የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዮሐንስ 1:19-51

ዮሐንስ 1:19-51 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አይ​ሁድ፥ “አንተ ማን ነህ?” ብለው ይጠ​ይ​ቁት ዘንድ ካህ​ና​ት​ንና ሌዋ​ው​ያ​ንን ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም በላኩ ጊዜ የዮ​ሐ​ንስ ምስ​ክ​ር​ነት ይህ ነው። እር​ሱም፥ “እኔ ክር​ስ​ቶስ አይ​ደ​ለ​ሁም” ብሎ አመነ እንጂ አል​ካ​ደም። “እን​ኪያ አንተ ማነህ? አንተ ኤል​ያስ ነህን?” ብለው ጠየ​ቁት፤ “አይ​ደ​ለ​ሁም” አለ፤ “እን​ኪያ አንተ ነቢዩ ነህን?” አሉት፤ “አይ​ደ​ለ​ሁም” አለ። “እን​ኪ​ያስ አንተ ማነህ? ለላ​ኩ​ንም መልስ እን​ድ​ን​ሰጥ ስለ ራስህ ማን ትላ​ለህ?” አሉት። እር​ሱም፥ “ነቢዩ ኢሳ​ይ​ያስ እንደ ተና​ገረ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መን​ገድ ጥረጉ እያለ በም​ድረ በዳ የሚ​ሰ​ብክ የዐ​ዋጅ ነጋሪ ድምፅ እኔ ነኝ” አለ። የተ​ላ​ኩ​ትም ከፈ​ሪ​ሳ​ው​ያን ነበሩ። “እን​ኪ​ያስ ክር​ስ​ቶ​ስን ካል​ሆ​ንህ፥ ኤል​ያ​ስ​ንም ካል​ሆ​ንህ፥ ነቢ​ይ​ንም ካል​ሆ​ንህ ለምን ታጠ​ም​ቃ​ለህ?” ብለው ጠየ​ቁት። ዮሐ​ን​ስም መልሶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እኔ በውኃ አጠ​ም​ቃ​ች​ኋ​ለሁ፤ ነገር ግን እና​ንተ የማ​ታ​ው​ቁት በመ​ካ​ከ​ላ​ችሁ ቆሞ​አል። ከእኔ በኋላ የሚ​መ​ጣው፥ ከእኔ በፊት የነ​በ​ረው፥ የጫ​ማ​ውን ጠፍር ልፈታ እንኳ የማ​ይ​ገ​ባኝ ነው።” ዮሐ​ንስ ያጠ​ም​ቅ​በት በነ​በ​ረው በዮ​ር​ዳ​ኖስ ማዶ በቢ​ታ​ንያ በቤተ ራባ እን​ዲህ ሆነ። በማ​ግ​ሥ​ቱም ዮሐ​ንስ ወደ እርሱ ሲመጣ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን አይቶ እን​ዲህ አለ፤ “እነሆ፥ የዓ​ለ​ሙን ኀጢ​ኣት የሚ​ያ​ስ​ወ​ግድ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በግ። ከእኔ በፊት የነ​በረ ሰው ከእኔ በኋላ ይመ​ጣል ብዬ ስለ እርሱ የነ​ገ​ር​ኋ​ችሁ ይህ ነው፤ እርሱ ከእኔ አስ​ቀ​ድሞ ነበ​ርና። እኔ አላ​ው​ቀ​ውም ነበር፤ ነገር ግን እስ​ራ​ኤል እን​ዲ​ያ​ው​ቁት ስለ​ዚህ እኔ በውኃ ላጠ​ምቅ መጣሁ።” ዮሐ​ን​ስም ምስ​ክ​ር​ነ​ቱን እን​ዲህ ብሎ ተና​ገረ፥ “መን​ፈስ ቅዱስ ከሰ​ማይ እንደ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀ​መጥ አየሁ። እኔም አላ​ው​ቀ​ውም ነበር፤ ነገር ግን በውኃ እን​ዳ​ጠ​ምቅ የላ​ከኝ እርሱ መን​ፈስ ቅዱስ ወርዶ ሲቀ​መ​ጥ​በት የም​ታ​የው በመ​ን​ፈስ ቅዱስ የሚ​ያ​ጠ​ምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም ራሴ አይ​ቻ​ለሁ፤ እር​ሱም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅ እንደ ሆነ እኔ ምስ​ክሩ ነኝ።” በማ​ግ​ሥ​ቱም ደግሞ ዮሐ​ንስ ከሁ​ለቱ ደቀ መዛ​ሙ​ርቱ ጋር ቆሞ ሳለ፥ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን ሲሄድ አይቶ “እነሆ፥ የዓ​ለ​ሙን ኀጢ​ኣት የሚ​ያ​ስ​ወ​ግድ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በግ” አለ። ሁለቱ ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም እን​ዲህ ሲል ሰም​ተው ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን ተከ​ተ​ሉት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ዘወር ብሎ ሲከ​ተ​ሉት አየና፥ “ምን ትሻ​ላ​ችሁ?” አላ​ቸው። እነ​ር​ሱም፥ “ረቢ፥ ትር​ጓ​ሜ​ውም መም​ህር ሆይ፥ ማለት ነው፤ ወዴት ትኖ​ራ​ለህ?” አሉት። እር​ሱም “መጥ​ታ​ችሁ እዩ” አላ​ቸው፤ ሄደ​ውም የሚ​ኖ​ር​በ​ትን አዩ፤ ያን ዕለ​ትም እስከ ዐሥር ሰዓት ድረስ በእ​ርሱ ዘንድ ዋሉ። ከዮ​ሐ​ንስ ዘንድ ሰም​ተው ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን ከተ​ከ​ተ​ሉት ከሁ​ለ​ቱም አንዱ የስ​ም​ዖን ጴጥ​ሮስ ወን​ድም እን​ድ​ር​ያስ ነበር። እር​ሱም መጀ​መ​ሪያ ወን​ድሙ ስም​ዖ​ንን አግ​ኝቶ “በት​ር​ጓ​ሜው ክር​ስ​ቶስ የሚ​ሉት መሲ​ሕን አገ​ኘ​ነው” አለው። እር​ሱም ወደ ጌታ​ችን ወደ ኢየ​ሱስ ወሰ​ደው፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ባየው ጊዜ፥ “ አንተ የዮና ልጅ ስም​ዖን ነህን? አንተ ኬፋ ትባ​ላ​ለህ፤” አለው፤ ትር​ጓ​ሜ​ውም ጴጥ​ሮስ ማለት ነው። በማ​ግ​ሥ​ቱም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ወደ ገሊላ ሊሄድ ወደደ፤ ፊል​ጶ​ስ​ንም አገ​ኘ​ውና “ተከ​ተ​ለኝ” አለው። ፊል​ጶስ ግን ከእ​ን​ድ​ር​ያ​ስና ከጴ​ጥ​ሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበር። ፊል​ጶ​ስም ናት​ና​ኤ​ልን አገ​ኘ​ውና፥ “ሙሴ በኦ​ሪት፥ ነቢ​ያ​ትም ስለ እርሱ የጻ​ፉ​ለ​ትን የዮ​ሴ​ፍን ልጅ የና​ዝ​ሬ​ቱን ኢየ​ሱ​ስን አገ​ኘ​ነው” አለው። ናት​ና​ኤ​ልም፥ “በውኑ ከና​ዝ​ሬት ደግ ሰው ሊወጣ ይቻ​ላ​ልን?” አለው፤ ፊል​ጶ​ስም፥ “መጥ​ተህ እይ” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ናት​ና​ኤ​ልን ወደ እርሱ ሲመጣ ባየው ጊዜ ስለ እርሱ “እነሆ፥ በልቡ ተን​ኰል የሌ​ለ​በት እው​ነ​ተኛ እስ​ራ​ኤ​ላዊ ይህ ነው” አለ። ናት​ና​ኤ​ልም፥ “በየት ታው​ቀ​ኛ​ለህ?” አለው፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ፥ “ገና ፊል​ጶስ ሳይ​ጠ​ራህ በበ​ለስ ዛፍ ሥር ሳለህ አይ​ች​ሃ​ለሁ” አለው። ናት​ና​ኤ​ልም መልሶ፥ “መም​ህር ሆይ፥ በእ​ው​ነት አንተ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅ ነህ፤ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ንጉሥ አንተ ነህ” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ፥ “በበ​ለስ ዛፍ ሥር አየ​ሁህ ስለ አል​ሁህ አመ​ን​ህን? ከዚህ የሚ​በ​ልጥ ታያ​ለህ” አለው።

ዮሐንስ 1:19-51 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አይሁድ፣ ማንነቱን እንዲጠይቁት ካህናትንና ሌዋውያንን ከኢየሩሳሌም ወደ እርሱ ሲልኩ፣ ዮሐንስ የሰጠው ምስክርነት ይህ ነበር። ከመመስከርም ወደ ኋላ አላለም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤” ብሎ በግልጽ መሰከረ። እነርሱም፣ “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ ነቢዩ ነህ?” አሉት። እርሱም፣ “አይደለሁም” ሲል መለሰ። በመጨረሻም፣ “እንግዲያስ ማን ነህ? ለላኩን ሰዎች መልስ እንድንሰጥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። ዮሐንስም በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተነገረው፣ “ ‘ለጌታ መንገድ አቅኑለት’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ድምፅ እኔ ነኝ” ሲል መለሰ። ከተላኩትም ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፣ “ታዲያ፣ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፤ ለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ እናንተ የማታውቁት ግን በመካከላችሁ ቆሟል፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው፣ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ እርሱ ነው።” ይህ ሁሉ የሆነው ዮሐንስ ሲያጠምቅ በነበረበት ከዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር። ዮሐንስ በማግስቱም፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበር ከእኔ ይልቃል’ ያልሁት እርሱ ነው፤ እኔ ራሴ አላወቅሁትም ነበር፤ በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁትም እርሱ በእስራኤል ዘንድ እንዲገለጥ ነው።” ከዚያም ዮሐንስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፤ “መንፈስ እንደ ርግብ ከሰማይ ወርዶ በእርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ፤ በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝም፣ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣ መንፈስ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲያርፍ የምታየው እርሱ ነው’ ብሎ እስከ ነገረኝ ድረስ እኔም አላወቅሁትም ነበር፤ አይቻለሁ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እመሰክራለሁ።” በማግስቱም፣ ዮሐንስ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ ገና እዚያው ቦታ ነበር፤ ኢየሱስንም በዚያ ሲያልፍ አይቶ፣ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር በግ!” አለ። ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት። ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉት አየና፣ “ምን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ረቢ፣ የት ትኖራለህ?” አሉት፤ “ረቢ” ማለት መምህር ማለት ነው። እርሱም፣ “ኑና እዩ” አላቸው። ስለዚህ ሄደው የት እንደሚኖር አዩ፤ በዚያም ዕለት አብረውት ዋሉ፤ ከቀኑም ዐሥር ሰዓት ያህል ነበር። ዮሐንስ የተናገረውን ሰምተው፣ ኢየሱስን ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበር። እንድርያስ በመጀመሪያ ያደረገው ወንድሙን ስምዖንን ፈልጎ፣ “መሲሑን አገኘነው” ብሎ መንገር ነው፤ “መሲሕ” ማለት ክርስቶስ ማለት ነው። ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመለከተውና፣ “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ ኬፋ ተብለህ ትጠራለህ” አለው፤ “ኬፋ” ማለት ጴጥሮስ ማለት ነው። በማግስቱም፣ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ለመሄድ ፈለገ፤ ፊልጶስንም አግኝቶ፣ “ተከተለኝ” አለው። ፊልጶስም እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ ሁሉ የቤተ ሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፣ “ሙሴ በሕግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስን አግኝተነዋል” አለው። ናትናኤልም፣ “ከናዝሬት በጎ ነገር ሊወጣ ይችላልን?” አለ። ፊልጶስም፣ “መጥተህ እይ” አለው። ኢየሱስም፣ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ፣ “እነሆ፤ ተንኰል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ” አለ። ናትናኤልም “እንዴት ዐወቅኸኝ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ፣ ገና ፊልጶስ ሳይጠራህ አየሁህ” ሲል መለሰለት። ናትናኤልም መልሶ፣ “ረቢ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለ። ኢየሱስም፣ “ያመንኸው ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ ስላልሁህ ነውን? ገና ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ” አለው፤ ጨምሮም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይ ተከፍቶ፣ የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” አለው።

ዮሐንስ 1:19-51 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አይሁድም፦ አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። መሰከረም አልካደምም እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ። እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ብለው ጠየቁት። አይደለሁም አለ። ነቢዩ ነህን? አይደለሁም ብሎ መለሰ። እንኪያስ፦ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት። እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ፦ የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና፦ እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት። ዮሐንስ መልሶ፦ እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው። ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ። በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ፦ መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፦ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ። በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ፦ እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት። ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ፦ ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ ትርጓሜው መምህር ሆይ ማለት ነው። መጥታችሁ እዩ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ። ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ። እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና፦ መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው። ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመልክቶ፦ አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ አለው፤ ትርጓሜው ጴጥሮስ ማለት ነው። በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና፦ ተከተለኝ አለው። ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፦ ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው። ናትናኤልም፦ ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን? አለው። ፊልጶስ፦ መጥተህ እይ አለው። ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ፦ ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ። ናትናኤልም፦ ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው። ናትናኤልም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው።

ዮሐንስ 1:19-51 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የአይሁድ ባለሥልጣኖች ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን ወደ ዮሐንስ ልከው፦ “አንተ ማን ነህ?” ብለው ባስጠየቁት ጊዜ የሰጠው ምስክርነት የሚከተለው ነው፤ እርሱ “እኔ መሲሕ አይደለሁም” ሲል መሰከረ እንጂ አልካደም። እነርሱም “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “አይደለሁም” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም “ይመጣል የተባለው ነቢይ ነህን?” አሉት። እርሱም “አይደለሁም” አለ። እነርሱም “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ለላኩን ሰዎች መልሱን እንድንነግር ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። እርሱም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ተናገረው እኔ ‘የጌታን መንገድ አቅኑ’ እያለ በበረሓ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነኝ” አለ። ሰዎቹ የተላኩት ከፈሪሳውያን ነበረ፤ ስለዚህ “አንተ መሲሕ ወይም ኤልያስ ወይም ይመጣል የተባለው ነቢይ ካልሆንክ ታዲያ፥ ስለምን ታጠምቃለህ?” ሲሉ ጠየቁት። ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ የማጠምቀው በውሃ ነው፤ ነገር ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል። እርሱ ከእኔ በኋላ የሚመጣ ነው፤ እኔ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የበቃሁ አይደለሁም።” ይህ የሆነው ዮሐንስ ያጠምቅ በነበረበት ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ በምትገኘው በቢታንያ ከተማ ነው። በማግስቱ ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ይህ ነው! ‘ያ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ እጅግ ይበልጣል’ ያልኳችሁ ይህ ነው። እኔም ራሴ አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲገለጥ እኔ በውሃ እያጠመቅሁ መጣሁ።” ቀጥሎም ዮሐንስ እንዲህ ሲል መሰከረ፦ “መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ ከሰማይ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲያርፍበት አየሁ፤ እኔ ራሴ አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝ፥ ‘መንፈስ ቅዱስ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲያርፍበት የምታየው በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው’ ሲል ነግሮኛል። እኔም ይህን አይቼአለሁ፤ ስለዚህ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እመሰክራለሁ።” በማግስቱ ዮሐንስ ከሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደገና እዚያ ቆሞ ነበር፤ ዮሐንስ ኢየሱስን በዚያ ሲያልፍ አይቶ፥ “እነሆ፥ የእግዚአብሔር በግ!” አለ። ሁለቱ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ዮሐንስ ይህን ሲል ሰምተው፥ ኢየሱስን ተከተሉት። ኢየሱስ መለስ ብሎ ሲከተሉት አየና “ምን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ረቢ! የምትኖረው የት ነው?” አሉት። (ረቢ ማለት መምህር ማለት ነው) እርሱም “ኑና እዩ” አላቸው። ስለዚህ ሄዱና የት እንደሚኖር አዩ። በዚያን ቀን ከእርሱ ጋር አብረው ዋሉ፤ ጊዜው ወደ ዐሥር ሰዓት ገደማ ነበር። ዮሐንስ የተናገረውን ቃል ሰምተው ኢየሱስን ከተከተሉት ደቀ መዛሙርት አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበር። እንድርያስ በመጀመሪያ ወደ ወንድሙ ወደ ስምዖን ሄደና “መሲሕን አገኘነው!” አለው። (መሲሕ ማለት ክርስቶስ ማለት ነው።) ከዚህ በኋላ እንድርያስ ስምዖንን ወደ ኢየሱስ አመጣው። ኢየሱስም ትኲር ብሎ ተመለከተውና “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ኬፋ ትባላለህ” አለው። (ኬፋ ማለት ጴጥሮስ ወይም አለት ማለት ነው።) በማግስቱ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ለመሄድ ፈለገ፤ ፊልጶስንም አገኘውና “ተከተለኝ!” አለው። ፊልጶስ እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ የቤተ ሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፥ “ሙሴ በሕግ መጽሐፍ፥ ነቢያትም በትንቢት መጻሕፍት ስለ እርሱ የጻፉለትን አገኘነው፤ እርሱም የዮሴፍ ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው” አለው። ናትናኤል ግን፥ “ከናዝሬት መልካም ነገር ከቶ ሊገኝ ይችላልን?” አለው። ፊልጶስም “መጥተህ እይ!” አለው። ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ኢየሱስ “እነሆ! ተንኰል የሌለበት እውነተኛ የእስራኤል ሰው!” ሲል ስለ እርሱ ተናገረ። ናትናኤልም “የት ታውቀኛለህ?” አለው። ኢየሱስም “ፊልጶስ ሳይጠራህ በፊት ከበለስ ዛፍ ሥር ሆነህ አይቼሃለሁ” ሲል መለሰለት። በዚህ ጊዜ ናትናኤል፥ “መምህር ሆይ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ! አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ!” አለ። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “አንተ ያመንከው፥ ‘ከበለስ ዛፍ ሥር ሆነህ አይቼሃለሁ’ ስላልኩህ ነውን? ከዚህ የበለጡ ነገሮችን ገና ታያለህ። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፦ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔር መላእክትም በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ።”

ዮሐንስ 1:19-51 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አይሁድም “አንተ ማን ነህ?” ብለው ለመጠየቅ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። መሰከረም፤ አልካደምም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤” ብሎ መሰከረ። “እንግዲያውስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ብለው ጠየቁት። “አይደለሁም” አለ። “ነቢዩ ነህን?” “አይደለሁም” ብሎ መለሰ። “እንግዲያውስ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። እርሱም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ ‘የጌታን መንገድ አቅኑ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነኝ” አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩ፤ “እንግዲያውስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፥ ስለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስ መልሶ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ነው፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የተገበሁ አይደለሁም” አላቸው። ይህ የሆነው ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር። በማግሥቱ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። ‘አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይበልጣል፤’ ብዬ ስለ እርሱ የተናገርሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ለእስራኤል እንዲገለጥ ነው በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁት።” ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ “መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሲወርድና በእርሱ ላይም ሲኖር አየሁ። እኔም አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን በውሃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ ‘መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው፤’ አለኝ። እኔም አይቻለሁ፥ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሬአለሁ።” በማግሥቱ ዮሐንስ ከሁለት ደቀመዛሙርቱ ጋር እንደገና እዚያ ቆሞ ነበር፤ ኢየሱስንም ሲራመድ ተመልክቶ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ፤” አለ። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት። ኢየሱስም መለስ ብሎ ሲከተሉትም አይቶ “ምን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ረቢ!፥ (ሲተረጎም ‘መምህር ሆይ’ ማለት ነው) የምትኖረው የት ነው?” አሉት፤ እርሱም “መጥታችሁ እዩ፤” አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፤ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ ጊዜው ወደ ዐሥር ሰዓት ገደማ ነበር። ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ። እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና “መሢሕን አግኝተናል” አለው፤ ትርጓሜውም “ክርስቶስ” ማለት ነው። ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመልክቶ “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ” አለው፤ ትርጓሜውም “ጴጥሮስ” ማለት ነው። በማግሥቱ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊሄድ ፈለገ፤ ፊልጶስንም አገኘውና “ተከተለኝ” አለው። ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ “ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል፤” አለው። ናትናኤልም “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?” አለው። ፊልጶስ “መጥተህ እይ” አለው። ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ “ተንኰል የሌለበት እውነተኛ የእስራኤል ሰው እነሆ!” አለ። ናትናኤልም “እንዴት አወቅኸኝ?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ ዛፍ ሥር ሆነህ፥ አየሁህ፤” አለው። ናትናኤልም መልሶ “መምህር ሆይ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለው። ኢየሱስም መልሶ “ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ፤” ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” አለው።