ያዕቆብ 1:13-27
ያዕቆብ 1:13-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ማንም ሲፈተን “በእግዚአብሔር እፈተናለሁ፤” አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኀጢአትን ትወልዳለች፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! አትሳቱ። በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፤ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። ለፍጥረቱ የበኵራት ዐይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን። ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና። ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፤ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው። ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።
ያዕቆብ 1:13-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ማንም ሲፈተን፣ “እግዚአብሔር ፈተነኝ” አይበል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፤ እርሱም ማንንም አይፈትንም፤ ነገር ግን እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞትም ከፀነሰች በኋላ ኀጢአትን ትወልዳለች፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ አትታለሉ። በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከላይ፣ ከሰማይ ብርሃናት አባት ይወርዳሉ፤ በእርሱ ዘንድ መለዋወጥ፣ ከመዞር የተነሣ የሚያርፍ ጥላም የለም። የፍጥረቱ በኵራት እንድንሆን በገዛ ፈቃዱ በእውነት ቃል ወለደን። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ይህን አስተውሉ፤ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ፣ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያመጣምና። ስለዚህ ርኩሰትንና ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ክፋትን አስወግዳችሁ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን፣ በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በትሕትና ተቀበሉ። ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ ሆናችሁ ራሳችሁን አታታልሉ። ቃሉን የሚሰማ፣ ነገር ግን የሚለውን የማይፈጽም ሰው ፊቱን በመስተዋት እንደሚያይ ሰው ነው፤ ራሱንም አይቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል፤ ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ ተመልክቶ የሚጸና፣ የሰማውን የሚያደርግና የማይረሳ ሰው በሥራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ፣ ልቡን እያሳተ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚል ሰው፣ ራሱን ያታልላል፤ ሃይማኖቱም ከንቱ ነው። በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳትና ከዓለም ርኩሰት ራስን መጠበቅ ነው።
ያዕቆብ 1:13-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ። በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን። ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና። ስለዚህ ርኵሰትና ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው። ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።
ያዕቆብ 1:13-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር በክፉ ነገር ስለማይፈተንና እንዲሁም እርሱ ማንንም ስለማይፈትን ሰው በሚፈተንበት ጊዜ “እግዚአብሔር ፈተነኝ” አይበል። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው የሚፈተነው በገዛ ራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ከዚህ በኋላ ምኞት ስትፀንስ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ስታድግ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! አትታለሉ! መልካም ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህም የሚመጣው እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ ከሌለበት ከብርሃን አባት ከእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር የፍጥረቱ ሁሉ መጀመሪያ እንድንሆን በገዛ ፈቃዱ በእውነት ቃል ወለደን። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ይህን አትርሱ፤ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፥ ለመናገርና ለቊጣም የዘገየ ይሁን። የሰው ቊጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያስገኝም። ስለዚህ ርኲሰትንና የክፋትንም ብዛት ሁሉ አስወግዳችሁ እግዚአብሔር በልባችሁ የተከለውንና ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን ቃል በትሕትና ተቀበሉ። ቃሉን በሥራ ላይ የምታውሉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያታለላችሁ ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ። ቃሉን ሰምቶ በሥራ ላይ የማያውለው ሰው የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት እንደሚያይ ሰው ነው፤ ይህ ሰው ፊቱን በመስተዋት ካየ በኋላ ይሄዳል፤ እንዴት እንደ ሆነም ወዲያውኑ ይረሳዋል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ መርምሮ በእርሱ የሚጸና፥ እርሱንም ሰምቶ መርሳት ሳይሆን፥ በሥራ ላይ የሚያውለው ሰው በሥራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይቈጣጠር እግዚአብሔርን አመልካለሁ የሚል ሰው ራሱን ያታልላል፤ የእርሱም አምልኮ ከንቱ ነው። በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ያልረከሰ ሃይማኖት “አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች፥ እንዲሁም ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳት፥ ራስንም ከዓለም ርኲሰት መጠበቅ ነው።”
ያዕቆብ 1:13-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ማንም ሲፈተን “እግዚአብሔር ፈተነኝ፤” አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! አትታለሉ! መልካም ስጦታ ሁሉ፥ ፍጹምም በረከት ሁሉ፥ እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ ከሌለበት ከላይ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። ለፍጥረቱ የበኵራት እንድንሆን በገዛ ፈቃዱ በእውነት ቃል ወለደን። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ይህን አትርሱ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፥ ለመናገርም የዘገየ፥ ለቁጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና። ስለዚህ ርኩሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያታለላችሁ፥ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማና የማያደርግ ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ፥ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው። በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ፥ “አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች፥ እንዲሁም ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳት፥ ራስንም ከዓለም ርኲሰት መጠበቅ ነው።”