መሳፍንት 6:6-18

መሳፍንት 6:6-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከም​ድ​ያ​ምም ፊት የተ​ነሣ እስ​ራ​ኤል እጅግ ተቸ​ገሩ፤ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጮኹ። እን​ዲ​ህም ሆነ፤ የእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች በም​ድ​ያም ምክ​ን​ያት ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በጮኹ ጊዜ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ወደ እስ​ራ​ኤል ልጆች ነቢይ ላከ፤ እር​ሱም አለ፥ “የእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፦ እኔ ከግ​ብፅ ምድር አወ​ጣ​ኋ​ችሁ፤ ከባ​ር​ነ​ትም ቤት አስ​ለ​ቀ​ቅ​ኋ​ችሁ፤ ከግ​ብ​ፃ​ው​ያ​ንም እጅ ከሚ​ጋ​ፉ​አ​ች​ሁም ሁሉ እጅ አዳ​ን​ኋ​ችሁ፤ ከፊ​ታ​ች​ሁም አሳ​ደ​ድ​ኋ​ቸው፤ ሀገ​ራ​ቸ​ው​ንም ሰጠ​ኋ​ችሁ፤ እና​ን​ተ​ንም፦ እኔ አም​ላ​ካ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ነኝ፤ በም​ድ​ራ​ቸው የተ​ቀ​መ​ጣ​ች​ሁ​ባ​ቸ​ውን የአ​ሞ​ሬ​ዎ​ና​ው​ያ​ንን አማ​ል​ክት አት​ፍሩ አል​ኋ​ችሁ። እና​ንተ ግን ቃሌን አል​ሰ​ማ​ች​ሁም።” የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ መጥቶ በኤ​ፍ​ራታ ባለ​ችው ለኤ​ዝሪ አባት ለኢ​ዮ​አስ በነ​በ​ረ​ችው ዛፍ በታች ተቀ​መጠ፤ ልጁም ጌዴ​ዎን ከም​ድ​ያ​ማ​ው​ያን ለማ​ሸሽ በወ​ይን መጭ​መ​ቂ​ያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ ለእ​ርሱ ተገ​ልጦ፥ “አንተ ጽኑዕ ኀያል ሰው! እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከአ​ንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴ​ዎ​ንም፥ “ጌታዬ ሆይ! እሺ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረ​ሰ​ብን? አባ​ቶ​ቻ​ች​ንስ፦ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከግ​ብፅ አው​ጥ​ቶ​ናል ብለው ይነ​ግ​ሩን የነ​በረ ተአ​ም​ራት ወዴት አለ? አሁን ግን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ትቶ​ናል፤ በም​ድ​ያም እጅም አሳ​ልፎ ሰጥ​ቶ​ናል” አለው። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ ወደ እርሱ ተመ​ለ​ከ​ተና፥ “በዚህ በጕ​ል​በ​ትህ ሂድ፤ እስ​ራ​ኤ​ል​ንም ከም​ድ​ያም እጅ ታድ​ና​ቸ​ዋ​ለህ፤ እነሆ፥ ልኬ​ሃ​ለሁ” አለው። እር​ሱም፥ “ጌታ ሆይ! እሺ፥ እስ​ራ​ኤ​ልን በምን አድ​ና​ለሁ? ወገኔ በም​ናሴ ነገድ ዘንድ ጥቂ​ቶች ናቸው፤ እኔም በአ​ባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ” አለው። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከአ​ንተ ጋር ነው፤ ምድ​ያ​ም​ንም እንደ አንድ ሰው አድ​ር​ገህ ታጠ​ፋ​ለህ” አለው። ጌዴ​ዎ​ንም፥ “በፊ​ትህ ሞገ​ስን ካገ​ኘሁ፥ የም​ት​ና​ገ​ረ​ኝም አንተ እንደ ሆንህ ምል​ክት አድ​ር​ግ​ልኝ፤ ወደ አን​ተም እስ​ክ​መ​ለስ ድረስ፥ መሥ​ዋ​ዕ​ቴ​ንም አም​ጥቼ እስ​ካ​ቀ​ር​ብ​ልህ ድረስ፥ እባ​ክህ፥ ከዚህ አት​ሂድ” አለው። እር​ሱም፥ “እስ​ክ​ት​መ​ለስ ድረስ እቈ​ያ​ለሁ” አለው።

መሳፍንት 6:6-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ምድያማውያን እስራኤላውያንን ችግር ላይ ስለ ጣሏቸው፣ ይረዳቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። ከምድያማውያን ጥቃት የተነሣ እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔር አንድ ነቢይ ላከላቸው፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከባርነት ቤት ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ነኝ። ከግብጻውያን እጅ ታደግኋችሁ፤ ከሚያስጨንቋችሁ ሁሉ አዳንኋችሁ፤ እነርሱንም ከፊታችሁ አሳድጄ አስወጣኋቸው፤ ምድራቸውንም ሰጠኋችሁ። እናንተንም፣ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ በምድራቸው ላይ የምትኖሩባቸው የአሞራውያንን አማልክት አታምልኩ’ አልኋችሁ፤ እናንተ ግን አላዳመጣችሁኝም።” የእግዚአብሔር መልአክ ዖፍራ ወደምትባል መንደር መጥቶ፣ በአቢዔዝራዊው በኢዮአስ ዕርሻ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን፣ ምድያማውያን እንዳያዩበት ደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴውን ይወቃ ነበር። የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ፣ “አንተ ኀያል ጦረኛ እነሆ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነው” አለው። ጌዴዎን መልሶ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ? ‘እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር አውጥቶናል’ በማለት አባቶቻችን የነገሩን ታምራት የት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፤ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፣ “ሂድ፤ ባለህ ኀይል እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን?” አለው። ጌዴዎንም፣ “ጌታ ሆይ፤ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተ ሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለ። እግዚአብሔርም፣ “በርግጥ እኔ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው። ጌዴዎን እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “አሁን በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ በርግጥ የምታነጋግረኝ አንተ ራስህ ለመሆንህ ምልክት ስጠኝ፤ ተመልሼ እስክመጣ፣ መሥዋዕቴንም አምጥቼ በፊትህ እስካቀርብ ድረስ እባክህ አትሂድ።” እግዚአብሔርም፣ “እስክትመለስ እጠብቅሃለሁ” አለው።

መሳፍንት 6:6-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከምድያምም የተነሣ እስራኤል እጅግ ተጠቁ፥ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እንዲህም ሆነ፥ የእስራኤል ልጆች በምድያም ምክንያት ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ እስራኤል ልጆች ነቢይ ላከ፥ እርሱም አለ፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፥ ከባርነትም ቤት አስለቀቅኋችሁ፥ ከግብፃውያንም እጅ፥ ከሚጋፉአችሁም ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ፥ ከፊታችሁም አሳደድኋቸው፥ አገራቸውንም ሰጠኋችሁ፥ እናንተም፦ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ፥ በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራያውያንን አማልክት አትፍሩ አልኋችሁ። እናንተ ግን ድምፄን አልሰማችሁም። የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ በዖፍራ ባለችው ለአቢዔዝራዊው ለኢዮአስ በነበረችው በአድባሩ ዛፍ በታች ተቀመጠ፥ ልጁም ጌዴዎን ከምድያማውያን ለመሸሸግ በወይን መጠመቂያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር። የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጦ፦ አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው። ጌዴዎንም፦ ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ፦ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ? ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል አለው። እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፦ በዚህ በጉልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን፥ እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው። እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፥ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ አለው። እግዚአብሔርም፦ በእርግጥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታለህ አለው። እርሱም፦ በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ፥ የምትናገረኝም አንተ እንደ ሆንህ ምልክት አሳየኝ፥ ወደ አንተም እስክመለስ ድረስ፥ ቁርባኔንም አምጥቼ እስካቀርብልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ከዚህ አትላወስ አለው። እርሱም፦ እስክትመለስ ድረስ እቆያለሁ አለ።

መሳፍንት 6:6-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ በምድያማውያን ምክንያት ችግር ደረሰባቸው፤ እንዲረዳቸውም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እስራኤላውያን ከምድያማውያን እጅ ያድናቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ እስራኤል ሕዝብ አንድ ነቢይ ላከ፤ ያም ነቢይ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያመጣው መልእክት ይህ ነው፦ “እኔ በባርነት ከኖራችሁባት ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፤ ከግብጻውያንና በዚህች ምድር ከሚጨቊኑአችሁ ሕዝቦች ሁሉ አዳንኳችሁ፤ ከፊታችሁም አስወጣኋቸው፤ ምድራቸውንም ሰጠኋችሁ። እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩና አሁን ምድራቸውን የወረሳችኋቸውን የአሞራውያንን ባዕዳን አማልክት እንዳታመልኩ ነግሬአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን አልሰማችሁኝም።” ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ “ዖፍራ” ተብላ ወደምትጠራው መንደር መጥቶ ከአቢዔዜር ጐሣ የተወለደው የኢዮአስ ንብረት በሆነው የወርካ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ምድያማውያን እንዳያዩት ተሸሽጎ በወይን መጭመቂያው ስፍራ የስንዴ ነዶ ይወቃ ነበር። በዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና “አንተ ኀያልና ብርቱ ሰው! እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎንም እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ሆይ! ታዲያ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ ችግር እንዴት ሊደርስብን ቻለ? አባቶቻችን እንደ ነገሩን እግዚአብሔር ያደርገው የነበረ ድንቅ ሥራ ሁሉ ዛሬ የት አለ? ከግብጽ እንዴት እንዳወጣቸውም ነግረውን ነበር፤ ዛሬ ግን እግዚአብሔር እኛን በመተው እንደ ፈለጉ ያደርጉን ዘንድ ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጥቶናል።” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ሂድ፤ በዚህ ባለህ ብርቱ ኀይል ሁሉ በመጠቀም እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ አውጣ፤ እነሆ እኔ ራሴ ልኬሃለሁ” ሲል አዘዘው። ጌዴዎንም “ታዲያ እኔ እንዴት አድርጌ እስራኤልን ላድን እችላለሁ? ወገኔም ከምናሴ ነገድ መካከል እጅግ ደካማ ነው፤ እኔም ከቤተሰቤ መካከል በጣም አነስተኛ ነኝ” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም “እኔ ስለምረዳህ ይህን ማድረግ ትችላለህ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው ያኽል አድርገህ ታደቃቸዋለህ” አለው። ጌዴዎንም “በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፥ አንተ በእርግጥ እግዚአብሔር መሆንህን የሚያስረዳ ምልክት ስጠኝ፤ ምግብ የሚሆን ቊርባን እስካመጣልህም ድረስ እባክህ ከዚህ ስፍራ አትሂድ” አለው። እግዚአብሔርም “አንተ እስክትመለስ ድረስ እቈያለሁ” አለው።

መሳፍንት 6:6-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ምድያማውያን እስራኤላውያንን ችግር ላይ ስለጣሏቸው፥ ይረዳቸው ዘንድ ወደ ጌታ ጮኹ። ከምድያማውያን ጥቃት የተነሣ እስራኤላውያን ወደ ጌታ ጮኹ። ጌታ አንድ ነቢይ ላከላቸው፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል ከባርነት ቤት ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ነኝ። ከግብፃውያን እጅ ታደግኋችሁ፤ ከሚያስጨንቋችሁ ሁሉ አዳንኋችሁ፤ እነርሱንም ከፊታችሁ አሳድጄ አስወጣኋቸው፤ ምድራቸውንም ሰጠኋችሁ።” እናንተንም፥ “‘እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ፤ በምድራቸው ላይ የምትኖሩባቸው የአሞራውያንን አማልክት አታምልኩ’ አልኋችሁ፤ እናንተ ግን አላዳመጣችሁኝም።” የጌታ መልአክ ዖፍራ ወደምትባል መንደር መጥቶ፥ በአቢዔዝራዊው በኢዮአስ ዕርሻ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን፥ ምድያማውያን እንዳያዩት ተደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴውን ይወቃ ነበር። የጌታ መልአክ ተገልጦለት “አንተ ኃያል ጦረኛ! እነሆ፥ ጌታ ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎን መልሶ፥ “ጌታዬ ሆይ ጌታ ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ? ‘ጌታ ከግብጽ ምድር አውጥቶናል’ በማለት አባቶቻችን የነገሩን ታምራት የት አለ? አሁን ግን ጌታ ትቶናል፤ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። በዚህ ጊዜ ጌታ ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፥ “ባለህ ኃይል ሂድ፤ እስራኤውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን? አለው” ጌዴዎንም፥ “ጌታ ሆይ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለ። ጌታም፥ “በእርግጥ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው። ጌዴዎን እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “አሁን በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ በእርግጥ የምታነጋግረኝ አንተ ራስህ ለመሆንህ ምልክት ስጠኝ፤ ተመልሼ እስክመጣ፥ መሥዋዕቴንም አምጥቼ በፊትህ እስካቀርብ ድረስ እባክህ አትሂድ።” ጌታም፥ “እስክትመለስ እጠብቅሃለሁ” አለው።