ዮሐንስ 13:12-18
ዮሐንስ 13:12-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግራቸውንም ካጠባቸው በኋላ ልብሱን አንሥቶ ለበሰና እንደ ገና ከእነርሱ ጋር ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፥ “ያደረግሁላችሁን ዐወቃችሁን? እናንተ ‘መምህራችን፥ ጌታችንም’ ትሉኛላችሁ፤ መልካም ትላላችሁ፤ እኔ እንዲሁ ነኝና። እንግዲህ እኔ መምህራችሁና ጌታችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኋችሁ እናንተም እንዲሁ የባልጀሮቻችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል። እኔ እንደ አደረግሁላችሁ እናንተም ልታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከጌታው የሚበልጥ አገልጋይ የለም፤ ከላከው የሚበልጥ መልእክተኛም የለም። ይህንም ዐውቃችሁ ብትሠሩ ብፁዓን ናችሁ። ነገር ግን ይህን የምናገር ስለ ሁላችሁ አይደለም፤ የመረጥኋቸው እነማን እንደ ሆኑ እኔ አውቃለሁ፤ ነገር ግን መጽሐፍ ‘እንጀራዬን የሚመገብ ተረከዙን በእኔ ላይ አነሣ’ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው።
ዮሐንስ 13:12-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግራቸውን ዐጥቦ ካበቃ በኋላም፣ ልብሱን ለብሶ ተመልሶ በቦታው ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ፣ ‘መምህርና፣ ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ ትክክል ነው፤ እንደምትሉኝ እንዲሁ ነኝና። እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተም እንደዚሁ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል። እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ ምሳሌ ትቼላችኋለሁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ባሪያ ከጌታው፣ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። እንግዲህ እነዚህን ነገሮች ዐውቃችሁ ብትፈጽሙ ትባረካላችሁ። “ስለ ሁላችሁ መናገሬ አይደለም፤ የመረጥኋቸውን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን፣ ‘እንጀራዬን የሚበላ ተረከዙን አነሣብኝ’ የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው።
ዮሐንስ 13:12-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው፦ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ። ስለ ሁላችሁ አልናገርም፤ እኔ የመረጥኋቸውን አውቃለሁ፤ ነገር ግን መጽሐፍ፦ ‘እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ’ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው።
ዮሐንስ 13:12-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግራቸውን ካጠበ በኋላ ልብሱን ለበሰና ወደ ቦታው ተመልሶ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ምን እንዳደረግሁላችሁ አስተዋላችሁን? እናንተ ‘መምህርና ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ እኔ መምህርና ጌታ ስለ ሆንኩ ያላችሁት ትክክል ነው። እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን መተጣጠብ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁት እናንተም እንድታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላኪው አይበልጥም። ይህን ነገር ብታውቁና በሥራ ላይ ብታውሉት የተባረካችሁ ናችሁ። ይህን የምናገረው ስለ ሁላችሁም አይደለም፤ እኔ የመረጥኳችሁን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ‘እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ በጠላትነት ተነሣብኝ’ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል መፈጸም አለበት።
ዮሐንስ 13:12-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ ስለሆንኩም መልካም ትናገራላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተም እንዲሁ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ ይህንን ስታውቁና ስታደርጉ ብፁዓን ናችሁ። ስለ ሁላችሁም አይደለም የምናገረው፤ እኔ የመረጥኋቸውን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ቅዱስ መጽሐፍ ‘እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ’ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው።