ኤርምያስ 25:8-14
ኤርምያስ 25:8-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህ ኀያል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ቃሌን አልሰማችሁምና፤ እነሆ ልኬ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ፤ ባሪያዬንም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እወስዳለሁ፤ በዚችም ምድርና በሚቀመጡባትም ሰዎች ላይ፥ በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፤ ለጥፋትና ለፉጨት ለዘለዓለምም ዕፍረት ባድማ አደርጋቸዋለሁ። ከእነርሱም የሐሤትን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራን ድምጽና የሴት ሙሽራን ድምፅ፥ የወፍጮንም ድምፅ የመብራትንም ብርሃን አስቀራለሁ። ይህችም ምድር ሁሉ ትጠፋለች፤ ለእነዚህም አሕዛብና ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ። “ሰባው ዓመትም በተፈጸመ ጊዜ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ያን ሕዝብ ስለ ኀጢአታቸው እቀጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ የከለዳውያንንም ምድር ለዘለዓለም አጠፋቸዋለሁ። በእርስዋም ላይ የተናገርሁትን ቃሌን ሁሉ፥ ኤርምያስ በአሕዛብ ሁሉ ላይ በትንቢት የተናገረውን በዚች መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ፥ በዚያች ምድር ላይ አመጣለሁ። ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት እነርሱን ይገዙአቸዋል፤ እኔም እንደ አደራረጋቸውና እንደ እጃቸው ሥራ እከፍላቸዋለሁ።”
ኤርምያስ 25:8-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ቃሌን ስላልሰማችሁ፣ የሰሜንን ሕዝብ ሁሉ፣ አገልጋዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እጠራለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “በዚህች ምድርና በነዋሪዎቿም ላይ፣ በአካባቢዋም ባሉ ሕዝቦች ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፤ ሰዎች የሚጸየፏቸውና የሚሣለቁባቸው፣ የዘላለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ፤ የደስታንና የእልልታን ድምፅ፣ የሙሽራውንና የሙሽራዪቱን ድምፅ፣ የወፍጮን ድምፅና የመብራትን ብርሃን አስቀራለሁ። አገሪቱ በሞላ ባድማና ጠፍ ትሆናለች፤ እነዚህም ሕዝቦች ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ። “ነገር ግን ሰባው ዓመት ከተፈጸመ በኋላ፣ የባቢሎንን ንጉሥና ሕዝቡን፣ የባቢሎናውያንንም ምድር ስለ በደላቸው እቀጣቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ለዘላለምም ባድማ አደርጋታለሁ፤ በምድሪቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ ይኸውም በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውንና ኤርምያስ በሕዝቦች ሁሉ ላይ የተናገረውን ትንቢት አመጣባታለሁ። ሕዝቧም ለብዙ ሕዝቦችና ለታላላቅ ነገሥታት ባሮች ይሆናሉ፤ እንደ አድራጎታቸውና እንደ እጃቸውም ሥራ እከፍላቸዋለሁ።”
ኤርምያስ 25:8-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ቃሌን አልሰማችሁምና እነሆ፥ ልኬ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ ባሪያዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እወስዳለሁ፥ በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፥ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፥ ለመደነቂያና ለማፍዋጫም ለዘላለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ። ከእነርሱም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ፥ የወፍጮንም ድምፅ የመብራትንም ብርሃን አስቀራለሁ። ይህችም ምድር ሁሉ ባድማና መደነቂያ ትሆናለች፥ እነዚህም አሕዛብ ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ። ሰባው ዓመትም በተፈጸመ ጊዜ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ያንን ሕዝብ ስለ ኃጢአታቸው እቀጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የከለዳውያንንም ምድር ለዘላለም ባድማ አደርጋታለሁ። በእርስዋም ላይ የተናገርሁትን ቃሌን ሁሉ፥ ማለት ኤርምያስ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ትንቢት የተናገረውን በዚህች መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ፥ በዚያች ምድር አመጣለሁ። ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት እነርሱን ያስገዙአቸዋል፥ እኔም እንደ አደራረጋቸውና እንደ እጃቸው ሥራ እከፍላቸዋለሁ።
ኤርምያስ 25:8-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“አናዳምጥም ከማለታችሁም የተነሣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ‘እነሆ በስተሰሜን ወዳሉት ነገዶችና አገልጋዬ ወደ ሆነው ወደ ባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር መልእክተኛ እልካለሁ፤ ይሁዳንና በውስጥዋ የሚኖሩትን፥ እንዲሁም በጐረቤት ያሉትን ሕዝቦች ይወጉ ዘንድ አመጣቸዋለሁ፤ ይህችን አገር ከነጐረቤቶችዋ አጠፋለሁ፤ ለማየት የሚያስፈሩና መሳለቂያ እስኪሆኑ ድረስ ለዘለዓለም ፍርስራሽ ሆነው እንዲቀሩ አደርጋቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። የደስታና የሐሤት ድምፅ፥ የሠርግ ዘፈንም ድምፅ እንዳይኖር፥ ማንም ሰው እህል እንዳይፈጭ፥ ወይም በሌሊት መብራት እንዳያበራ አደርጋለሁ። ምድሪቱ በሙሉ ፍርስራሽና ባድማ ትሆናለች፤ እነዚህ ሕዝቦችም ለሰባ ዓመት ለባቢሎን ንጉሥ ይገዛሉ። ከዚህም በኋላ ሰባው ዓመት ሲፈጸም ባቢሎንን፥ ሕዝብዋንና ንጉሥዋን በበደላቸው ምክንያት እቀጣቸዋለሁ፤ የባቢሎንም ምድር ለዘለዓለም ባድማ ሆና እንድትቀር አደርጋለሁ፤ በኤርምያስ አማካይነት በሕዝብ ሁሉ ላይ አመጣለሁ ያልኩትን፥ ማለትም በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ሁሉ በላይዋ ላይ በማውረድ ባቢሎንን እቀጣለሁ። ባቢሎናውያን ስላደረጉትም ክፋት ሁሉ ቅጣታቸውን እንዲያገኙ አደርጋለሁ፤ ብዙ ሕዝቦችና ታላላቅ ነገሥታት ባሪያ አድርገው ይገዙአቸዋል።’ ”
ኤርምያስ 25:8-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ቃሎቼን አልሰማችሁምና እነሆ፥ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ እልካለሁ ይላል ጌታ፥ ባርያዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እወስዳለሁ፥ በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች፥ በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፥ ለመሣቀቂያና ለማፍዋጫም ለዘለዓለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ። ከእነርሱም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የሙሽራውን ድምፅና የሙሽራይቱን ድምፅ፥ የወፍጮንም ድምፅ የመብራትንም ብርሃን አስቀራለሁ። ይህችም ምድር ሁሉ ባድማና መሣቀቂያ ትሆናለች፤ እነዚህም አሕዛብ ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ያገለግላሉ። ሰባው ዓመትም በተፈጸመ ጊዜ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ያንን ሕዝብ ስለ ኃጢአታቸው እቀጣለሁ፥ ይላል ጌታ፥ የከለዳውያንንም ምድር ለዘለዓለም ባድማ አደርጋታለሁ። በእርሷም ላይ የተናገርሁትን ቃሎቼን ሁሉ፥ ማለት ኤርምያስ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ትንቢት የተናገረውን በዚህች መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ፥ በዚያች ምድር አመጣለሁ። ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት ደግሞ እነርሱን ይገዙአቸዋል፤ እኔም እንደ አድራጎታቸውና እንደ እጃቸው ሥራ እከፍላቸዋለሁ።