ዮሐንስ 11:17-36
ዮሐንስ 11:17-36 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታችን ኢየሱስም ወደ ቢታንያ ሄደ፤ ከዚያም በደረሰ ጊዜ ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት አገኘው። ቢታንያም ለኢየሩሳሌም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርያምና ወደ ማርታ የሄዱ ብዙዎች ነበሩ። ማርታም ጌታችን ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ወጥታ ተቀበለችው፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ጌታችን ኢየሱስን እንዲህ አለችው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኖረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር። አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ።” ጌታችን ኢየሱስም፥ “ወንድምሽስ ይነሣል” አላት። ማርታም፥ “ሙታን በሚነሡባት በኋለኛዪቱ ቀን እንደሚነሣ አውቃለሁ” አለችው። ጌታችን ኢየሱስም አላት፥ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞትም ይነሣል። ሕያው የሆነ የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህንስ ታምኛለሽን?” እርስዋም፥ “አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅቷን ማርያምንም ቀስ ብላ ጠራችና፥ “እነሆ፥ መምህራችን መጥቶ ይጠራሻል” አለቻት። እርስዋም ይህን በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፤ ወደ እርሱም ሄደች። ጌታችን ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር። ሊያጽናኑአት መጥተው በቤት ከእርስዋ ጋር የነበሩ አይሁድም ፈጥና ተነሥታ እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ በዚያ ለወንድምዋ ልታለቅስ ወደ መቃብሩ የምትሄድ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ጌታችን ኢየሱስ ወደ አለበት ስፍራ ደረሰችና በአየችው ጊዜ ከእግሩ በታች ሰግዳ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኑረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። ጌታችን ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ፥ ከእርስዋ ጋር የመጡ አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ በልቡ አዘነ፤ በራሱም ታወከ። እርሱም፥ “የት ቀበራችሁት?” አለ፤ እነርሱም፥ “አቤቱ፥ መጥተህ እይ” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። አይሁድም፥ “ምን ያህል ይወደው እንደ ነበር እዩ” አሉ።
ዮሐንስ 11:17-36 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ሲደርስ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ቢታንያ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ትርቅ ነበር። ብዙዎች አይሁድም ማርታንና ማርያምን ስለ ወንድማቸው ሞት ሊያጽናኗቸው መጥተው ነበር፤ ማርታ የኢየሱስን መምጣት ሰምታ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ቀርታ ነበር። ማርታም ኢየሱስን እንዲህ አለችው፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር። አሁንም ቢሆን የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ።” ኢየሱስም፣ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት። ማርታም፣ “በመጨረሻው ቀን፣ በትንሣኤ እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በእኔ የሚኖር፣ የሚያምንብኝም ከቶ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽን?” እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። ይህን ካለች በኋላ፣ ተመልሳ እኅቷን ማርያምን ለብቻዋ ጠርታ፣ “መምህሩ መጥቷል፤ ይፈልግሻልም” አለቻት። ማርያምም ይህን እንደ ሰማች፣ ፈጥና ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ቦታ ነበር እንጂ፣ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር። ማርያምን ሲያጽናኑ በቤት ውስጥ የነበሩ አይሁድም፣ ብድግ ብላ መውጣቷን ሲያዩ፣ ወደ መቃብሩ ሄዳ የምታለቅስ መስሏቸው ተከተሏት። ማርያምም ኢየሱስ ወደ ነበረበት ቦታ ደርሳ እንዳየችው፣ እግሩ ላይ ተደፍታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው። ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ፣ ተከትለዋትም የመጡት አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ መንፈሱ በሐዘን ታውኮ፣ “የት ነው ያኖራችሁት?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ መጥተህ እይ” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። አይሁድም፣ “እንዴት ይወድደው እንደ ነበር አያችሁ” አሉ።
ዮሐንስ 11:17-36 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም በመጣ ጊዜ በመቃብር እስከ አሁን አራት ቀን ሆኖት አገኘው። ቢታንያም አሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም፦ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት። ማርታም፦ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም፦ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝ ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርስዋም፦ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ፦ “መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል” አለቻት። እርስዋም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ሲያጽናኑአት ከእርስዋ ጋር በቤት የነበሩ አይሁድም ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ “ወዴት አኖራችሁት?” አለም። እነርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ መጥተህ እይ” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህ አይሁድ፦ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ” አሉ።
ዮሐንስ 11:17-36 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ እዚያ በደረሰ ጊዜ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት አገኘው። ቢታንያ ከኢየሩሳሌም የምትርቀው ሦስት ኪሎ ሜትር ያኽል ነው። ከአይሁድም ብዙዎች ማርታንና ማርያምን ስለ ወንድማቸው ሞት ለማጽናናት ወደ እነርሱ መጥተው ነበር። ማርታ የኢየሱስን መምጣት በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ቀርታ ነበር። ማርታ ኢየሱስን፥ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፥ ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ ነገር ግን አሁንም የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ እንደገና ከሞት ይነሣል” አላት። ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ ጊዜ ከሞት እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በሕይወት የሚኖርና በእኔም የሚያምን ሁሉ ፈጽሞ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽ?” አላት። እርስዋም “አዎ ጌታ ሆይ! አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። ማርታ ይህን ከተናገረች በኋላ ሄደችና እኅትዋን ማርያምን “መምህር መጥቶአል፤ አንቺንም ይጠራሻል” ብላ በስውር ጠራቻት። ማርያም ይህን በሰማች ጊዜ በፍጥነት ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች። ያን ጊዜ ኢየሱስ ማርታ እርሱን ባገኘችበት ስፍራ ነበር እንጂ ወደ መንደር ገና አልገባም ነበር። እርስዋን ለማጽናናት መጥተው በቤት ውስጥ አብረዋት የነበሩ አይሁድ ማርያም በፍጥነት ተነሥታ ስትወጣ አይተው ወደ አልዓዛር መቃብር ሄዳ የምታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያም ኢየሱስ ወደ ነበረበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ሥር ወደቀችና “ጌታ ሆይ፥ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። ኢየሱስ እርስዋ ስታለቅስና አብረዋት የመጡትም አይሁድ ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ በመንፈሱ እጅግ አዝኖ በመታወክ፥ “የት ነው የቀበራችሁት?” አለ። እነርሱም “ጌታ ሆይ! ና እይ” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህ አይሁድ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ ተመልከቱ” አሉ።
ዮሐንስ 11:17-36 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም በመጣ ጊዜ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ቢታንያም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። ማርታም ኢየሱስ እንደመጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሣል፤” አላት። ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሣ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነና በእኔ የሚያምን ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ “መምህር መጥቷል፤ እየጠራሽም ነው፤” አለቻት። እርሷም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፥ ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ከእርሷ ጋር በቤት ሲያጽናኑአት የነበሩ አይሁድም፥ ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤” አለችው። ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ ከእርሷም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ “ወዴት አኖራችሁት?” ዓለም። እነርሱም “ጌታ ሆይ! መጥተህ እይ፤” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህም አይሁድ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ፤” አሉ።