ዮሐንስ 11:45-53
ዮሐንስ 11:45-53 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህ ከአይሁድም ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው የነበሩ ብዙ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ያደረገውን አይተው በእርሱ አመኑ። ከእነርሱም መካከል ወደ ፈሪሳውያን ሄደው የከሰሱት ነበሩ፤ ጌታችን ኢየሱስ ያደረገውንም ሁሉ ነገሩአቸው። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ጉባኤውን ሰብስበው እንዲህ አሉአቸው፥ “እነሆ፥ ይህ ሰው ብዙ ተአምራት ያደርጋል፤ ምን እናድርግ? እንዲሁ ብንተወውም ሁሉ ያምኑበታል፤ የሮም ሰዎችም መጥተው ሀገራችንንና ወገናችንን ይወስዱብናል።” በዚያችም ዓመት የካህናት አለቃ የነበረው ስሙ ቀያፋ የተባለው ከእነርሱ አንዱ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተስ ምንም አታውቁም። ምንም አትመክሩም፤ ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ይሻለናል።” ይህንም ከልቡ የተናገረው አይደለም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት የካህናት አለቃ ነበርና ጌታችን ኢየሱስ ስለ ሕዝብ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ይሞት ዘንድ ስላለው ይህን ትንቢት ተናገረ። ስለ ሕዝብ ብቻ አልነበረም፤ የተበተኑትን የእግዚአብሔርንም ልጆች በአንድነት ይሰበስባቸው ዘንድ ነው እንጂ። ከዚያችም ቀን ጀምሮ የካህናት አለቆች ሊገድሉት ተማከሩ።
ዮሐንስ 11:45-53 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፣ ኢየሱስ ያደረገውን ካዩት አይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ። አንዳንዶቹ ግን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ለፈሪሳውያን ተናገሩ፤ ከዚያም የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የአይሁድን ሸንጎ ስብሰባ ጠሩ። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው ብዙ ታምራዊ ምልክቶችን እያደረገ ስለሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል? እንዲሁ ብንተወው ሰው ሁሉ በእርሱ ያምናል፤ ሮማውያንም መጥተው ስፍራችንንና ሕዝባችንን ይወስዱብናል።” ከመካከላቸውም አንዱ፣ በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እናንተ እኮ ምንም አታውቁም! ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት የሚሻል መሆኑን አታስተውሉም።” ይህን ያለው ከራሱ አልነበረም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት እንደ መሆኑ፣ ኢየሱስ ለአይሁድ ሕዝብ እንደሚሞት ትንቢት መናገሩ ነበር፤ ለዚያም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች በአንድነት ለመሰብሰብ ነው። ከዚያን ቀን ጀምሮም፣ ሊገድሉት አሤሩ።
ዮሐንስ 11:45-53 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሩአቸው። እንግዲህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ሸንጎ ሰብስበው፦ “ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋል። እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ” አሉ። በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ፦ “እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም” አላቸው። ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፥ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፥ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ። እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ።
ዮሐንስ 11:45-53 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ማርያምን ለማጽናናት መጥተው ከነበሩት አይሁድ ብዙዎቹ ያደረገውን አይተው በኢየሱስ አመኑ። አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሩአቸው። ስለዚህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የሸንጎውን አባሎች ሰብስበው እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው ብዙ ተአምራት ስለሚያደርግ ምን ብናደርግ ይሻላል? እንዲሁ ብንተወው ሰው ሁሉ በእርሱ ያምናል፤ ሮማውያንም መጥተው ቤተ መቅደሳችንንና ሕዝባችንን ሁሉ ይደመስሳሉ።” ነገር ግን ከእነርሱ አንዱ በዚያን ዓመት የካህናት አለቃ የነበረው ቀያፋ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝብ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝብ ቢሞት ለእናንተ የሚሻል መሆኑን ከቶ አልተገነዘባችሁምን?” እርሱም ይህን የተናገረው፥ ከራሱ አመንጭቶ አልነበረም፤ ነገር ግን በዚያን ዓመት እርሱ የካህናት አለቃ ስለ ነበረ፥ ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ መሞት እንደሚገባው ሲያመለክት ይህን ትንቢት ተናገረ። የሚሞተውም ስለ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን፥ የተበተኑትንም የእግዚአብሔርን ልጆች በአንድነት ለመሰብሰብ ነው። ስለዚህ ከዚያ ቀን ጀምሮ ኢየሱስን ለመግደል ተማከሩ።
ዮሐንስ 11:45-53 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሩአቸው። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ሸንጎ ሰብስበው እንዲህ አሉ፥ “ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶችን ያደርጋልና። እንዲሁ ብንተወው ሁሉም በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንንና ወገናችንንም ይወስዳሉ፤” በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ “እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንደሚሻል አታስቡም፤” አላቸው። ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፤ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ። እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ።