ዮሐንስ 11:1-32

ዮሐንስ 11:1-32 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የማ​ር​ያ​ምና የእ​ኅቷ የማ​ርታ መን​ደር በሚ​ሆን በቢ​ታ​ንያ ስሙ አል​ዓ​ዛር የሚ​ባል የታ​መመ አንድ ሰው ነበር። ማር​ያም ግን ጌታ​ች​ንን ሽቱ የቀ​ባ​ችው፥ እግ​ሩ​ንም በጠ​ጕ​ርዋ ያሸ​ችው ናት፤ ወን​ድ​ምዋ አል​ዓ​ዛ​ርም ታሞ ነበር። እኅ​ቶ​ቹም፥ “ጌታ​ችን ሆይ፥ እነሆ፥ የም​ት​ወ​ደው ታሞ​አል” ብለው ወደ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ላኩ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ሰምቶ እን​ዲህ አለ፥ “ይህ ደዌ በእ​ርሱ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅ ይከ​ብር ዘንድ ስለ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይ​ደ​ለም።” ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ማር​ታ​ንና እኅ​ቷን ማር​ያ​ምን፥ አል​ዓ​ዛ​ር​ንም ይወ​ዳ​ቸው ነበር። እንደ ታመመ በሰማ ጊዜM በነ​በ​ረ​በት ቦታ ሁለት ቀን ቈየ። ከዚ​ህም በኋላ፥ ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱን፥ “ኑ፥ ወደ ይሁዳ ሀገር ደግሞ እን​ሂድ” አላ​ቸው። ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም፥ “መም​ህር ሆይ፥ አይ​ሁድ ሊወ​ግ​ሩህ ይሹ አል​ነ​በ​ረ​ምን? ዛሬ ደግሞ አንተ ወደ​ዚያ ልት​ሄድ ትሻ​ለ​ህን?” አሉት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ቀኑ ዐሥራ ሁለት ሰዓት አይ​ደ​ለ​ምን? በቀን የሚ​ሄድ አይ​ሰ​ና​ከ​ልም፤ የዚ​ህን ዓለም ብር​ሃን ያያ​ልና። በሌ​ሊት የሚ​ሄድ ግን ይሰ​ነ​ካ​ከ​ላል፤ በው​ስጡ የሚ​ያ​የው ብር​ሃን የለ​ምና።” ይህ​ንም ለደቀ መዛ​ሙ​ርቱ ነገ​ራ​ቸው፤ ከዚ​ህም በኋላ፥ “ወዳ​ጃ​ችን አል​ዓ​ዛር ተኝ​ቶ​አል፤ ነገር ግን ላነ​ቃው እሄ​ዳ​ለሁ” አላ​ቸው። ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም፥ “አቤቱ፥ ከተ​ኛስ ይነ​ቃል፤ ይድ​ና​ልም” አሉት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ስለ ሞቱ ተና​ገረ፤ እነ​ርሱ ግን ስለ እን​ቅ​ልፍ መተ​ኛት መስ​ሎ​አ​ቸው ነበር። ከዚህ በኋ​ላም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ገልጦ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “አል​ዓ​ዛር ሞተ። ታም​ኑም ዘንድ እኔ በዚያ ባለ​መ​ኖሬ ስለ እና​ንተ ደስ ይለ​ኛል፤ ነገር ግን ኑ፥ ወደ እርሱ እን​ሂድ።” ዲዲ​ሞስ የሚ​ሉት ቶማ​ስም፥ ባል​ን​ጀ​ሮ​ቹን ደቀ መዛ​ሙ​ርት፥ “እኛም ከእ​ርሱ ጋር እን​ሞት ዘንድ እን​ሂድ” አላ​ቸው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ወደ ቢታ​ንያ ሄደ፤ ከዚ​ያም በደ​ረሰ ጊዜ ከተ​ቀ​በረ አራት ቀን ሆኖት አገ​ኘው። ቢታ​ን​ያም ለኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ዐሥራ አም​ስት ምዕ​ራፍ ያህል ቅርብ ነበ​ረች። ከአ​ይ​ሁ​ድም ስለ ወን​ድ​ማ​ቸው ሊያ​ጽ​ና​ኑ​አ​ቸው ወደ ማር​ያ​ምና ወደ ማርታ የሄዱ ብዙ​ዎች ነበሩ። ማር​ታም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ እንደ መጣ በሰ​ማች ጊዜ ወጥታ ተቀ​በ​ለ​ችው፤ ማር​ያም ግን በቤት ተቀ​ምጣ ነበር። ማር​ታም ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን እን​ዲህ አለ​ችው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኖረህ ቢሆን ወን​ድሜ ባል​ሞ​ተም ነበር። አሁ​ንም ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የም​ት​ለ​ም​ነ​ውን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲ​ሰ​ጥህ አው​ቃ​ለሁ።” ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ወን​ድ​ም​ሽስ ይነ​ሣል” አላት። ማር​ታም፥ “ሙታን በሚ​ነ​ሡ​ባት በኋ​ለ​ኛ​ዪቱ ቀን እን​ደ​ሚ​ነሣ አው​ቃ​ለሁ” አለ​ችው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም አላት፥ “ትን​ሣ​ኤና ሕይ​ወት እኔ ነኝ፤ የሚ​ያ​ም​ን​ብኝ ቢሞ​ትም ይነ​ሣል። ሕያው የሆነ የሚ​ያ​ም​ን​ብ​ኝም ሁሉ ለዘ​ለ​ዓ​ለም አይ​ሞ​ትም፤ ይህ​ንስ ታም​ኛ​ለ​ሽን?” እር​ስ​ዋም፥ “አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ወደ ዓለም የሚ​መ​ጣው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅ ክር​ስ​ቶስ እንደ ሆንህ እኔ አም​ና​ለሁ” አለ​ችው። ይህ​ንም ብላ ሄደች፤ እኅ​ቷን ማር​ያ​ም​ንም ቀስ ብላ ጠራ​ችና፥ “እነሆ፥ መም​ህ​ራ​ችን መጥቶ ይጠ​ራ​ሻል” አለ​ቻት። እር​ስ​ዋም ይህን በሰ​ማች ጊዜ ፈጥና ተነ​ሣች፤ ወደ እር​ሱም ሄደች። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ማርታ በተ​ቀ​በ​ለ​ች​በት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መን​ደር አል​ገ​ባም ነበር። ሊያ​ጽ​ና​ኑ​አት መጥ​ተው በቤት ከእ​ር​ስዋ ጋር የነ​በሩ አይ​ሁ​ድም ፈጥና ተነ​ሥታ እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ በዚያ ለወ​ን​ድ​ምዋ ልታ​ለ​ቅስ ወደ መቃ​ብሩ የም​ት​ሄድ መስ​ሎ​አ​ቸው ተከ​ተ​ሉ​አት። ማር​ያ​ምም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ወደ አለ​በት ስፍራ ደረ​ሰ​ችና በአ​የ​ችው ጊዜ ከእ​ግሩ በታች ሰግዳ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኑረህ ቢሆን ወን​ድሜ ባል​ሞ​ተም ነበር” አለ​ችው።

ዮሐንስ 11:1-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በማርያምና በእኅቷ በማርታ መንደር በቢታንያ ይኖር የነበረው አልዓዛር ታምሞ ነበር። ይህች ወንድሟ አልዓዛር የታመመባት ማርያም፣ ጌታን ሽቱ ቀብታ እግሮቹን በጠጕሯ ያበሰችው ነበረች። እኅትማማቾቹም፣ “ጌታ ሆይ፤ የምትወድደው ሰው ታምሟል” ብለው መልእክት ላኩበት። ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ፣ “ይህ ሕመም የእግዚአብሔር ልጅ በርሱ ይከብር ዘንድ ለእግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት የሚያደርስ አይደለም” አለ። ኢየሱስም ማርታን፣ እኅቷንና አልዓዛርን ይወድዳቸው ነበር። ሆኖም አልዓዛር መታመሙን በሰማ ጊዜ፣ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ቈየ። ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ወደ ይሁዳ እንመለስ” አላቸው። እነርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ ከጥቂት ጊዜ በፊት አይሁድ በድንጋይ ሊወግሩህ እየፈለጉህ ነበር፤ እንደ ገና ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ቀኑ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ብርሃን አይደለምን? ከዚህ ዓለም ብርሃን የተነሣ ስለሚያይ በቀን የሚመላለስ አይሰናከልም፤ የሚሰናከለው ግን በሌሊት የሚመላለስ ነው፤ ብርሃን የለውምና።” ይህን ከነገራቸው በኋላ፣ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ እኔም ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ጌታ ሆይ፤ ተኝቶ ከሆነስ ይድናል” አሉት። ኢየሱስ ይህን የነገራቸው ስለ ሞቱ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን እንቅልፍ ስለ መተኛቱ የተናገረ መሰላቸው። ስለዚህም በግልጽ እንዲህ አላቸው፤ “አልዓዛር ሞቷል፤ ታምኑ ዘንድ፣ በዚያ ባለ መኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ አሁን ግን ወደ እርሱ እንሂድ።” ከዚያም ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ለተቀሩት ደቀ መዛሙርት፣ “እኛም ሄደን ከርሱ ጋራ እንሙት” አላቸው። ኢየሱስ ሲደርስ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ቢታንያ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ ዐምስት ምዕራፍ ያህል ትርቅ ነበር። ብዙዎች አይሁድም ማርታንና ማርያምን ስለ ወንድማቸው ሞት ሊያጽናኗቸው መጥተው ነበር፤ ማርታ የኢየሱስን መምጣት ሰምታ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ቀርታ ነበር። ማርታም ኢየሱስን እንዲህ አለችው፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር። አሁንም ቢሆን የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ።” ኢየሱስም፣ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት። ማርታም፣ “በመጨረሻው ቀን፣ በትንሣኤ እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በእኔ የሚኖር፣ የሚያምንብኝም ከቶ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽን?” እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። ይህን ካለች በኋላ፣ ተመልሳ እኅቷን ማርያምን ለብቻዋ ጠርታ፣ “መምህሩ መጥቷል፤ ይፈልግሻልም” አለቻት። ማርያምም ይህን እንደ ሰማች፣ ፈጥና ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ቦታ ነበር እንጂ፣ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር። ማርያምን ሲያጽናኑ በቤት ውስጥ የነበሩ አይሁድም፣ ብድግ ብላ መውጣቷን ሲያዩ፣ ወደ መቃብሩ ሄዳ የምታለቅስ መስሏቸው ተከተሏት። ማርያምም ኢየሱስ ወደ ነበረበት ቦታ ደርሳ እንዳየችው፣ እግሩ ላይ ተደፍታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው።

ዮሐንስ 11:1-32 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከማርያምና ከእኅትዋ ከማርታ መንደር ከቢያትንያ የሆነ አልዓዛር የሚባል አንድ ሰው ታሞ ነበር። ማርያምም ጌታን ሽቱ የቀባችው እግሩንም በጠጕርዋ ያበሰሰችው ነበረች፤ ወንድምዋም አልዓዛር ታሞ ነበር። ስለዚህ እኅቶቹ “ጌታ ሆይ፥ እነሆ የምትወደው ታሞአል” ብለው ወደ እርሱ ላኩ። ኢየሱስም ሰምቶ፦ “ይህ ህመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም” አለ። ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን አልዓዛርንም ይወድ ነበር። እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያን ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤ ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ፦ “ወደ ይሁዳ ደግሞ እንሂድ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ፦ “መምህር ሆይ፥ አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፥ ደግሞም ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ፦ “ቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ ቢኖር የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል” አላቸው። ከዚህም በኋላ፦ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አላቸው። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ፦ “ጌታ ሆይ፥ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል” አሉት። ኢየሱስስ ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት እንደ ተናገረ መሰላቸው። እንግዲህ ያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጥ፦ “አልዓዛር ሞተ፤ እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ” አላቸው። ስለዚህ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ለባልንጀሮቹ ለደቀ መዛሙርቱ፦ “ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ” አለ። ኢየሱስም በመጣ ጊዜ በመቃብር እስከ አሁን አራት ቀን ሆኖት አገኘው። ቢታንያም አሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም፦ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት። ማርታም፦ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም፦ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝ ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርስዋም፦ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ፦ “መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል” አለቻት። እርስዋም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ሲያጽናኑአት ከእርስዋ ጋር በቤት የነበሩ አይሁድም ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው።

ዮሐንስ 11:1-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በቢታንያ የሚኖር አልዓዛር የሚባል አንድ ሰው ታሞ ነበር፤ ቢታንያ ማርያምና እኅትዋ ማርታ የሚኖሩባት መንደር ነበረች። ይህች ማርያም የጌታን እግር ሽቶ የቀባችውና በጠጒርዋ ያበሰችው ናት፤ የታመመውም አልዓዛር የእርስዋ ወንድም ነበር። እኅትማማቾቹም “ጌታ ሆይ፥ ያ የምትወደው ታሞአል” ብለው ወደ ኢየሱስ ላኩበት። ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ፥ “ይህ ሕመም ለሞት የሚያደርስ አይደለም፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ክብር እንዲሆንና የእግዚአብሔር ልጅም በዚህ ምክንያት እንዲከበር ነው” አለ። ኢየሱስ ማርታንና እኅትዋን ማርያምን ወንድማቸውን አልዓዛርንም ይወድ ነበር። ሆኖም የአልዓዛርን መታመም በሰማ ጊዜ በነበረበት ቦታ ሁለት ቀን ቈየ። ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፥ “ወደ ይሁዳ ምድር እንደገና እንሂድ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “መምህር ሆይ! አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፤ ታዲያ እንደገና ወደዚያ ተመልሰህ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በቀን ውስጥ ያለው ጊዜ ዐሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ የዚህን ዓለም ብርሃን ስለሚያይ አይሰናከልም። ነገር ግን በሌሊት የሚመላለስ ብርሃን ስለሌለው ይሰናከላል።” ኢየሱስ ይህን ካላቸው በኋላ፥ “ወዳጃችን አልዓዛር አንቀላፍቶአል፤ እኔ ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አለ። ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! አንቀላፍቶስ ከሆነ ይሻለዋል ማለት ነው” አሉት። ኢየሱስ ይህን የተናገረው ስለ አልዓዛር መሞት ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ የተናገረ መስሎአቸው ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በግልጥ እንዲህ አላቸው፦ “አልዓዛር ሞቶአል፤ እናንተ እንድታምኑ እዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ብሎኛል፤ አሁን ግን ወደ እርሱ እንሂድ።” በዚህ ጊዜ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ሌሎቹን ደቀ መዛሙርት፥ “ከእርሱ ጋር እንድንሞት እኛም እንሂድ” አላቸው። ኢየሱስ እዚያ በደረሰ ጊዜ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት አገኘው። ቢታንያ ከኢየሩሳሌም የምትርቀው ሦስት ኪሎ ሜትር ያኽል ነው። ከአይሁድም ብዙዎች ማርታንና ማርያምን ስለ ወንድማቸው ሞት ለማጽናናት ወደ እነርሱ መጥተው ነበር። ማርታ የኢየሱስን መምጣት በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ቀርታ ነበር። ማርታ ኢየሱስን፥ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፥ ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ ነገር ግን አሁንም የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ እንደገና ከሞት ይነሣል” አላት። ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ ጊዜ ከሞት እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በሕይወት የሚኖርና በእኔም የሚያምን ሁሉ ፈጽሞ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽ?” አላት። እርስዋም “አዎ ጌታ ሆይ! አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። ማርታ ይህን ከተናገረች በኋላ ሄደችና እኅትዋን ማርያምን “መምህር መጥቶአል፤ አንቺንም ይጠራሻል” ብላ በስውር ጠራቻት። ማርያም ይህን በሰማች ጊዜ በፍጥነት ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች። ያን ጊዜ ኢየሱስ ማርታ እርሱን ባገኘችበት ስፍራ ነበር እንጂ ወደ መንደር ገና አልገባም ነበር። እርስዋን ለማጽናናት መጥተው በቤት ውስጥ አብረዋት የነበሩ አይሁድ ማርያም በፍጥነት ተነሥታ ስትወጣ አይተው ወደ አልዓዛር መቃብር ሄዳ የምታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያም ኢየሱስ ወደ ነበረበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ሥር ወደቀችና “ጌታ ሆይ፥ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው።

ዮሐንስ 11:1-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አንድ ሰው ታሞ ነበር፤ እርሱም እንደ ማርያምና እንደ እኅትዋ ማርታ ከቢታንያ የነበረው አልዓዛር ነው። ማርያም ጌታን ሽቱ የቀባችው፥ እግሩንም በጠጉርዋ ያበሰችው ስትሆን፤ የታመመውም አልዓዛር ወንድምዋ ነበር። ስለዚህም እኅቶቹ “ጌታ ሆይ! እነሆ የምትወደው ታሞአል፤” ብለው ወደ እርሱ ላኩበት። ኢየሱስም ሰምቶ “ይህ ሕመም ለሞት አይሰጥም፤ ይልቁንም ለእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ነው” አለ። ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን እንዲሁም አልዓዛርን ይወድ ነበር። እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያንጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤ ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ ይሁዳ እንደገና እንሂድ፤” አላቸው። ደቀመዛሙርቱ “መምህር ሆይ! አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፤ በድጋሚ ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ “በቀን ውስጥ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ይገኙ የለምን? በቀን የሚመላለስ የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል፤” አላቸው። ይህንንም ከተናገረ በኋላ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ፤” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! ተኝቶ እንደ ሆነስ ይድናል፤” አሉት። ኢየሱስ ግን ስለ ሞቱ ነበር የተናገረው፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ የተናገረ መሰላቸው። እንግዲህ ያንጊዜ ኢየሱስ በግልጥ “አልዓዛር ሞተ፤ እናንተ እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ፤” አላቸው። ዲዲሞስ የሚሉትም ቶማስ ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርት “ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛም እንሂድ፤” አለ። ኢየሱስም በመጣ ጊዜ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ቢታንያም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። ማርታም ኢየሱስ እንደመጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሣል፤” አላት። ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሣ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነና በእኔ የሚያምን ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ “መምህር መጥቷል፤ እየጠራሽም ነው፤” አለቻት። እርሷም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፥ ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ከእርሷ ጋር በቤት ሲያጽናኑአት የነበሩ አይሁድም፥ ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤” አለችው።