ዮሐንስ 12:20-26
ዮሐንስ 12:20-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከጽርዕ ሰዎችም ይሰግዱ ዘንድ ለበዓል የወጡ ነበሩ። እነርሱም ከገሊላ፥ የቤተ ሳይዳ ሰው ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ሄደው፥ “አቤቱ፥ ጌታ ኢየሱስን ልናየው እንወድዳለን” ብለው ለመኑት። ፊልጶስም ሄዶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስም ሄደው ለጌታችን ለኢየሱስ ነገሩት። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁን የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ጊዜው ደረሰ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በምድር ላይ ካልወደቀችና ካልሞተች ብቻዋን ትኖራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ፍሬን ታፈራለች። ነፍሱን የሚወዳት ይጥላታል፤ በዚህ ዓለም ነፍሱን የሚጥላትም ለዘለዓለም ሕይወት ይጠብቃታል። እኔን የሚያገለግለኝ ካለ ይከተለኝ፤ የሚያገለግለኝ እኔ ባለሁበት በዚያ ይኖራልና፤ እኔን የሚያገለግለኝንም አብ ያከብረዋል።
ዮሐንስ 12:20-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ለአምልኮ ወደ በዓሉ ከወጡት መካከል የግሪክ ሰዎችም ነበሩ። እነርሱም በገሊላ ከምትገኘው ከቤተ ሳይዳ ወደ ሆነው ሰው፣ ወደ ፊልጶስ መጥተው፣ “ጌታው፤ እባክህን፣ ኢየሱስን ለማየት እንፈልጋለን” አሉት። ፊልጶስም፤ ለእንድርያስ ሊነግረው ሄደ፤ እንድርያስና ፊልጶስም ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የሰው ልጅ የሚከብርበት ሰዓቱ ደርሷል፤ እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ሕይወቱን የሚወድድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝንም አባቴ ያከብረዋል።
ዮሐንስ 12:20-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በበዓሉም ሊሰግዱ ከመጡት አንዳንዶቹ የግሪክ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ከገሊላ ቤተ ሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው፦ “ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን” ብለው ለመኑት። ፊልጶስም መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል፦ “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፥ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል።
ዮሐንስ 12:20-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በበዓሉ ጊዜ ሊሰግዱ ወደ ኢየሩሳሌም ከሄዱት ሰዎች መካከል፥ አንዳንድ ግሪኮች ይገኙ ነበር። እነርሱም ከገሊላ የቤተ ሳይዳ ሰው ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ቀርበው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ ኢየሱስን ማየት እንፈልጋለን” አሉት። ፊልጶስም ሄዶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ አብረው ሄደው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እነሆ፥ የሰው ልጅ የሚከበርበት ሰዓት ደርሶአል፤ እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በመሬት ወድቃ ካልሞተች፥ ብቻዋን ትቀራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ታፈራለች። ሕይወቱን የሚወድ ያጠፋታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘለዓለም ሕይወት ይጠብቃታል። እኔን ማገልገል የሚፈልግ ይከተለኝ፤ እኔ ባለሁበት አገልጋዬ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝንም አብ ያከብረዋል።”
ዮሐንስ 12:20-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በበዓሉም ሊሰግዱ ከመጡት አንዳንዶቹ የግሪክ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ከገሊላ ቤተሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው “ጌታ ሆይ! ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን፤” ብለው ለመኑት። ፊልጶስም መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስ ስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፤ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘለዓለም ሕይወት ይጠብቃታል። የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል።