ዮሐንስ 1:1-28
ዮሐንስ 1:1-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉም በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም። ሕይወት በእርሱ ነበረ፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፤ ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላገኘውም። ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበር። እርሱም ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምን ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክርነት መጣ። ስለ ብርሃን ምስክር ሊሆን መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃንስ ወደ ዓለም የመጣው ነው። በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፤ ዓለሙ ግን አላወቀውም። ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም። ያም ቃል ሥጋ ሆነ፤ በእኛም አደረ፤ ለአባቱ አንድ እንደ ሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩን አየን፤ ጸጋንና እውነትን የተመላ ነው። ምስክሩ ዮሐንስ ስለ እርሱ ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ፤ እንዲህም አለ፥ “እኔ ስለ እርሱ ከእኔ በፊት የነበረ ከእኔ በኋላ ይመጣል ያልኋችሁ ሰው ይህ ነው፥ እርሱ ከእኔ አስቀድሞ ነበረና።” እኛም ሁላችን ከሙላቱ በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀበልን። ኦሪት በሙሴ ተሰጥታን ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነልን። በአባቱ ዕቅፍ ያለ አንድ ልጅ እርሱ ገለጠልን እንጂ እግዚአብሔርንስ ከቶ ያየው የለም። አይሁድ፥ “አንተ ማን ነህ?” ብለው ይጠይቁት ዘንድ ካህናትንና ሌዋውያንን ከኢየሩሳሌም በላኩ ጊዜ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። እርሱም፥ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም” ብሎ አመነ እንጂ አልካደም። “እንኪያ አንተ ማነህ? አንተ ኤልያስ ነህን?” ብለው ጠየቁት፤ “አይደለሁም” አለ፤ “እንኪያ አንተ ነቢዩ ነህን?” አሉት፤ “አይደለሁም” አለ። “እንኪያስ አንተ ማነህ? ለላኩንም መልስ እንድንሰጥ ስለ ራስህ ማን ትላለህ?” አሉት። እርሱም፥ “ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ተናገረ የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ እያለ በምድረ በዳ የሚሰብክ የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እኔ ነኝ” አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩ። “እንኪያስ ክርስቶስን ካልሆንህ፥ ኤልያስንም ካልሆንህ፥ ነቢይንም ካልሆንህ ለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል። ከእኔ በኋላ የሚመጣው፥ ከእኔ በፊት የነበረው፥ የጫማውን ጠፍር ልፈታ እንኳ የማይገባኝ ነው።” ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ እንዲህ ሆነ።
ዮሐንስ 1:1-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ። ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሯል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም። ሕይወት በእርሱ ነበረች፤ ይህች ሕይወት የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማውም አላሸነፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ዮሐንስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። ሰዎች ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ፣ ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ ለመቆም መጣ፤ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ ብርሃን ሰጭ የሆነው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። እርሱ በዓለም ውስጥ ነበረ፤ ዓለም የተፈጠረው በእርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ዓለም አላወቀውም። ወደ ራሱ ወገኖች መጣ፤ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፤ ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት ሰጣቸው። እነዚህም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ፣ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም ዐደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን። ዮሐንስም፣ “ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይልቃል’ ብዬ የመሰከርሁለት እርሱ ነው” በማለት ጮኾ ስለ እርሱ መሰከረ። ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤ ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ ዕቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው። አይሁድ፣ ማንነቱን እንዲጠይቁት ካህናትንና ሌዋውያንን ከኢየሩሳሌም ወደ እርሱ ሲልኩ፣ ዮሐንስ የሰጠው ምስክርነት ይህ ነበር። ከመመስከርም ወደ ኋላ አላለም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤” ብሎ በግልጽ መሰከረ። እነርሱም፣ “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ ነቢዩ ነህ?” አሉት። እርሱም፣ “አይደለሁም” ሲል መለሰ። በመጨረሻም፣ “እንግዲያስ ማን ነህ? ለላኩን ሰዎች መልስ እንድንሰጥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። ዮሐንስም በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተነገረው፣ “ ‘ለጌታ መንገድ አቅኑለት’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ድምፅ እኔ ነኝ” ሲል መለሰ። ከተላኩትም ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፣ “ታዲያ፣ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፤ ለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ እናንተ የማታውቁት ግን በመካከላችሁ ቆሟል፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው፣ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ እርሱ ነው።” ይህ ሁሉ የሆነው ዮሐንስ ሲያጠምቅ በነበረበት ከዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር።
ዮሐንስ 1:1-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ፦ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ። እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው። አይሁድም፦ አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። መሰከረም አልካደምም እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ። እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ብለው ጠየቁት። አይደለሁም አለ። ነቢዩ ነህን? አይደለሁም ብሎ መለሰ። እንኪያስ፦ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት። እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ፦ የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና፦ እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት። ዮሐንስ መልሶ፦ እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው። ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ።
ዮሐንስ 1:1-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቃል በመጀመሪያ ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ይህም ቃል እግዚአብሔር ነበረ። እርሱ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጠረ፤ ከተፈጠረው ሁሉ፥ አንድም ነገር ያለ እርሱ የተፈጠረ የለም። በእርሱ ሕይወት ነበረ፤ ይህም ሕይወት የሰዎች ብርሃን ነበረ። ብርሃን በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም ብርሃንን አያሸንፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ በእርሱ ምስክርነት ሰው ሁሉ እንዲያምን ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ መጣ። እርሱ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። እርሱም በዓለም ነበረ፤ ዓለምም የተፈጠረው በእርሱ ነው፤ ዓለም ግን አላወቀውም። ወደ ወገኖቹ መጣ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ይሁን እንጂ ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን መብት ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሰው ዘር፥ ማለትም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከሰው ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በመካከላችን ኖረ፤ የአባቱ አንድያ ልጅ በአባቱ ዘንድ እንዳለው ያለውን ክብሩን አይተናል። ዮሐንስም “ ‘ያ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለነበረ ከእኔ እጅግ ይበልጣል’ ብዬ የነገርኳችሁ እነሆ፥ ይህ ነው” እያለ መሰከረ። ከእርሱ የጸጋ ሙላት እኛ ሁላችን በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀብለናል። ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጠ፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ያለው አንድያ ልጁ ብቻ ገለጠው። የአይሁድ ባለሥልጣኖች ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን ወደ ዮሐንስ ልከው፦ “አንተ ማን ነህ?” ብለው ባስጠየቁት ጊዜ የሰጠው ምስክርነት የሚከተለው ነው፤ እርሱ “እኔ መሲሕ አይደለሁም” ሲል መሰከረ እንጂ አልካደም። እነርሱም “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “አይደለሁም” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም “ይመጣል የተባለው ነቢይ ነህን?” አሉት። እርሱም “አይደለሁም” አለ። እነርሱም “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ለላኩን ሰዎች መልሱን እንድንነግር ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። እርሱም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ተናገረው እኔ ‘የጌታን መንገድ አቅኑ’ እያለ በበረሓ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነኝ” አለ። ሰዎቹ የተላኩት ከፈሪሳውያን ነበረ፤ ስለዚህ “አንተ መሲሕ ወይም ኤልያስ ወይም ይመጣል የተባለው ነቢይ ካልሆንክ ታዲያ፥ ስለምን ታጠምቃለህ?” ሲሉ ጠየቁት። ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ የማጠምቀው በውሃ ነው፤ ነገር ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል። እርሱ ከእኔ በኋላ የሚመጣ ነው፤ እኔ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የበቃሁ አይደለሁም።” ይህ የሆነው ዮሐንስ ያጠምቅ በነበረበት ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ በምትገኘው በቢታንያ ከተማ ነው።
ዮሐንስ 1:1-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ አንድም ነገር ያለ እርሱ የሆነ የለም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፤ ሕይወትም የሰዎች ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፤ ጨለማም አላሸነፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክርነት መጣ፤ ሁሉም በእርሱ በኩል ያምኑ ዘንድ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፤ ዓለም ግን አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፤ ነገር ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበትን ሥልጣን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በእኛም ዘንድ አደረ፤ ጸጋንና እውነትን የተመላውን፥ የአባቱ አንድያ ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብሩንም አየን። ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ፤ እንዲህም ብሎ ጮኸ “‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤’ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።” እኛ ሁላችንም ከሙላቱ ተቀበልን፥ በጸጋ ላይ ጸጋን፤ ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ገለጠው። አይሁድም “አንተ ማን ነህ?” ብለው ለመጠየቅ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። መሰከረም፤ አልካደምም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤” ብሎ መሰከረ። “እንግዲያውስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ብለው ጠየቁት። “አይደለሁም” አለ። “ነቢዩ ነህን?” “አይደለሁም” ብሎ መለሰ። “እንግዲያውስ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። እርሱም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ ‘የጌታን መንገድ አቅኑ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነኝ” አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩ፤ “እንግዲያውስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፥ ስለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስ መልሶ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ነው፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የተገበሁ አይደለሁም” አላቸው። ይህ የሆነው ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር።