ዮሐንስ 10:1-42
ዮሐንስ 10:1-42 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች ስፍራ በበሩ የማይገባ፥ በሌላም በኩል የሚገባ ሌባ፥ ወንበዴም ነው። በበሩ የሚገባ ግን የበጎች ጠባቂ ነው። ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፤ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል። ሁሉንም አውጥቶ ባሰማራቸው ጊዜ በፊት በፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ይከተሉታል፤ ቃሉን ያውቃሉና። ሌላውን ግን ይሸሹታል እንጂ አይከተሉትም፤ የሌላውን ቃሉን አያውቁምና።” ጌታችን ኢየሱስም ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸውን አላወቁም። ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የበጎች በር እኔ ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ነገር ግን፤ በጎች አልሰሙአቸውም። እውነተኛዉ የበጎች በር እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩልም የሚገባ ይድናል፤ ይገባልም ይወጣልም፤ መሰማርያም ያገኛል። ሌባ ግን ሊሰርቅና ሊያርድ፥ ሊያጠፋም ካልሆነ በቀር አይመጣም፤ እኔ ግን የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኙ፥ እጅግም እንዲበዛላቸው መጣሁ። “ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ ግን፥ ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም መጥቶ በጎችን ይነጥቃቸዋል፥ ይበትናቸዋልም። ምንደኛስ ይሸሻል፤ ስለ በጎችም አያዝንም፤ ምንደኛ ነውና። ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ የእኔ የሆኑትን መንጋዎችን አውቃለሁ፤ የእኔ የሆኑትም ያውቁኛል። አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን አውቀዋለሁ፤ ለበጎችም ቤዛ አድርጌ ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህ ቦታ ያይደሉ ሌሎች በጎችም አሉኝ፤ እነርሱንም ወደዚህ አመጣቸው ዘንድ ይገባኛል፤ ቃሌንም ይሰሙኛል፤ ለአንድ እረኛም አንድ መንጋ ይሆናሉ። ስለዚህም፤ አብ ይወድደኛል፥ እንደ ገና አስነሣት ዘንድ እኔ ነፍሴን እሰጣለሁና። ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ነገር ግን እኔ በፈቃዴ እሰጣታለሁ፤ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝና፤ ይህንም ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።” ስለዚህም ነገር አይሁድ እንደገና እርስ በርሳቸው ተለያዩ። ከእነርሱም ብዙዎች፥ “ጋኔን ይዞት ያብዳል፤ ለምንስ ታዳምጡታላችሁ?” አሉ። ሌሎችም ይህ ነገር ጋኔን ከያዘው ሰው የሚገኝ አይደለም፤ ጋኔን የዕዉሮችን ዐይን ማብራት ይችላልን?” አሉ። በዚያም ወራት በኢየሩሳሌም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ክረምትም ነበር። ጌታችን ኢየሱስም በቤተ መቅደስ በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ይመላለስ ነበር። አይሁድም እርሱን ከብበው፥ “እስከ መቼ ድረስ ሰውነታችንን ታስጨንቀናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “አታምኑኝም እንጂ ነገርኋችሁ፤ እኔ በአባቴ ስም የምሠራው ሥራ እርሱ ምስክሬ ነው። እናንተ ግን አታምኑኝም፤ እንደ ነገርኋችሁ ከበጎች ውስጥ አይደላችሁምና። የእኔ የሆኑ በጎች ግን ቃሌን ይሰሙኛል፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል። እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘለዓለሙም አይጠፉም፤ ከእጄም የሚነጥቃቸው የለም። እነርሱን የሰጠኝ አባቴ እርሱ ከሁሉ ይበልጣልና፤ ከአባቴም እጅ መንጠቅ የሚችል የለም። እኔና አብ አንድ ነን።” ዳግመኛም አይሁድ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ በየትኛው ሥራ ምክንያት ትወግሩኛላችሁ?” አይሁድም፥ “አንተ፥ ሰው ስትሆን ራስህን እግዚአብሔርን ታደርጋለህና፤ ስለ መሳደብህ ነው እንጂ ስለ መልካም ሥራህስ አንወግርህም” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እኔ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በኦሪታችሁ ተጽፎ የለምን? የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን እነዚያን አማልክት ካላቸው፥ የመጽሐፉ ቃል ይታበል ዘንድ አይቻልም። እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብላችሁ፥ አብ የቀደሰውንና ወደ ዓለምም የላከውን እንዴት ትሳደባለህ? ትሉኛላችሁ። የአባቴን ሥራ ባልሠራ በእኔ አትመኑ። ከሠራሁ ግን፥ እኔን እንኳን ባታምኑ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ታውቁና ትረዱ ዘንድ ሥራዬን እመኑ።” ዳግመኛም ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም አመለጠ። ዳግመኛም ቀድሞ ዮሐንስ ያጠምቅበት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ሄደ፤ በዚያም ተቀመጠ። ብዙዎችም ወደ እርሱ ሄደው፥ “ዮሐንስ ምንም ያደረገው ተአምራት የለም፤ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ሆነ” አሉ። በዚያም ብዙ ሰዎች አመኑበት።
ዮሐንስ 10:1-42 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች ጕረኖ በበሩ ሳይሆን፣ በሌላ በኩል ዘልሎ የሚገባ ሌባና ነጣቂ ነው። በበሩ የሚገባ ግን እርሱ የበጎቹ እረኛ ነው፤ በር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል። የራሱ የሆኑትንም ሁሉ ካወጣ በኋላ ፊት ፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። እንግዳ የሆነውን ግን ድምፁን ስለማያውቁ ከርሱ ይሸሻሉ እንጂ ፈጽሞ አይከተሉትም።” ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን ምን እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም። ስለዚህ ኢየሱስ ዳግም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የበጎች በር እኔ ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ቀማኞች ነበሩ፤ በጎቹ ግን አልሰሟቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ሁሉ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅ፣ ሊገድልና ሊያጠፋ ብቻ ይመጣል፤ እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል፤ ተቀጣሪው እረኛ ግን በጎቹ የርሱ ስላልሆኑ፣ ተኵላ ሲመጣ ጥሏቸው ይሸሻል፤ ተኵላውም በጎቹን ይነጥቃል፤ ይበትናቸዋልም። የሚሸሸውም ተቀጣሪ ስለ ሆነና ለበጎቹ ደንታ ስለሌለው ነው። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤ ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው። ሕይወቴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህ ጕረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ። እነርሱም ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። መልሼ ለማንሣት ሕይወቴን አሳልፌ ስለምሰጥ አባቴ ይወድደኛል። ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ መልሼ ለመውሰድ ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልሁትም ከአባቴ ነው።” ከዚህም ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ተፈጠረ። ብዙዎቹም፣ “ጋኔን ያደረበት እብድ ነው፤ ለምን ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎች ግን፣ “ይህ ጋኔን ያደረበት ሰው ንግግር አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ስውርን ዐይን መክፈት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳሌምም የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ጊዜውም ክረምት ነበረ፤ ኢየሱስም በቤተ መቅደስ ግቢ፣ በሰሎሞን መመላለሻ ያልፍ ነበር፤ አይሁድም ከብበውት፣ “እስከ መቼ ልባችንን አንጠልጥለህ ታቈየናለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንህ በግልጽ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔ ነግሬአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የማደርጋቸው ታምራትም ስለ እኔ ይናገራሉ፤ እናንተ ግን በጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም፤ በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል፤ እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም። እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ማንም ሊነጥቃቸው አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን።” አይሁድ ሊወግሩት እንደ ገና ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን፣ “ከአብ የሆኑ ብዙ ታላላቅ ታምራትን አሳየኋችሁ፤ ታዲያ ከእነዚህ ስለ የትኛው ትወግሩኛላችሁ?” አላቸው። አይሁድም፣ “የምንወግርህ፣ ተራ ሰው ሆነህ ሳለህ፣ ራስህን አምላክ በማድረግ፣ የስድብ ቃል ስለ ተናገርህ ነው እንጂ ከእነዚህ ስለ የትኛውም አይደለም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በሕጋችሁ፣ ‘እናንተ አማልክት ናችሁ አልሁ’ ተብሎ አልተጻፈምን? የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን ‘አማልክት’ ካላቸውና መጽሐፍም ሊሻር የማይቻል ከሆነ፣ ታዲያ፣ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ስላልሁ፣ አብ ለራሱ ለይቶ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን፣ ‘ተሳድበሃል’ ብላችሁ ለምን ትወነጅሉኛላችሁ? አባቴ የሚያደርገውን ባላደርግ አትመኑኝ፤ የማደርገው ከሆነ ግን እኔን ባታምኑኝ እንኳ፣ አብ በእኔ እንዳለ እኔም በአብ እንዳለሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ታምራቱን እመኑ።” እንደ ገናም ሊይዙት ሞከሩ፤ እርሱ ግን ከእጃቸው አመለጠ። ከዚያም ኢየሱስ፣ ቀደም ሲል ዮሐንስ ያጠምቅበት ወደ ነበረበት፣ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ተመለሰ፤ በዚያም ሰነበተ፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጡ። እነርሱም፣ “ዮሐንስ አንድም ታምራዊ ምልክት አላደረገም፤ ነገር ግን ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ” አሉ። በዚያም ስፍራ ብዙዎች በኢየሱስ አመኑ።
ዮሐንስ 10:1-42 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና።” ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነሩስ ግን የነገራቸው ምን እንደ ሆነ አላስተዋሉም። ኢየሱስም ደግሞ አላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንድሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎቼ አኖራለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ። ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።” እንግዲህ ከዚህ ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ሆነ። ከእነርሱም ብዙዎች፦ “ጋኔን አለበት አብዶአልም፤ ስለ ምንስ ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎችም፦ “ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዕውሮችን ዓይኖች ሊከፍት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳልውምም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ክረምትም ነበረ። ኢየሱስም በመቅደስ በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ይመላለስ ነበር። አይሁድም እርሱን ከበው፦ “እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሪ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል፦ “ነገርኋችሁ አታምኑምም እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተ ግን እንደ ነገርኋችሁ ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን።” አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ። ኢየሱስ፦ “ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ?” ብሎ መለሰላቸው። አይሁድም፦ “ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ “እኔ፦ ‘አማልክት ናችሁ አልሁ’ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የተቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን፦ ትሳደባለህ ትሉታላችሁን? እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አንትመኑኝ፤ ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።” እንግዲህ ደግመው ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም ወጣ። ዮሐንስም በመጀመሪያ ያጠምቅበት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ እንደ ገና ሄደ በዚያም ኖረ። ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው፦ “ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ” አሉ። በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ።
ዮሐንስ 10:1-42 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች በረት በበር ሳይሆን በሌላ በኩል የሚገባ ሰው ሌባና ወንበዴ ነው። በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ የበር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹ ድምፁን ይሰማሉ፤ እርሱም የራሱን በጎች በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ እየመራም ወደ ውጪ ያወጣቸዋል። የራሱን በጎች ካስወጣ በኋላም እፊት እፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። የሌላውን ድምፅ ግን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉም።” ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የተናገረውን አላስተዋሉም። ስለዚህ ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጎች በር ነኝ፤ ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ በጎቹ ግን አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣል፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው የሚመጣው ለመስረቅ፥ ለማረድና ለማጥፋት ብቻ ነው፤ እኔ ግን የመጣሁት ሕይወት እንዲያገኙና የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲኖራቸው ነው። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። በጎቹ የራሱ ያልሆኑ ቅጥረኛ እንጂ እውነተኛ ያልሆነ እረኛ ግን ተኲላ ሲመጣ በሚያይበት ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኲላውም በጎቹን ነጥቆ ይበታትናቸዋል። እረኛው የሚሸሸውም ቅጥረኛ ስለ ሆነና ለበጎቹም ስለማያስብ ነው። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ እኔ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ በጎቼም እኔን ያውቁኛል። እኔ እነርሱን የማውቃቸው አብ እኔን እንደሚያውቀኝና እኔም አብን እንደማውቀው ዐይነት ነው፤ እኔ ስለ በጎቼ ሕይወቴን አሳልፌ እሰጣለሁ። በዚህ መንጋ ውስጥ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት ይገባኛል፤ እነርሱ ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ ይሆናል። “እንደገና መልሼ እወስዳት ዘንድ ሕይወቴን የምሰጥ ስለ ሆንኩ አብ እኔን ይወደኛል። ሕይወቴን በፈቃዴ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ የሚወስዳት ማንም የለም፤ ሕይወቴን ለመስጠትና መልሼም ለመውሰድ ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልኩት ከአባቴ ነው።” ከዚህ ንግግር የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደገና መለያየት ሆነ። ከእነርሱም ብዙዎቹ፥ “እርሱ ጋኔን አለበት፤ አብዶአል፤ ስለምን ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎች “ይህ ንግግር ጋኔን ካለበት ሰው አንደበት የሚወጣ አይደለም፤ ጋኔን የዕውርን ዐይን ማብራት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳሌም የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል የሚከበርበት ጊዜ ደረሰ፤ ወቅቱም ክረምት ነበር፤ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ በሰሎሞን መተላለፊያ ይመላለስ ነበር። በዚያን ጊዜ አይሁድ በዙሪያው ተሰብስበው፥ “እስከ መቼ በጥርጣሬ ታቈየናለህ? አንተ መሲሕ እንደ ሆንክ በግልጥ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ ነግሬአችኋለሁ፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የምሠራው ሥራ ስለ እኔ ይመሰክራል። እናንተ ግን ከበጎቼ መንጋ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል። እኔ የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ስለዚህ ከቶ አይጠፉም፤ ከእኔ እጅ ማንም ነጥቆ አይወስዳቸውም። እነርሱን ለእኔ የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል። ከአባቴ እጅ እነርሱን ነጥቆ መውሰድ የሚችል ማንም የለም። እኔና አብ አንድ ነን።” በዚህ ጊዜ አይሁድ ኢየሱስን ለመውገር እንደገና ድንጋይ አነሡ። ኢየሱስም “ከአብ ዘንድ ብዙ መልካም ሥራዎችን አሳየኋችሁ፤ ታዲያ፥ የምትወግሩኝ ከእነዚህ ስለየትኛው ሥራ ነው?” አላቸው። እነርሱም “እኛ የምንወግርህ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ስለ መናገርህ ነው እንጂ ስለ መልካም ሥራህ አይደለም፤ ይኸውም አንተ ሰው ሆነህ ሳለ፥ ራስህን አምላክ ስላደረግህ ነው” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “በሕጋችሁስ ‘እናንተ አማልክት ናችሁ አልኩ’ የሚል ተጽፎ የለምን? እንግዲህ ቅዱስ መጽሐፍን መሻር አይቻልም፤ የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን ቅዱስ መጽሐፍ አማልክት ብሎ ከጠራቸው ታዲያ፥ አብ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ስለ አለ ስለምን ‘በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ትናገራለህ’ ትሉታላችሁ? እኔ የአባቴን ሥራ የማልሠራ ከሆንኩ አትመኑኝ። የአባቴን ሥራ የምሠራ ከሆንኩ ግን በእኔ እንኳ ባታምኑ በሥራዬ እመኑ፤ በዚህ ዐይነት አብ በእኔ እንደ ሆነና እኔም በአብ እንደ ሆንኩ በሚገባ ታውቃላችሁ።” እነርሱም እንደገና ሊይዙት ፈለጉ፤ እርሱ ግን ከእጃቸው አምልጦ ሄደ። እንደገናም ኢየሱስ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ ዮሐንስ መጀመሪያ ያጠምቅበት ወደነበረው ስፍራ ሄደ፤ በዚያም ቈየ። ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ መጥተው “ዮሐንስ ምንም ተአምር አላደረገም፤ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ” አሉ። እዚያም ብዙ ሰዎች በእርሱ አመኑ።
ዮሐንስ 10:1-42 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች በረት በበሩ ሳይሆን የማይገባ በሌላ መንገድ የሚገባ እርሱ ሌባና ወንበዴ ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ በር ጠባቂው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፤ የእራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። የእራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፤ የሌሎቹን ድምፅ አያውቁምና።” ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ምን እንደሆነ አላስተዋሉም። ኢየሱስም ደግሞ አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጎች በር ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፤ ይገባልም፤ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድና ሊያጠፋ እንጂ ለሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወትን እንዲያገኙ፥ የተትረፈረፈ ሕይወትን እንዲያገኙ መጣሁ፤ መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑት ተቀጣሪው ግን፥ ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኩላም ይነጥቃቸዋል፤ በጎቹንም ይበትናቸዋል። ተቀጣሪ ስለሆነ፥ ለበጎቹም ስለማይገደው ይሸሻል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ የእራሴን በጎች አውቃለሁ፤ የእራሴም በጎች ያውቁኛል። አብም እንደሚያውቀኝ፥ እኔም አብን እንደማውቀው፤ ነፍሴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ማምጣት ይገባኛል፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ አንድም መንጋ ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። መልሼ ለመውሰድ ነፍሴን አሳልፌ ስለምሰጥ አብ ይወደኛል። እኔ ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። አሳልፌ ለመስጠት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ ለመውሰድም ሥልጣን አለኝ፤ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።” ከእነኚህ ቃላት የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደገና መለያየት ሆነ። ከእነርሱም ብዙዎች “ጋኔን አለበት፤ አብዶአልም፤ ለምንስ ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎችም “ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ሥውሮችን ዐይን ሊከፍት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳሌምም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ወቅቱም የብርድ ጊዜ ነበር። ኢየሱስም በመቅደስ፥ በሰሎሞን ታዛ ይመላለስ ነበር። አይሁድም እርሱን ከብበው “እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሬ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንህ በግልጥ ንገረን፤” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ነገርኋችሁ፤ ነገር ግን አታምኑም፤ እኔ በአባቴ ስም የማደርጋቸው ሥራዎች ስለ እኔ ይመሰክራሉ፤ እናንተ ግን ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘለዓለምም አይጠፉም፤ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን።” አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ። ኢየሱስ “ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ የትኛው ሥራ ትወግሩኛላችሁ?” ብሎ መለሰላቸው። አይሁድም “ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ እንጂ፤ ይልቁንም አንተ ሰው ሆነህ ሳለህ እራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ ‘አማልክት ናችሁ አልሁ፤’ ተብሎ በሕጋችሁ ተጽፎ የለምን? መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ አብ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን እናንተ ‘ትሳደባለህ፤’ ትሉታላችሁን? እኔ የአባቴን ሥራ የማልሠራ ከሆነ አትመኑኝ፤ የምሠራ ከሆነ ግን፥ እኔን እንኳን ባታምኑ፥ አብ በእኔ እንደሆነ እኔም በአብ እንደሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።” ደግመኛም ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም አምልጦ ሄደ። ዮሐንስም በመጀመሪያ ያጠምቅበት ወደነበረው ስፍራ፥ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ፥ እንደገና ሄደ፤ በዚያም ተቀመጠ። ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው “ዮሐንስ አንድ ምልክት እንኳን አላደረገም፤ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ፤” አሉ። በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ።