ዮሐንስ 13:31-38
ዮሐንስ 13:31-38 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይሁዳም ከወጣ በኋላ ያንጊዜ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ከበረ። እግዚአብሔር በእርሱ ከከበረ እግዚአብሔርም እርሱን ያከብረዋል፥ ያንጊዜም ያከብረዋል። ልጆች ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር አለሁ፤ ትሹኛላችሁ፤ ለአይሁድም እኔ ወደምሄድበት እናንተ መምጣት አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፥ አሁንም ለእናንተ እነግራችኋለሁ። “እርስ በርሳችሁ ቷደዱ ዘንድ፥ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁም ብቷደዱ፥ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ሁሉ ያውቋችኋል።” ስምዖን ጴጥሮስም፥ “ጌታ ሆይ፥ ወዴት ትሄዳለህ?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ ኋላ ግን ትከተለኛለህ” አለው። ጴጥሮስም፥ “ጌታ ሆይ፥ ስለ ምን አሁን ልከተልህ አልችልም? እኔ ነፍሴንም እንኳ ቢሆን ስለ አንተ አሳልፌ እሰጣለሁ” አለው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ነፍስህን ስለ እኔ አሳልፈህ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ዶሮ አይጮህም።
ዮሐንስ 13:31-38 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይሁዳ ከወጣ በኋላ፣ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ፤ በእርሱም እግዚአብሔር ከበረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእርሱ ከከበረ፣ እግዚአብሔር ልጁን በራሱ ዘንድ ያከብረዋል፤ ወዲያውም ያከብረዋል። “ልጆቼ ሆይ፤ ከእናንተ ጋር የምቈየው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድ፣ ‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ እንዳልኋቸው፣ አሁንም ለእናንተ ይህንኑ እላችኋለሁ። “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” ስምዖን ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ የምትሄደው ወዴት ነው?” አለው። ኢየሱስም፣ “ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ ኋላ ግን ትከተለኛለህ” ሲል መለሰለት። ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አሁን ልከተልህ የማልችለው ለምንድን ነው? ስለ አንተ ሕይወቴንም ቢሆን አሳልፌ እሰጣለሁ” አለው። ኢየሱስም፣ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሕይወትህን በርግጥ ለእኔ አሳልፈህ ትሰጣለህን? እውነት እልሃለሁ፤ ዶሮ ሳይጮኸ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ።
ዮሐንስ 13:31-38 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከወጣም በኋላ ኢየሱስ እንዲ አለ፦ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ እግዚአብሔርም ሰለ እርሱ ከበረ፤ እግዚአብሔር ስለ እርሱ የከበረ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን ራሱን ያከብረዋል ወዲያውም ያከብረዋል። ልጆች ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁዳም፦ ‘እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፥ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ።’ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” ስምዖን ጴጥሮስም፦ “ጌታ ሆይ፥ ወዴት ትሄዳለህ?” አለው። ኢየሱስም፦ “ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፥ ነገር ግን በኋላ ትከተለኛለህ” ብሎ መለሰለት። ጴጥሮስም፦ “ጌታ ሆይ፥ አሁን ልከተልህ አለመቻሌ ስለ ምንድር ነው? ነፍሴን ስንኳ ስለ አንተ እሰጣለሁ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ “ነፍስህን ስለ እኔ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዶሮ አይጮኽም።
ዮሐንስ 13:31-38 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይሁዳ ወጥቶ ከሄደ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አሁን የሰው ልጅ ከብሮአል፤ በእርሱም አማካይነት እግዚአብሔር ከብሮአል፤ እግዚአብሔር በእርሱ አማካይነት ከከበረ እግዚአብሔርም እርሱን ያከብረዋል፤ ሳይዘገይም ያከብረዋል። ልጆቼ ሆይ፥ ከእናንተ ጋር ብዙ ጊዜ አልቆይም፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድ ባለሥልጣኖች ‘እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም’ እንዳልኳቸው፥ አሁንም ለእናንተ እንዲሁ እላችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በእርሳችሁ ከተዋደዳችሁ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ ሰው ሁሉ ያውቃል።” ከዚህ በኋላ ስምዖን ጴጥሮስ ኢየሱስን፥ “ጌታ ሆይ! ወዴት ነው የምትሄደው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም “እኔ ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ በኋላ ግን ትከተለኛለህ” ሲል መለሰለት። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ስለምን አሁን ልከተልህ አልችልም? እኔ ሕይወቴን እንኳ ስለ አንተ አሳልፌ እሰጣለሁ” አለው። ኢየሱስም “አንተ ሕይወትህን ስለ እኔ አሳልፈህ ትሰጣለህን? እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ዶሮ ከመጮሁ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ሲል መለሰ።
ዮሐንስ 13:31-38 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከወጣም በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አሁን የሰው ልጅ ከብሯል፤ በእርሱም እግዚአብሔር ከብሯል፤ እግዚአብሔር ስለ እርሱ የከበረ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን ራሱን ያከብረዋል፤ ወዲያውም ያከብረዋል። ልጆች ሆይ! ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድም ‘እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም፤’ እንዳልኋቸው፥ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ። አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እርሱም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋድዱ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ወዴት ትሄዳለህ?” አለው። ኢየሱስም “ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፥ ነገር ግን በኋላ ትከተለኛለህ” ብሎ መለሰለት። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! አሁን ልከተልህ የማልችለው በምን ምክንያት ነው? ነፍሴን እንኳ ስለ አንተ እሰጣለሁ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰለት “ነፍስህን ስለ እኔ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዶሮ አይጮኽም።”