምንድነው? የሚናገረውን አናውቅም” አሉ። ጌታችን ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደሚሹ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፥ “ጥቂት ጊዜ አለ፤ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንደገናም ታዩኛላችሁ” ስለ አልኋችሁ፥ ስለዚህ ነገር እርስ በርሳችሁ ትመራመራላችሁን? “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝኑማላችሁ፤ ዓለምም ደስ ይለዋል፤ እናንተ ግን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራቷ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ነገር ግን ልጅዋን ከወለደች በኋላ ስለ ደስታዋ ከዚያ ወዲያ ምጥዋን አታስበውም፤ በዓለም ወንድ ልጅን ወልዳለችና። እናንተም ዛሬ ታዝናላችሁ፤ እንደገናም አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። ያንጊዜም እኔን የምትለምኑኝ አንዳች የለም፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በስሜ አብን ብትለምኑት ሁሉን ይሰጣችኋል። እስካሁን ምንም በስሜ አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም ይሆን ዘንድ ለምኑ፤ ታገኙማላችሁ። “ዛሬስ በምሳሌ ነገርኋችሁ፤ ነገር ግን የአብን ነገር ገልጬ እነግራችኋለሁ እንጂ ለእናንተ በምሳሌ የማልናገርበት ጊዜ ይመጣል። ያንጊዜ በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እለምነዋለህ አልላችሁም፤ እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ፤ ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣሁ ስለ አመናችሁብኝ እርሱ ራሱ አብ ወድዷችኋልና። ከአብ ወጣሁ፤ ወደ ዓለምም መጣሁ፤ ዳግመኛም ዓለምን እተወዋለሁ፤ ወደ አብም እሄዳለሁ።” ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉት፥ “እነሆ፥ ዛሬ ገልጠህ ትናገራለህ፤ ምንም በምሳሌ የተናገርኸው የለም። አሁን አንተ ሁሉን እንደምታውቅ፥ ማንም ሊነግርህ እንደማትሻ ዐወቅን፤ በዚህም ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን።” ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “አሁን ታምናላችሁን? እያንዳንዳችሁ በየቦታዉ የምትበታተኑበት፥ እኔንም ብቻዬን የምትተዉበት ጊዜ ይደርሳል፤ ደርሶአልም፤ እኔ ግን ብቻዬን አይደለሁም፤ አብ ከእኔ ጋር ነውና። በእኔም ሰላምን እንድታገኙ ይህን ነገርኋችሁ፤ በዓለም ግን መከራን ትቀበላላችሁ፤ ነገር ግን ጽኑ፤ እኔ ዓለሙን ድል ነሥቼዋለሁና።”
ዮሐንስ 16:4-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አስቀድሜ ይህን የነገርኋችሁ ጊዜው ሲደርስ እንድታስታውሱ ነው፤ ከእናንተ ጋራ ስለ ነበርሁ፣ ይህን ከመጀመሪያው አልነገርኋችሁም። “እንግዲህ ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ ይሁን እንጂ ከእናንተ፣ ‘የምትሄደው የት ነው?’ ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። ይህን በመናገሬም ልባችሁ በሐዘን ተሞልቷል፤ ነገር ግን፣ እውነት እላችኋለሁ፤ መሄዴ ይበጃችኋል። እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድሁ ግን እርሱን ወደ እናንተ እልካለሁ፤ በሚመጣበትም ጊዜ ዓለምን ስለ ኀጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ይወቅሣል። ስለ ኀጢአት ሲባል፣ ሰዎች በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅ፣ ወደ አብ ስለምሄድና ከእንግዲህ ስለማታዩኝ ነው፤ ስለ ፍርድም፣ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። “ብዙ የምነግራችሁ ነበረኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም። የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤ የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ በማድረግ ያከብረኛል። የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው፤ እንግዲህ፣ ‘የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ ያደርጋል’ ያልኋችሁ ለዚሁ ነው። “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ።” ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ፣ “ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ እንዲሁም፣ ‘ወደ አብ ስለምሄድ’ ሲል ምን ማለቱ ነው?” ተባባሉ፤ “ ‘ጥቂት ጊዜ’ ማለቱስ ምን ይሆን? የሚለውም ነገር አልገባንም” እያሉ ይጠያየቁ ነበር። ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ፈለጉ ባወቀ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ፣ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ ስላልኋችሁ፣ ምን ማለቴ እንደ ሆነ እርስ በርሳችሁ ትጠያየቃላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝናላችሁም፤ ዓለም ግን ሐሤት ያደርጋል፤ ይሁን እንጂ ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። ሴት ቀኗ ደርሶ ስትወልድ ትጨነቃለች፤ ከተገላገለች በኋላ ግን፣ ሰው ወደ ዓለም ተወልዷልና ስለ ደስታዋ ጭንቋን ትረሳለች፤ ለእናንተም እንደዚሁ አሁን የሐዘን ጊዜ ነው፤ ሆኖም እንደ ገና አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። በዚያ ቀን ከእኔ ምንም አትለምኑም፤ እውነት እላችኋለሁ፤ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ለምኑ ትቀበላላችሁ፤ ደስታችሁም ሙሉ ይሆናል። “እስከ አሁን የነገርኋችሁ በምሳሌ ቢሆንም እንኳ፣ ከእንግዲህ ግን ስለ አብ በምሳሌ ሳይሆን በግልጽ የምናገርበት ጊዜ ይመጣል። በዚያ ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ ይህም በእናንተ ፈንታ አብን እለምናለሁ ማለቴ አይደለም፤ ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ ራሱ ይወድዳችኋል። ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ አሁን ግን ዓለምን ትቼ ወደ አብ እሄዳለሁ።” ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አሉ፤ “አሁንም እኮ ያለ ምሳሌ በግልጽ እየተናገርህ ነው። አሁን ሁሉን ነገር እንደምታውቅና ማንም ሊጠይቅህ እንደማያስፈልግ ተረድተናል፤ ይህም ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እንድናምን አድርጎናል።” ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንስ አመናችሁ ማለት ነው? እነሆ፤ ሁላችሁም በየፊናችሁ የምትበታተኑበት ጊዜ ይመጣል፤ ያም ጊዜ አሁን ነው። እኔንም ብቻዬን ትተዉኛላችሁ፤ ይሁን እንጂ አባቴ ከእኔ ጋራ ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም። “በእኔ ሰላም እንዲኖራችሁ፣ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”
ዮሐንስ 16:4-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ተናግራአችኋለሁ። ከእንናንተም ጋር ስለ ነበርሁ በመጀመሪያ ይህን አልነገርኋችሁም። አሁን ግን ወደ ላከኝ እሄዳለሁ ከእናንተም፦ “ወዴት ትሄዳለህ?” ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። ነገር ግን ይህን ስለ ተናገርኋሁ ኀዘን በልባችሁ ሞልቶአል። እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ከእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፦ “ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል” አልሁ። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና።” ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው፦ “ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁ፤ ደግሞ፦ “ወደ አብ እሄዳለሁና” የሚለን ይህ ምንድር ነው?” ተባባሉ። “እንግዲህ፦ “ጥቂት” የሚለው ይህ ምንድር ነው? የሚናገረውን አናውቅም” አሉ። ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ወደዱ አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁ ስላልሁ፥ ስለዚህ እርስ በርሳችሁ ትመራመራላችሁን? እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተ ታለቅሳለችሁ ሙሾም ታወጣላችሁ፥ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተም ታዝናላችሁ፥ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራትዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ነገር ግን ሕፃን ከወለደች በኋላ፥ ሰው በዓለም ተወልዶአልና ስለ ደስታዋ መከራዋን ኋላ አታስበውም። እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን እንደ ገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል፥ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ። ይህን በምሳሌ ነግሬአችኋለሁ፤ ነገር ግን ስለ አብ ለእናንተ በግልጥ የምናገርበት እንጂ ከዚያ ወዲያ በምሳሌ የማልናገርበት ሰዓት ይመጣል። በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፤ እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና። ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ።” ደቀ መዛሙርቱ፦ “እነሆ፥ አሁን በግልጥ ትናገራለህ በምሳሌም ምንም አትነግርም። ሁሉን እንድታውቅ ማንምም ሊጠይቅህ እንዳትፈልግ አሁን እናውቃለን፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ “አሁን ታምናላችሁን? እነሆ፥ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤት የምትበታተኑበት እኔንም ለብቻዬ የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፥ አሁንም ደርሶአል፤ ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም። በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”
ዮሐንስ 16:4-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህንን ለእናንተ መናገሬ ግን ጊዜው ሲደርስ ምን እንዳልኳችሁ እንድታስታውሱ ነው።” “ይህን ሁሉ ከአሁን በፊት ያልነገርኳችሁ ከእናንተ ጋር ስለ ነበርኩ ነው፤ አሁን ግን ወደ ላከኝ መሄዴ ነው፤ ሆኖም ከእናንተ ‘ወዴት ትሄዳለህ?’ ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ስለ ነገርኳችሁ ልባችሁ በሐዘን ተሞልቶአል። እኔ ግን እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ የእኔ መሄድ ለእናንተ ይጠቅማችኋል፤ እኔ ካልሄድኩ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ እኔ ከሄድኩ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱ በመጣ ጊዜ ስለ ኃጢአት፥ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድም ምክንያት የዓለምን ሰዎች ያጋልጣል። ስለ ኃጢአት የሚያጋልጠው በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅ የሚያጋልጠው ወደ አብ ስለምሄድና ከእንግዲህ ወዲህ ስለማታዩኝ ነው፤ ስለ ፍርድ የሚያጋልጠው የዚህ ዓለም ገዢ ስለ ተፈረደበት ነው። “ገና የምነግራችሁ ብዙ ነገር አለኝ፤ ነገር ግን አሁን ይከብዳችኋል፤ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ የሚናገረው የሰማውን እንጂ የራሱን ስላልሆነ እርሱ ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ይነግራችኋል። የእኔ ከሆነው ወስዶ ስለሚነግራችሁ እኔን ያከብረኛል። የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው፤ ‘የእኔ ከሆነው ወስዶ ይነግራችኋል’ ያልኳችሁ ስለዚህ ነው። “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ እንደገናም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁ።” ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶች፥ “ይህ፥ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ደግሞ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁ፤ ደግሞ ወደ አብ እሄዳለሁ’ የሚለን ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ። “እንግዲህ ይህ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ’ የሚለው ነገር ምንድን ነው? የሚናገረውን ነገር አናውቅም” በመባባል መላልሰው ተጠያየቁ። ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ፈለጉ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ የምትጠያየቁ፥ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ደግሞም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁ’ ስላልኳችሁ ነውን? እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ትጮኻላችሁም፤ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተ ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። ሴት በምትወልድበት ጊዜ የምጥ ቀንዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ከወለደች በኋላ ግን በዓለም ላይ ሕፃን ስለ ተወለደ ከመደሰትዋ የተነሣ ጭንቀትዋን አታስታውሰውም። እንዲሁም እናንተ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን እኔ እንደገና አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። “በዚያን ቀን ከእኔ ምንም አትለምኑም፤ እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ አብን በስሜ ብትለምኑት ሁሉን ነገር ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም ነገር አለመናችሁም፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ደስታችሁም ፍጹም ይሆናል። “እስከ አሁን በምሳሌ ነገርኳችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ በምሳሌ የማልናገርበት ጊዜ ይመጣል፤ ነገር ግን ስለ አብ ሁሉን ነገር ገልጬ እነግራችኋለሁ። በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ‘አብን እለምንላችኋለሁ’ አልላችሁም። ምክንያቱም አብ ራሱ ስለሚወዳችሁ ነው፤ አብም የሚወዳችሁ እኔን ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣሁ ስላመናችሁ ነው። ከአብ ዘንድ ወጥቼ፥ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ እንደገናም ይህን ዓለም ትቼ፥ ወደ አብ እሄዳለሁ።” ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉ፤ “እነሆ! አሁን በምሳሌ ሳይሆን በግልጥ ተናገርክ፤ አንተ ሁሉን እንደምታውቅና ማንም ጥያቄ ሊያቀርብልህ እንደማያስፈልግህ አሁን ዐወቅን፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ወጣህ እናምናለን።” ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አሁንስ አምናችኋል? ይሁን እንጂ እያንዳንዳችሁ በየበኩላችሁ የምትበታተኑበትና እኔን ብቻዬን የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፤ ሰዓቱም አሁን ደርሶአል፤ ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም። ይህን ለእናንተ መናገሬ በእኔ ሆናችሁ ሰላም እንዲኖራችሁ ብዬ ነው፤ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፥ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”
ዮሐንስ 16:4-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። ከእናንተም ጋር ስለ ነበርሁ በመጀመሪያ ይህን አልነገርኋችሁም። “አሁን ግን ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ ከእናንተም ‘ወዴት ትሄዳለህ?’ ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። ነገር ግን ይህን ስለ ነገርኋችሁ ኀዘን በልባችሁ ሞልቶአል። እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ ብሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። “ገና ብዙ የምነግራችሁ አለኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ግን እርሱ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ ከራሱ አይናገርምና፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፤ የእኔ ከሆነው ወስዶ ይነግራችኋልና። በአብ ዘንድ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህም ‘በእኔ ዘንድ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል’ አልሁ። “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ፤ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና።” ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ፤”፥ ደግሞ “ወደ አብ እሄዳለሁና፤ የሚለን ነገር ምንድነው?” ተባባሉ። “እንግዲህ ‘ጥቂት’ ሲል ምን ማለቱ ነው? የሚናገረውን አናውቅም” አሉ። ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ወደዱ አውቆ እንዲህ አላቸው “‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ፤’ ስላልሁ፥ እርስ በርሳችሁ ትመራመራላችሁን? እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳለችሁ፤ ሙሾም ታወጣላችሁ፤ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተም ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራትዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ነገር ግን ሕፃን ከወለደች በኋላ፥ ሰው በዓለም ተወልዶአልና በደስታዋ ምክንያት መከራዋን ከቶውን አታስበውም። እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን እንደገና አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። በዚያን ቀንም ከእኔ ምንም ነገር አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ፤ ትቀበሉማላችሁ።” ይህን በምሳሌ ነግሬአችኋለሁ፤ ነገር ግን ስለ አብ በምሳሌ ሳይሆን በግልጥ ለእናንተ የምናገርበት ሰዓት ይመጣል። በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እለምናለሁ አልላችሁም፤ ምክንያቱም አብ እራሱ ስለሚወዳችሁ ነው፤ ይህም እናንተ ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደመጣሁ ስላመናችሁ ነው። ከአብ ዘንድ መጣሁ፤ ወደ ዓለምም መጥቻለሁ፤ ደግሞም ዓለምን እተወዋለሁ፤ ወደ አብም እሄዳለሁ። ደቀመዛሙርቱ “እነሆ፥ አሁን በግልጥ ትናገራለህ፤ በምሳሌም መናገር አቆምህ። ሁሉንም ነገር እንደምታውቅ፥ እንዲሁም ማንም ሊጠይቅህ እንደማያስፈልግ አሁን እናውቃለን፤ ስለዚህም ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናምናለን፤” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ “አሁን ታምናላችሁን? እነሆ፥ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤት የምትበታተኑበት እኔንም ለብቻዬ የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፤ አሁንም ደርሶአል፤ ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም። በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ፤”