ዮሐንስ 11:20-44
ዮሐንስ 11:20-44 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ማርታም ጌታችን ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ወጥታ ተቀበለችው፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ጌታችን ኢየሱስን እንዲህ አለችው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኖረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር። አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ።” ጌታችን ኢየሱስም፥ “ወንድምሽስ ይነሣል” አላት። ማርታም፥ “ሙታን በሚነሡባት በኋለኛዪቱ ቀን እንደሚነሣ አውቃለሁ” አለችው። ጌታችን ኢየሱስም አላት፥ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞትም ይነሣል። ሕያው የሆነ የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህንስ ታምኛለሽን?” እርስዋም፥ “አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅቷን ማርያምንም ቀስ ብላ ጠራችና፥ “እነሆ፥ መምህራችን መጥቶ ይጠራሻል” አለቻት። እርስዋም ይህን በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፤ ወደ እርሱም ሄደች። ጌታችን ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር። ሊያጽናኑአት መጥተው በቤት ከእርስዋ ጋር የነበሩ አይሁድም ፈጥና ተነሥታ እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ በዚያ ለወንድምዋ ልታለቅስ ወደ መቃብሩ የምትሄድ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ጌታችን ኢየሱስ ወደ አለበት ስፍራ ደረሰችና በአየችው ጊዜ ከእግሩ በታች ሰግዳ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኑረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። ጌታችን ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ፥ ከእርስዋ ጋር የመጡ አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ በልቡ አዘነ፤ በራሱም ታወከ። እርሱም፥ “የት ቀበራችሁት?” አለ፤ እነርሱም፥ “አቤቱ፥ መጥተህ እይ” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። አይሁድም፥ “ምን ያህል ይወደው እንደ ነበር እዩ” አሉ። ከእነርሱም መካከል፥ “ዕዉር ሆኖ የተወለደውን ዐይን ያበራው ይህ ሰው ይህስ እንዳይሞት ሊያደርግ ባልቻለም ነበርን?” ያሉ ነበሩ። ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ በልቡ አዘነ፤ ወደ መቃብሩም ሄደ፤ መቃብሩም ዋሻ ነበር፤ በላዩም ታላቅ ድንጋይ ተገጥሞበት ነበር። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ድንጋዩን አንሡ” አላቸው፤ የሟቹ እኅት ማርታም፥ “ጌታዬ ሆይ፥ አራት ቀን ሆኖታልና ፈጽሞ ሸትቶ ይሆናል” አለችው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ብታምናስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ አላልሁሽም ነበርን?” አላት። ድንጋዩንም አነሡ፤ ጌታችን ኢየሱስም ዐይኖቹን አቅንቶ እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ፥ ሰምተኸኛልና አመሰግንሃለሁ። እኔም ዘወትር እንደምትሰማኝ አውቃለሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ቆመው ስላሉት ሰዎች ይህን እናገራለሁ።” ይህንም ብሎ በታላቅ ቃል ጮኸና፥ “አልዓዛር፥ ና፤ ወደ ውጭ ውጣ” አለ። ሞቶ የነበረውም እንደ ተገነዘ፥ እጁንና እግሩንም እንደ ታሰረ፥ ፊቱም በሰበን እንደ ተጠቀለለ ወጣ፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እንግዲህስ ፍቱትና ተዉት ይሂድ” አላቸው።
ዮሐንስ 11:20-44 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ማርታ የኢየሱስን መምጣት ሰምታ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ቀርታ ነበር። ማርታም ኢየሱስን እንዲህ አለችው፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር። አሁንም ቢሆን የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ።” ኢየሱስም፣ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት። ማርታም፣ “በመጨረሻው ቀን፣ በትንሣኤ እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በእኔ የሚኖር፣ የሚያምንብኝም ከቶ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽን?” እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። ይህን ካለች በኋላ፣ ተመልሳ እኅቷን ማርያምን ለብቻዋ ጠርታ፣ “መምህሩ መጥቷል፤ ይፈልግሻልም” አለቻት። ማርያምም ይህን እንደ ሰማች፣ ፈጥና ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ቦታ ነበር እንጂ፣ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር። ማርያምን ሲያጽናኑ በቤት ውስጥ የነበሩ አይሁድም፣ ብድግ ብላ መውጣቷን ሲያዩ፣ ወደ መቃብሩ ሄዳ የምታለቅስ መስሏቸው ተከተሏት። ማርያምም ኢየሱስ ወደ ነበረበት ቦታ ደርሳ እንዳየችው፣ እግሩ ላይ ተደፍታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው። ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ፣ ተከትለዋትም የመጡት አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ መንፈሱ በሐዘን ታውኮ፣ “የት ነው ያኖራችሁት?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ መጥተህ እይ” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። አይሁድም፣ “እንዴት ይወድደው እንደ ነበር አያችሁ” አሉ። ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን፣ “የዐይነ ስውሩን ዐይን የከፈተ፣ ይህም ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበር?” አሉ። ኢየሱስ ልቡ ዳግመኛ በሐዘን ተነክቶ ወደ መቃብሩ መጣ፤ መቃብሩም በድንጋይ የተገጠመ ዋሻ ነበር፤ እርሱም፣ “ድንጋዩን አንሡት” አለ። የሟቹም እኅት ማርታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሁንማ አራት ቀን ስለ ቈየ ይሸታል” አለችው። ኢየሱስም፣ “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርሁሽም?” አላት። ስለዚህ ድንጋዩን አነሡ። ኢየሱስም ወደ ላይ ተመልክቶ አንዲህ አለ፤ “አባት ሆይ፤ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ይህን መናገሬ ግን በዚህ የቆሙ ሰዎች አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ ነው።” ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ በታላቅ ድምፅ፣ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” ብሎ ተጣራ። የሞተውም ሰው እጅና እግሩ በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ፣ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ። ኢየሱስም “መግነዙን ፍቱለትና ይሂድ” አላቸው።
ዮሐንስ 11:20-44 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም፦ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት። ማርታም፦ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም፦ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝ ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርስዋም፦ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ፦ “መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል” አለቻት። እርስዋም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ሲያጽናኑአት ከእርስዋ ጋር በቤት የነበሩ አይሁድም ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ “ወዴት አኖራችሁት?” አለም። እነርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ መጥተህ እይ” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህ አይሁድ፦ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ” አሉ። ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ፦ “ይህ የዕውሩን ዓይኖች የከፈተ ይህን ደግሞ እንዳይሞት ያደርግ ዘንድ ባልቻለም ነበርን?” አሉ። ኢየሱስም በራሱ አዝኖ ወደ መቃብሩ መጣ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ኢየሱስ፦ “ድንጋዩን አንሡ” አለ። የሞተውም እኅት ማርታ፦ “ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል” አለችው። ኢየሱስ፦ “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን?” አላት። ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ፦ “አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ” አለ። ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ፦ “አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና” ብሎ ጮኸ። የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም፦ “ፍቱትና ይሂድ ተዉት” አላቸው።
ዮሐንስ 11:20-44 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ማርታ የኢየሱስን መምጣት በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ቀርታ ነበር። ማርታ ኢየሱስን፥ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፥ ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ ነገር ግን አሁንም የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ እንደገና ከሞት ይነሣል” አላት። ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ ጊዜ ከሞት እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በሕይወት የሚኖርና በእኔም የሚያምን ሁሉ ፈጽሞ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽ?” አላት። እርስዋም “አዎ ጌታ ሆይ! አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። ማርታ ይህን ከተናገረች በኋላ ሄደችና እኅትዋን ማርያምን “መምህር መጥቶአል፤ አንቺንም ይጠራሻል” ብላ በስውር ጠራቻት። ማርያም ይህን በሰማች ጊዜ በፍጥነት ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች። ያን ጊዜ ኢየሱስ ማርታ እርሱን ባገኘችበት ስፍራ ነበር እንጂ ወደ መንደር ገና አልገባም ነበር። እርስዋን ለማጽናናት መጥተው በቤት ውስጥ አብረዋት የነበሩ አይሁድ ማርያም በፍጥነት ተነሥታ ስትወጣ አይተው ወደ አልዓዛር መቃብር ሄዳ የምታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያም ኢየሱስ ወደ ነበረበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ሥር ወደቀችና “ጌታ ሆይ፥ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። ኢየሱስ እርስዋ ስታለቅስና አብረዋት የመጡትም አይሁድ ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ በመንፈሱ እጅግ አዝኖ በመታወክ፥ “የት ነው የቀበራችሁት?” አለ። እነርሱም “ጌታ ሆይ! ና እይ” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህ አይሁድ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ ተመልከቱ” አሉ። ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን፥ “የዕውርን ዐይኖች ያበራ፥ ይህ ሰው እንዳይሞት ሊያደርግ አይችልም ነበርን?” አሉ። ኢየሱስ በጣም እያዘነ ወደ መቃብሩ ሄደ፤ መቃብሩ በድንጋይ የተዘጋ ዋሻ ነበር። ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሡት” አለ። የሟቹ እኅት ማርታ፥ “ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታል፤ አሁን ይሸታል” አለችው። ኢየሱስም “ካመንሽ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብዬሽ አልነበረምን?” አላት። ሰዎቹም ድንጋዩን አነሡት፤ ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ላይ ተመልክቶ፥ “አባት ሆይ! ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ይህን ያልኩት፥ እዚህ የቆሙት ሰዎች አንተ እንደ ላክኸኝ እንዲያምኑ ብዬ ነው” አለ። ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ “አልዓዛር! ና ውጣ!” ብሎ በታላቅ ድምፅ ተናገረ። ሟቹ አልዓዛርም እጆቹና እግሮቹ በመገነዣ እንደ ተገነዙ ከመቃብሩ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር፤ ኢየሱስም “ፍቱትና ተዉት ይሂድ!” አላቸው።
ዮሐንስ 11:20-44 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ማርታም ኢየሱስ እንደመጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሣል፤” አላት። ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሣ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነና በእኔ የሚያምን ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ “መምህር መጥቷል፤ እየጠራሽም ነው፤” አለቻት። እርሷም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፥ ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ከእርሷ ጋር በቤት ሲያጽናኑአት የነበሩ አይሁድም፥ ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤” አለችው። ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ ከእርሷም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ “ወዴት አኖራችሁት?” ዓለም። እነርሱም “ጌታ ሆይ! መጥተህ እይ፤” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህም አይሁድ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ፤” አሉ። ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ “የዐይነ ሥውሩን ዐይኖች እንደ ከፈተ ይህም ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበርን?” አሉ። ኢየሱስም በድጋሚ በጥልቅ ኀዘን ተውጦ ወደ መቃብሩ መጣ፤ መቃብሩም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሡ፤” አለ። የሞተውም ሰው እኅት ማርታ “ጌታ ሆይ! ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል፤” አለችው። ኢየሱስ “ካመንሽ የእግዚአብሔርን ክብር እንደምታዪ አልነገርሁሽምን?” አላት። ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዐይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ! ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ፤” ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ “አልዓዛር ሆይ! ና፥ ወደ ውጭ ውጣ፤” ብሎ ጮኸ። ሞቶ የነበረውም ሰው እጆቹና እግሮቹ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ። ኢየሱስም “ፍቱትና ይሂድ፤ ተዉት፤” አላቸው።