የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዮሐንስ 1:1-18

ዮሐንስ 1:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በመ​ጀ​መ​ሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ነበረ። ይህም በመ​ጀ​መ​ሪያ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉም በእ​ርሱ ሆነ፤ ከሆ​ነ​ውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም። ሕይ​ወት በእ​ርሱ ነበረ፥ ሕይ​ወ​ትም የሰው ብር​ሃን ነበረ፤ ብር​ሃ​ንም በጨ​ለማ ያበ​ራል፤ ጨለ​ማም አላ​ገ​ኘ​ውም። ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ የተ​ላከ ስሙ ዮሐ​ንስ የሚ​ባል አንድ ሰው ነበር። እር​ሱም ሁሉ በእ​ርሱ በኩል እን​ዲ​ያ​ምን ስለ ብር​ሃን ይመ​ሰ​ክር ዘንድ ለም​ስ​ክ​ር​ነት መጣ። ስለ ብር​ሃን ምስ​ክር ሊሆን መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብር​ሃን አል​ነ​በ​ረም። ለሰው ሁሉ የሚ​ያ​በ​ራው እው​ነ​ተ​ኛው ብር​ሃ​ንስ ወደ ዓለም የመ​ጣው ነው። በዓ​ለም ነበረ፤ ዓለ​ሙም በእ​ርሱ ሆነ፤ ዓለሙ ግን አላ​ወ​ቀ​ውም። ወደ ወገ​ኖቹ መጣ፤ ወገ​ኖቹ ግን አል​ተ​ቀ​በ​ሉ​ትም። ለተ​ቀ​በ​ሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚ​ያ​ምኑ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጆች እን​ዲ​ሆኑ ሥል​ጣ​ንን ሰጣ​ቸው። እነ​ር​ሱም ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ተወ​ለዱ እንጂ ከሥ​ጋ​ዊና ከደ​ማዊ ግብር ወይም ከወ​ን​ድና ከሴት ፈቃድ አል​ተ​ወ​ለ​ዱም። ያም ቃል ሥጋ ሆነ፤ በእ​ኛም አደረ፤ ለአ​ባቱ አንድ እንደ ሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብ​ሩን አየን፤ ጸጋ​ንና እው​ነ​ትን የተ​መላ ነው። ምስ​ክሩ ዮሐ​ንስ ስለ እርሱ ድም​ፁን ከፍ አድ​ርጎ ተና​ገረ፤ እን​ዲ​ህም አለ፥ “እኔ ስለ እርሱ ከእኔ በፊት የነ​በረ ከእኔ በኋላ ይመ​ጣል ያል​ኋ​ችሁ ሰው ይህ ነው፥ እርሱ ከእኔ አስ​ቀ​ድሞ ነበ​ረና።” እኛም ሁላ​ችን ከሙ​ላቱ በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀ​በ​ልን። ኦሪት በሙሴ ተሰ​ጥ​ታን ነበ​ርና፤ ጸጋና እው​ነት ግን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ሆነ​ልን። በአ​ባቱ ዕቅፍ ያለ አንድ ልጅ እርሱ ገለ​ጠ​ልን እንጂ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንስ ከቶ ያየው የለም።

ዮሐንስ 1:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ። ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሯል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም። ሕይወት በእርሱ ነበረች፤ ይህች ሕይወት የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማውም አላሸነፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ዮሐንስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። ሰዎች ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ፣ ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ ለመቆም መጣ፤ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ ብርሃን ሰጭ የሆነው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። እርሱ በዓለም ውስጥ ነበረ፤ ዓለም የተፈጠረው በእርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ዓለም አላወቀውም። ወደ ራሱ ወገኖች መጣ፤ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፤ ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት ሰጣቸው። እነዚህም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ፣ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም ዐደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን። ዮሐንስም፣ “ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይልቃል’ ብዬ የመሰከርሁለት እርሱ ነው” በማለት ጮኾ ስለ እርሱ መሰከረ። ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤ ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ ዕቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው።

ዮሐንስ 1:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ፦ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ። እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።

ዮሐንስ 1:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ቃል በመጀመሪያ ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ይህም ቃል እግዚአብሔር ነበረ። እርሱ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጠረ፤ ከተፈጠረው ሁሉ፥ አንድም ነገር ያለ እርሱ የተፈጠረ የለም። በእርሱ ሕይወት ነበረ፤ ይህም ሕይወት የሰዎች ብርሃን ነበረ። ብርሃን በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም ብርሃንን አያሸንፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ በእርሱ ምስክርነት ሰው ሁሉ እንዲያምን ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ መጣ። እርሱ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። እርሱም በዓለም ነበረ፤ ዓለምም የተፈጠረው በእርሱ ነው፤ ዓለም ግን አላወቀውም። ወደ ወገኖቹ መጣ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ይሁን እንጂ ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን መብት ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሰው ዘር፥ ማለትም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከሰው ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በመካከላችን ኖረ፤ የአባቱ አንድያ ልጅ በአባቱ ዘንድ እንዳለው ያለውን ክብሩን አይተናል። ዮሐንስም “ ‘ያ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለነበረ ከእኔ እጅግ ይበልጣል’ ብዬ የነገርኳችሁ እነሆ፥ ይህ ነው” እያለ መሰከረ። ከእርሱ የጸጋ ሙላት እኛ ሁላችን በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀብለናል። ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጠ፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ያለው አንድያ ልጁ ብቻ ገለጠው።

ዮሐንስ 1:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ አንድም ነገር ያለ እርሱ የሆነ የለም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፤ ሕይወትም የሰዎች ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፤ ጨለማም አላሸነፈውም። ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክርነት መጣ፤ ሁሉም በእርሱ በኩል ያምኑ ዘንድ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፤ ዓለም ግን አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፤ ነገር ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበትን ሥልጣን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በእኛም ዘንድ አደረ፤ ጸጋንና እውነትን የተመላውን፥ የአባቱ አንድያ ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብሩንም አየን። ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ፤ እንዲህም ብሎ ጮኸ “‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤’ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።” እኛ ሁላችንም ከሙላቱ ተቀበልን፥ በጸጋ ላይ ጸጋን፤ ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ገለጠው።

ዮሐንስ 1:1-18

ዮሐንስ 1:1-18 NASV