የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዮሐንስ 13:6-17

ዮሐንስ 13:6-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ወደ ስም​ዖን ጴጥ​ሮ​ስም ደረሰ፤ እር​ሱም፥ “አቤቱ፥ አንተ እግ​ሬን ታጥ​በ​ኛ​ለ​ህን?” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “እኔ የም​ሠ​ራ​ውን አንተ ዛሬ አታ​ው​ቅም፤ ኋላ ግን ታስ​ተ​ው​ለ​ዋ​ለህ” ብሎ መለ​ሰ​ለት። ጴጥ​ሮ​ስም፥ “መቼም ቢሆን አንተ እግ​ሬን አታ​ጥ​በ​ኝም” አለው፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “እው​ነት እው​ነት እል​ሃ​ለሁ፤ እኔ እግ​ር​ህን ካላ​ጠ​ብ​ሁህ ከእኔ ጋር ዕድል ፋንታ የለ​ህም” ብሎ መለ​ሰ​ለት። ስም​ዖን ጴጥ​ሮ​ስም፥ “አቤቱ፥ እን​ኪ​ያስ የም​ታ​ጥ​በኝ እጆ​ች​ንና ራሴ​ንም እንጂ እግ​ሮ​ችን ብቻ አይ​ደ​ለም፤” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ፈጽሞ የታ​ጠበ ከእ​ግሩ በቀር ሊታ​ጠብ አያ​ስ​ፈ​ል​ገ​ውም፤ ሁለ​ን​ተ​ናው ንጹሕ ነውና፤ እና​ን​ተማ ንጹ​ሓን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላ​ችሁ አይ​ደ​ላ​ች​ሁም” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም አሳ​ልፎ የሚ​ሰ​ጠ​ውን ያውቅ ነበ​ርና ስለ​ዚህ “ሁላ​ችሁ ንጹ​ሓን አይ​ደ​ላ​ች​ሁም” አለ። እግ​ራ​ቸ​ው​ንም ካጠ​ባ​ቸው በኋላ ልብ​ሱን አን​ሥቶ ለበ​ሰና እንደ ገና ከእ​ነ​ርሱ ጋር ተቀ​መጠ፤ እን​ዲ​ህም አላ​ቸው፥ “ያደ​ረ​ግ​ሁ​ላ​ች​ሁን ዐወ​ቃ​ች​ሁን? እና​ንተ ‘መም​ህ​ራ​ችን፥ ጌታ​ች​ንም’ ትሉ​ኛ​ላ​ችሁ፤ መል​ካም ትላ​ላ​ችሁ፤ እኔ እን​ዲሁ ነኝና። እን​ግ​ዲህ እኔ መም​ህ​ራ​ች​ሁና ጌታ​ችሁ ስሆን እግ​ራ​ች​ሁን ካጠ​ብ​ኋ​ችሁ እና​ን​ተም እን​ዲሁ የባ​ል​ጀ​ሮ​ቻ​ች​ሁን እግር ልታ​ጥቡ ይገ​ባ​ች​ኋል። እኔ እንደ አደ​ረ​ግ​ሁ​ላ​ችሁ እና​ን​ተም ልታ​ደ​ርጉ ምሳሌ ሰጥ​ቻ​ች​ኋ​ለ​ሁና። እው​ነት እው​ነት እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ ከጌ​ታው የሚ​በ​ልጥ አገ​ል​ጋይ የለም፤ ከላ​ከው የሚ​በ​ልጥ መል​እ​ክ​ተ​ኛም የለም። ይህ​ንም ዐው​ቃ​ችሁ ብት​ሠሩ ብፁ​ዓን ናችሁ።

ዮሐንስ 13:6-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ እግሬን ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ፣ “የማደርገውን አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። ጴጥሮስም፣ “የለም፤ እግሬን ከቶ አታጥብም” አለው። ኢየሱስም፣ “ካላጠብሁህማ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ እንግዲያውስ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንም ራሴንም ዕጠበኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ገላውን የታጠበ ሰው የሚያስፈልገው እግሩን ብቻ መታጠብ ነው፤ የቀረው አካሉ ግን ንጹሕ ነው። ሁላችሁም ባትሆኑ፣ እናንተ ንጹሓን ናችሁ” አለው። “ሁላችሁም ንጹሓን አይደላችሁም” ያለው አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው። እግራቸውን ዐጥቦ ካበቃ በኋላም፣ ልብሱን ለብሶ ተመልሶ በቦታው ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ፣ ‘መምህርና፣ ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ ትክክል ነው፤ እንደምትሉኝ እንዲሁ ነኝና። እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተም እንደዚሁ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል። እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ ምሳሌ ትቼላችኋለሁ። እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው፣ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። እንግዲህ እነዚህን ነገሮች ዐውቃችሁ ብትፈጽሙ ትባረካላችሁ።

ዮሐንስ 13:6-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፥ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። ጴጥሮስም፦ “የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም” አለው። ኢየሱስም፦ “ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም” ብሎ መለሰለት። ስምዖን ጴጥሮስም፦ “ጌታ ሆይ፥ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም” አለው። ኢየሱስም፦ “የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ግን ንጽሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፥ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም” አለው። አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና፤ ስለዚህ፦ “ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም” አለው። እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው፦ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ።

ዮሐንስ 13:6-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ወደ ስምዖን ጴጥሮስ በመጣ ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ፥ “ጌታ ሆይ! አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። ጴጥሮስም “አንተ የእኔን እግር ከቶ አታጥብም!” አለው። ኢየሱስም “እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ድርሻ የለህም” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! እንዲህስ ከሆነ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንም፥ ራሴንም እጠበኝ!” አለው። ኢየሱስም “ሰውነቱን የታጠበ ሁለመናውም ንጹሕ በመሆኑ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፤ እናንተም ንጹሖች ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም ንጹሖች አይደላችሁም” አለው። ኢየሱስ “ሁላችሁም ንጹሖች አይደላችሁም” ያለው አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው። እግራቸውን ካጠበ በኋላ ልብሱን ለበሰና ወደ ቦታው ተመልሶ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ምን እንዳደረግሁላችሁ አስተዋላችሁን? እናንተ ‘መምህርና ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ እኔ መምህርና ጌታ ስለ ሆንኩ ያላችሁት ትክክል ነው። እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን መተጣጠብ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁት እናንተም እንድታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላኪው አይበልጥም። ይህን ነገር ብታውቁና በሥራ ላይ ብታውሉት የተባረካችሁ ናችሁ።

ዮሐንስ 13:6-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም “ጌታ ሆይ! አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። ጴጥሮስም “የእኔን እግር በጭራሽ አታጥብም” አለው። ኢየሱስም “ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ድርሻ የለህም፤” ብሎ መለሰለት። ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! እንግዲያውስ እግሬን ብቻ ሳይሆን፥ እጄንና ራሴንም ጭምር” አለው። ኢየሱስም “ሰውነቱን የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፤ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም አይደላችሁም፤” አለው። አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና “ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም” አለው። እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ ስለሆንኩም መልካም ትናገራላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተም እንዲሁ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ ይህንን ስታውቁና ስታደርጉ ብፁዓን ናችሁ።