የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዮሐንስ 11:7-54

ዮሐንስ 11:7-54 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚ​ህም በኋላ፥ ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱን፥ “ኑ፥ ወደ ይሁዳ ሀገር ደግሞ እን​ሂድ” አላ​ቸው። ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም፥ “መም​ህር ሆይ፥ አይ​ሁድ ሊወ​ግ​ሩህ ይሹ አል​ነ​በ​ረ​ምን? ዛሬ ደግሞ አንተ ወደ​ዚያ ልት​ሄድ ትሻ​ለ​ህን?” አሉት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ቀኑ ዐሥራ ሁለት ሰዓት አይ​ደ​ለ​ምን? በቀን የሚ​ሄድ አይ​ሰ​ና​ከ​ልም፤ የዚ​ህን ዓለም ብር​ሃን ያያ​ልና። በሌ​ሊት የሚ​ሄድ ግን ይሰ​ነ​ካ​ከ​ላል፤ በው​ስጡ የሚ​ያ​የው ብር​ሃን የለ​ምና።” ይህ​ንም ለደቀ መዛ​ሙ​ርቱ ነገ​ራ​ቸው፤ ከዚ​ህም በኋላ፥ “ወዳ​ጃ​ችን አል​ዓ​ዛር ተኝ​ቶ​አል፤ ነገር ግን ላነ​ቃው እሄ​ዳ​ለሁ” አላ​ቸው። ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም፥ “አቤቱ፥ ከተ​ኛስ ይነ​ቃል፤ ይድ​ና​ልም” አሉት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ስለ ሞቱ ተና​ገረ፤ እነ​ርሱ ግን ስለ እን​ቅ​ልፍ መተ​ኛት መስ​ሎ​አ​ቸው ነበር። ከዚህ በኋ​ላም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ገልጦ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “አል​ዓ​ዛር ሞተ። ታም​ኑም ዘንድ እኔ በዚያ ባለ​መ​ኖሬ ስለ እና​ንተ ደስ ይለ​ኛል፤ ነገር ግን ኑ፥ ወደ እርሱ እን​ሂድ።” ዲዲ​ሞስ የሚ​ሉት ቶማ​ስም፥ ባል​ን​ጀ​ሮ​ቹን ደቀ መዛ​ሙ​ርት፥ “እኛም ከእ​ርሱ ጋር እን​ሞት ዘንድ እን​ሂድ” አላ​ቸው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ወደ ቢታ​ንያ ሄደ፤ ከዚ​ያም በደ​ረሰ ጊዜ ከተ​ቀ​በረ አራት ቀን ሆኖት አገ​ኘው። ቢታ​ን​ያም ለኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ዐሥራ አም​ስት ምዕ​ራፍ ያህል ቅርብ ነበ​ረች። ከአ​ይ​ሁ​ድም ስለ ወን​ድ​ማ​ቸው ሊያ​ጽ​ና​ኑ​አ​ቸው ወደ ማር​ያ​ምና ወደ ማርታ የሄዱ ብዙ​ዎች ነበሩ። ማር​ታም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ እንደ መጣ በሰ​ማች ጊዜ ወጥታ ተቀ​በ​ለ​ችው፤ ማር​ያም ግን በቤት ተቀ​ምጣ ነበር። ማር​ታም ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን እን​ዲህ አለ​ችው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኖረህ ቢሆን ወን​ድሜ ባል​ሞ​ተም ነበር። አሁ​ንም ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የም​ት​ለ​ም​ነ​ውን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲ​ሰ​ጥህ አው​ቃ​ለሁ።” ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ወን​ድ​ም​ሽስ ይነ​ሣል” አላት። ማር​ታም፥ “ሙታን በሚ​ነ​ሡ​ባት በኋ​ለ​ኛ​ዪቱ ቀን እን​ደ​ሚ​ነሣ አው​ቃ​ለሁ” አለ​ችው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም አላት፥ “ትን​ሣ​ኤና ሕይ​ወት እኔ ነኝ፤ የሚ​ያ​ም​ን​ብኝ ቢሞ​ትም ይነ​ሣል። ሕያው የሆነ የሚ​ያ​ም​ን​ብ​ኝም ሁሉ ለዘ​ለ​ዓ​ለም አይ​ሞ​ትም፤ ይህ​ንስ ታም​ኛ​ለ​ሽን?” እር​ስ​ዋም፥ “አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ወደ ዓለም የሚ​መ​ጣው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅ ክር​ስ​ቶስ እንደ ሆንህ እኔ አም​ና​ለሁ” አለ​ችው። ይህ​ንም ብላ ሄደች፤ እኅ​ቷን ማር​ያ​ም​ንም ቀስ ብላ ጠራ​ችና፥ “እነሆ፥ መም​ህ​ራ​ችን መጥቶ ይጠ​ራ​ሻል” አለ​ቻት። እር​ስ​ዋም ይህን በሰ​ማች ጊዜ ፈጥና ተነ​ሣች፤ ወደ እር​ሱም ሄደች። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ማርታ በተ​ቀ​በ​ለ​ች​በት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መን​ደር አል​ገ​ባም ነበር። ሊያ​ጽ​ና​ኑ​አት መጥ​ተው በቤት ከእ​ር​ስዋ ጋር የነ​በሩ አይ​ሁ​ድም ፈጥና ተነ​ሥታ እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ በዚያ ለወ​ን​ድ​ምዋ ልታ​ለ​ቅስ ወደ መቃ​ብሩ የም​ት​ሄድ መስ​ሎ​አ​ቸው ተከ​ተ​ሉ​አት። ማር​ያ​ምም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ወደ አለ​በት ስፍራ ደረ​ሰ​ችና በአ​የ​ችው ጊዜ ከእ​ግሩ በታች ሰግዳ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኑረህ ቢሆን ወን​ድሜ ባል​ሞ​ተም ነበር” አለ​ችው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም እር​ስዋ ስታ​ለ​ቅስ፥ ከእ​ር​ስዋ ጋር የመጡ አይ​ሁ​ድም ሲያ​ለ​ቅሱ ባየ ጊዜ በልቡ አዘነ፤ በራ​ሱም ታወከ። እር​ሱም፥ “የት ቀበ​ራ​ች​ሁት?” አለ፤ እነ​ር​ሱም፥ “አቤቱ፥ መጥ​ተህ እይ” አሉት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም እን​ባ​ውን አፈ​ሰሰ። አይ​ሁ​ድም፥ “ምን ያህል ይወ​ደው እንደ ነበር እዩ” አሉ። ከእ​ነ​ር​ሱም መካ​ከል፥ “ዕዉር ሆኖ የተ​ወ​ለ​ደ​ውን ዐይን ያበ​ራው ይህ ሰው ይህስ እን​ዳ​ይ​ሞት ሊያ​ደ​ርግ ባል​ቻ​ለም ነበ​ርን?” ያሉ ነበሩ። ዳግ​መ​ኛም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ በልቡ አዘነ፤ ወደ መቃ​ብ​ሩም ሄደ፤ መቃ​ብ​ሩም ዋሻ ነበር፤ በላ​ዩም ታላቅ ድን​ጋይ ተገ​ጥ​ሞ​በት ነበር። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ድን​ጋ​ዩን አንሡ” አላ​ቸው፤ የሟቹ እኅት ማር​ታም፥ “ጌታዬ ሆይ፥ አራት ቀን ሆኖ​ታ​ልና ፈጽሞ ሸትቶ ይሆ​ናል” አለ​ችው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ብታ​ም​ናስ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ክብር ታያ​ለሽ አላ​ል​ሁ​ሽም ነበ​ርን?” አላት። ድን​ጋ​ዩ​ንም አነሡ፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ዐይ​ኖ​ቹን አቅ​ንቶ እን​ዲህ አለ፥ “አባት ሆይ፥ ሰም​ተ​ኸ​ኛ​ልና አመ​ሰ​ግ​ን​ሃ​ለሁ። እኔም ዘወ​ትር እን​ደ​ም​ት​ሰ​ማኝ አው​ቃ​ለሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክ​ኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ቆመው ስላ​ሉት ሰዎች ይህን እና​ገ​ራ​ለሁ።” ይህ​ንም ብሎ በታ​ላቅ ቃል ጮኸና፥ “አል​ዓ​ዛር፥ ና፤ ወደ ውጭ ውጣ” አለ። ሞቶ የነ​በ​ረ​ውም እንደ ተገ​ነዘ፥ እጁ​ንና እግ​ሩ​ንም እንደ ታሰረ፥ ፊቱም በሰ​በን እንደ ተጠ​ቀ​ለለ ወጣ፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “እን​ግ​ዲ​ህስ ፍቱ​ትና ተዉት ይሂድ” አላ​ቸው። ስለ​ዚህ ከአ​ይ​ሁ​ድም ወደ ማር​ታና ወደ ማር​ያም መጥ​ተው የነ​በሩ ብዙ ሰዎች ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ያደ​ረ​ገ​ውን አይ​ተው በእ​ርሱ አመኑ። ከእ​ነ​ር​ሱም መካ​ከል ወደ ፈሪ​ሳ​ው​ያን ሄደው የከ​ሰ​ሱት ነበሩ፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ያደ​ረ​ገ​ው​ንም ሁሉ ነገ​ሩ​አ​ቸው። የካ​ህ​ናት አለ​ቆ​ችና ፈሪ​ሳ​ው​ያ​ንም ጉባ​ኤ​ውን ሰብ​ስ​በው እን​ዲህ አሉ​አ​ቸው፥ “እነሆ፥ ይህ ሰው ብዙ ተአ​ም​ራት ያደ​ር​ጋል፤ ምን እና​ድ​ርግ? እን​ዲሁ ብን​ተ​ወ​ውም ሁሉ ያም​ኑ​በ​ታል፤ የሮም ሰዎ​ችም መጥ​ተው ሀገ​ራ​ች​ን​ንና ወገ​ና​ች​ንን ይወ​ስ​ዱ​ብ​ናል።” በዚ​ያ​ችም ዓመት የካ​ህ​ናት አለቃ የነ​በ​ረው ስሙ ቀያፋ የተ​ባ​ለው ከእ​ነ​ርሱ አንዱ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እና​ን​ተስ ምንም አታ​ው​ቁም። ምንም አት​መ​ክ​ሩም፤ ሕዝቡ ሁሉ ከሚ​ጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ይሻ​ለ​ናል።” ይህ​ንም ከልቡ የተ​ና​ገ​ረው አይ​ደ​ለም፤ ነገር ግን በዚ​ያች ዓመት የካ​ህ​ናት አለቃ ነበ​ርና ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ስለ ሕዝብ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ይሞት ዘንድ ስላ​ለው ይህን ትን​ቢት ተና​ገረ። ስለ ሕዝብ ብቻ አል​ነ​በ​ረም፤ የተ​በ​ተ​ኑ​ትን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ልጆች በአ​ን​ድ​ነት ይሰ​በ​ስ​ባ​ቸው ዘንድ ነው እንጂ። ከዚ​ያ​ችም ቀን ጀምሮ የካ​ህ​ናት አለ​ቆች ሊገ​ድ​ሉት ተማ​ከሩ። ከዚ​ያም ወዲያ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ በአ​ይ​ሁድ መካ​ከል በግ​ልጥ አል​ተ​መ​ላ​ለ​ሰም፤ ነገር ግን ለም​ድረ በዳ አቅ​ራ​ቢያ ወደ ሆነች ምድር፥ ኤፍ​ሬም ወደ​ም​ት​ባል ከተማ ሄደ፤ በዚ​ያም ከደቀ መዛ​ሙ​ርቱ ጋር ተቀ​መጠ።

ዮሐንስ 11:7-54 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ወደ ይሁዳ እንመለስ” አላቸው። እነርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ ከጥቂት ጊዜ በፊት አይሁድ በድንጋይ ሊወግሩህ እየፈለጉህ ነበር፤ እንደ ገና ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ቀኑ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ብርሃን አይደለምን? ከዚህ ዓለም ብርሃን የተነሣ ስለሚያይ በቀን የሚመላለስ አይሰናከልም፤ የሚሰናከለው ግን በሌሊት የሚመላለስ ነው፤ ብርሃን የለውምና።” ይህን ከነገራቸው በኋላ፣ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ እኔም ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ጌታ ሆይ፤ ተኝቶ ከሆነስ ይድናል” አሉት። ኢየሱስ ይህን የነገራቸው ስለ ሞቱ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን እንቅልፍ ስለ መተኛቱ የተናገረ መሰላቸው። ስለዚህም በግልጽ እንዲህ አላቸው፤ “አልዓዛር ሞቷል፤ ታምኑ ዘንድ፣ በዚያ ባለ መኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ አሁን ግን ወደ እርሱ እንሂድ።” ከዚያም ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ለተቀሩት ደቀ መዛሙርት፣ “እኛም ሄደን ከእርሱ ጋር እንሙት” አላቸው። ኢየሱስ ሲደርስ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ቢታንያ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ትርቅ ነበር። ብዙዎች አይሁድም ማርታንና ማርያምን ስለ ወንድማቸው ሞት ሊያጽናኗቸው መጥተው ነበር፤ ማርታ የኢየሱስን መምጣት ሰምታ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ቀርታ ነበር። ማርታም ኢየሱስን እንዲህ አለችው፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር። አሁንም ቢሆን የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ።” ኢየሱስም፣ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት። ማርታም፣ “በመጨረሻው ቀን፣ በትንሣኤ እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በእኔ የሚኖር፣ የሚያምንብኝም ከቶ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽን?” እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። ይህን ካለች በኋላ፣ ተመልሳ እኅቷን ማርያምን ለብቻዋ ጠርታ፣ “መምህሩ መጥቷል፤ ይፈልግሻልም” አለቻት። ማርያምም ይህን እንደ ሰማች፣ ፈጥና ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ቦታ ነበር እንጂ፣ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር። ማርያምን ሲያጽናኑ በቤት ውስጥ የነበሩ አይሁድም፣ ብድግ ብላ መውጣቷን ሲያዩ፣ ወደ መቃብሩ ሄዳ የምታለቅስ መስሏቸው ተከተሏት። ማርያምም ኢየሱስ ወደ ነበረበት ቦታ ደርሳ እንዳየችው፣ እግሩ ላይ ተደፍታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው። ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ፣ ተከትለዋትም የመጡት አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ መንፈሱ በሐዘን ታውኮ፣ “የት ነው ያኖራችሁት?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ መጥተህ እይ” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። አይሁድም፣ “እንዴት ይወድደው እንደ ነበር አያችሁ” አሉ። ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን፣ “የዐይነ ስውሩን ዐይን የከፈተ፣ ይህም ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበር?” አሉ። ኢየሱስ ልቡ ዳግመኛ በሐዘን ተነክቶ ወደ መቃብሩ መጣ፤ መቃብሩም በድንጋይ የተገጠመ ዋሻ ነበር፤ እርሱም፣ “ድንጋዩን አንሡት” አለ። የሟቹም እኅት ማርታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሁንማ አራት ቀን ስለ ቈየ ይሸታል” አለችው። ኢየሱስም፣ “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርሁሽም?” አላት። ስለዚህ ድንጋዩን አነሡ። ኢየሱስም ወደ ላይ ተመልክቶ አንዲህ አለ፤ “አባት ሆይ፤ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ይህን መናገሬ ግን በዚህ የቆሙ ሰዎች አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ ነው።” ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ በታላቅ ድምፅ፣ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” ብሎ ተጣራ። የሞተውም ሰው እጅና እግሩ በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ፣ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ። ኢየሱስም “መግነዙን ፍቱለትና ይሂድ” አላቸው። ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፣ ኢየሱስ ያደረገውን ካዩት አይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ። አንዳንዶቹ ግን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ለፈሪሳውያን ተናገሩ፤ ከዚያም የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የአይሁድን ሸንጎ ስብሰባ ጠሩ። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው ብዙ ታምራዊ ምልክቶችን እያደረገ ስለሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል? እንዲሁ ብንተወው ሰው ሁሉ በእርሱ ያምናል፤ ሮማውያንም መጥተው ስፍራችንንና ሕዝባችንን ይወስዱብናል።” ከመካከላቸውም አንዱ፣ በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እናንተ እኮ ምንም አታውቁም! ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት የሚሻል መሆኑን አታስተውሉም።” ይህን ያለው ከራሱ አልነበረም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት እንደ መሆኑ፣ ኢየሱስ ለአይሁድ ሕዝብ እንደሚሞት ትንቢት መናገሩ ነበር፤ ለዚያም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች በአንድነት ለመሰብሰብ ነው። ከዚያን ቀን ጀምሮም፣ ሊገድሉት አሤሩ። ስለዚህ ኢየሱስ ከዚያ ወዲያ በአይሁድ መካከል በይፋ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን በምድረ በዳ አጠገብ ወደምትገኝ ኤፍሬም ወደ ተባለች መንደር ገለል አለ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሰነበተ።

ዮሐንስ 11:7-54 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ፦ “ወደ ይሁዳ ደግሞ እንሂድ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ፦ “መምህር ሆይ፥ አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፥ ደግሞም ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ፦ “ቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ ቢኖር የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል” አላቸው። ከዚህም በኋላ፦ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አላቸው። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ፦ “ጌታ ሆይ፥ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል” አሉት። ኢየሱስስ ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት እንደ ተናገረ መሰላቸው። እንግዲህ ያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጥ፦ “አልዓዛር ሞተ፤ እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ” አላቸው። ስለዚህ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ለባልንጀሮቹ ለደቀ መዛሙርቱ፦ “ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ” አለ። ኢየሱስም በመጣ ጊዜ በመቃብር እስከ አሁን አራት ቀን ሆኖት አገኘው። ቢታንያም አሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም፦ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት። ማርታም፦ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም፦ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝ ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርስዋም፦ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ፦ “መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል” አለቻት። እርስዋም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ሲያጽናኑአት ከእርስዋ ጋር በቤት የነበሩ አይሁድም ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ “ወዴት አኖራችሁት?” አለም። እነርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ መጥተህ እይ” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህ አይሁድ፦ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ” አሉ። ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ፦ “ይህ የዕውሩን ዓይኖች የከፈተ ይህን ደግሞ እንዳይሞት ያደርግ ዘንድ ባልቻለም ነበርን?” አሉ። ኢየሱስም በራሱ አዝኖ ወደ መቃብሩ መጣ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ኢየሱስ፦ “ድንጋዩን አንሡ” አለ። የሞተውም እኅት ማርታ፦ “ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል” አለችው። ኢየሱስ፦ “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን?” አላት። ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ፦ “አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ” አለ። ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ፦ “አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና” ብሎ ጮኸ። የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም፦ “ፍቱትና ይሂድ ተዉት” አላቸው። ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሩአቸው። እንግዲህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ሸንጎ ሰብስበው፦ “ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋል። እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ” አሉ። በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ፦ “እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም” አላቸው። ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፥ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፥ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ። እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ። ከዚያ ወዲያም ኢየሱስ በአይሁድ መካከል ተገልጦ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ከዚያ በምድረ በዳ አጠገብ ወዳለች ምድር፥ ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ።

ዮሐንስ 11:7-54 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፥ “ወደ ይሁዳ ምድር እንደገና እንሂድ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “መምህር ሆይ! አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፤ ታዲያ እንደገና ወደዚያ ተመልሰህ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በቀን ውስጥ ያለው ጊዜ ዐሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ የዚህን ዓለም ብርሃን ስለሚያይ አይሰናከልም። ነገር ግን በሌሊት የሚመላለስ ብርሃን ስለሌለው ይሰናከላል።” ኢየሱስ ይህን ካላቸው በኋላ፥ “ወዳጃችን አልዓዛር አንቀላፍቶአል፤ እኔ ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አለ። ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! አንቀላፍቶስ ከሆነ ይሻለዋል ማለት ነው” አሉት። ኢየሱስ ይህን የተናገረው ስለ አልዓዛር መሞት ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ የተናገረ መስሎአቸው ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በግልጥ እንዲህ አላቸው፦ “አልዓዛር ሞቶአል፤ እናንተ እንድታምኑ እዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ብሎኛል፤ አሁን ግን ወደ እርሱ እንሂድ።” በዚህ ጊዜ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ሌሎቹን ደቀ መዛሙርት፥ “ከእርሱ ጋር እንድንሞት እኛም እንሂድ” አላቸው። ኢየሱስ እዚያ በደረሰ ጊዜ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት አገኘው። ቢታንያ ከኢየሩሳሌም የምትርቀው ሦስት ኪሎ ሜትር ያኽል ነው። ከአይሁድም ብዙዎች ማርታንና ማርያምን ስለ ወንድማቸው ሞት ለማጽናናት ወደ እነርሱ መጥተው ነበር። ማርታ የኢየሱስን መምጣት በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ቀርታ ነበር። ማርታ ኢየሱስን፥ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፥ ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ ነገር ግን አሁንም የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ እንደገና ከሞት ይነሣል” አላት። ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ ጊዜ ከሞት እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በሕይወት የሚኖርና በእኔም የሚያምን ሁሉ ፈጽሞ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽ?” አላት። እርስዋም “አዎ ጌታ ሆይ! አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። ማርታ ይህን ከተናገረች በኋላ ሄደችና እኅትዋን ማርያምን “መምህር መጥቶአል፤ አንቺንም ይጠራሻል” ብላ በስውር ጠራቻት። ማርያም ይህን በሰማች ጊዜ በፍጥነት ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች። ያን ጊዜ ኢየሱስ ማርታ እርሱን ባገኘችበት ስፍራ ነበር እንጂ ወደ መንደር ገና አልገባም ነበር። እርስዋን ለማጽናናት መጥተው በቤት ውስጥ አብረዋት የነበሩ አይሁድ ማርያም በፍጥነት ተነሥታ ስትወጣ አይተው ወደ አልዓዛር መቃብር ሄዳ የምታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያም ኢየሱስ ወደ ነበረበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ሥር ወደቀችና “ጌታ ሆይ፥ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። ኢየሱስ እርስዋ ስታለቅስና አብረዋት የመጡትም አይሁድ ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ በመንፈሱ እጅግ አዝኖ በመታወክ፥ “የት ነው የቀበራችሁት?” አለ። እነርሱም “ጌታ ሆይ! ና እይ” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህ አይሁድ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ ተመልከቱ” አሉ። ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን፥ “የዕውርን ዐይኖች ያበራ፥ ይህ ሰው እንዳይሞት ሊያደርግ አይችልም ነበርን?” አሉ። ኢየሱስ በጣም እያዘነ ወደ መቃብሩ ሄደ፤ መቃብሩ በድንጋይ የተዘጋ ዋሻ ነበር። ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሡት” አለ። የሟቹ እኅት ማርታ፥ “ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታል፤ አሁን ይሸታል” አለችው። ኢየሱስም “ካመንሽ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብዬሽ አልነበረምን?” አላት። ሰዎቹም ድንጋዩን አነሡት፤ ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ላይ ተመልክቶ፥ “አባት ሆይ! ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ይህን ያልኩት፥ እዚህ የቆሙት ሰዎች አንተ እንደ ላክኸኝ እንዲያምኑ ብዬ ነው” አለ። ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ “አልዓዛር! ና ውጣ!” ብሎ በታላቅ ድምፅ ተናገረ። ሟቹ አልዓዛርም እጆቹና እግሮቹ በመገነዣ እንደ ተገነዙ ከመቃብሩ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር፤ ኢየሱስም “ፍቱትና ተዉት ይሂድ!” አላቸው። ማርያምን ለማጽናናት መጥተው ከነበሩት አይሁድ ብዙዎቹ ያደረገውን አይተው በኢየሱስ አመኑ። አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሩአቸው። ስለዚህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የሸንጎውን አባሎች ሰብስበው እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው ብዙ ተአምራት ስለሚያደርግ ምን ብናደርግ ይሻላል? እንዲሁ ብንተወው ሰው ሁሉ በእርሱ ያምናል፤ ሮማውያንም መጥተው ቤተ መቅደሳችንንና ሕዝባችንን ሁሉ ይደመስሳሉ።” ነገር ግን ከእነርሱ አንዱ በዚያን ዓመት የካህናት አለቃ የነበረው ቀያፋ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝብ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝብ ቢሞት ለእናንተ የሚሻል መሆኑን ከቶ አልተገነዘባችሁምን?” እርሱም ይህን የተናገረው፥ ከራሱ አመንጭቶ አልነበረም፤ ነገር ግን በዚያን ዓመት እርሱ የካህናት አለቃ ስለ ነበረ፥ ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ መሞት እንደሚገባው ሲያመለክት ይህን ትንቢት ተናገረ። የሚሞተውም ስለ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን፥ የተበተኑትንም የእግዚአብሔርን ልጆች በአንድነት ለመሰብሰብ ነው። ስለዚህ ከዚያ ቀን ጀምሮ ኢየሱስን ለመግደል ተማከሩ። ከዚያን ወዲያ ኢየሱስ በአይሁድ መካከል በግልጥ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ከዚያ ወጥቶ በበረሓ አጠገብ ወዳለችው ኤፍሬም ወደምትባለው ከተማ ሄደ፤ እዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቈየ።

ዮሐንስ 11:7-54 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ ይሁዳ እንደገና እንሂድ፤” አላቸው። ደቀመዛሙርቱ “መምህር ሆይ! አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፤ በድጋሚ ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ “በቀን ውስጥ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ይገኙ የለምን? በቀን የሚመላለስ የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል፤” አላቸው። ይህንንም ከተናገረ በኋላ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ፤” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! ተኝቶ እንደ ሆነስ ይድናል፤” አሉት። ኢየሱስ ግን ስለ ሞቱ ነበር የተናገረው፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ የተናገረ መሰላቸው። እንግዲህ ያንጊዜ ኢየሱስ በግልጥ “አልዓዛር ሞተ፤ እናንተ እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ፤” አላቸው። ዲዲሞስ የሚሉትም ቶማስ ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርት “ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛም እንሂድ፤” አለ። ኢየሱስም በመጣ ጊዜ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ቢታንያም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። ማርታም ኢየሱስ እንደመጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሣል፤” አላት። ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሣ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነና በእኔ የሚያምን ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ “መምህር መጥቷል፤ እየጠራሽም ነው፤” አለቻት። እርሷም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፥ ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ከእርሷ ጋር በቤት ሲያጽናኑአት የነበሩ አይሁድም፥ ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤” አለችው። ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ ከእርሷም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ “ወዴት አኖራችሁት?” ዓለም። እነርሱም “ጌታ ሆይ! መጥተህ እይ፤” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህም አይሁድ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ፤” አሉ። ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ “የዐይነ ሥውሩን ዐይኖች እንደ ከፈተ ይህም ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበርን?” አሉ። ኢየሱስም በድጋሚ በጥልቅ ኀዘን ተውጦ ወደ መቃብሩ መጣ፤ መቃብሩም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሡ፤” አለ። የሞተውም ሰው እኅት ማርታ “ጌታ ሆይ! ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል፤” አለችው። ኢየሱስ “ካመንሽ የእግዚአብሔርን ክብር እንደምታዪ አልነገርሁሽምን?” አላት። ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዐይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ! ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ፤” ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ “አልዓዛር ሆይ! ና፥ ወደ ውጭ ውጣ፤” ብሎ ጮኸ። ሞቶ የነበረውም ሰው እጆቹና እግሮቹ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ። ኢየሱስም “ፍቱትና ይሂድ፤ ተዉት፤” አላቸው። ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሩአቸው። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ሸንጎ ሰብስበው እንዲህ አሉ፥ “ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶችን ያደርጋልና። እንዲሁ ብንተወው ሁሉም በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንንና ወገናችንንም ይወስዳሉ፤” በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ “እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንደሚሻል አታስቡም፤” አላቸው። ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፤ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ። እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ። ከዚያ ወዲያም ኢየሱስ በአይሁድ መካከል ተገልጦ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ከዚያ በምድረ በዳ አጠገብ ወዳለች ምድር፥ ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ።