ኢሳይያስ 57:15-19
ኢሳይያስ 57:15-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለዘለዓለም በአርያም የሚኖር ስሙም ቅዱሰ ቅዱሳን የሆነ፥ በቅዱሳን አድሮ የሚኖር፥ ለተዋረዱት ትዕግሥትን የሚሰጥ፥ ልባቸውም ለተቀጠቀጠ ሕይወትን የሚሰጥ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “መንፈስ ከእኔ ይወጣልና፥ የሁሉንም ነፍስ ፈጥሬአለሁና ለዘለዓለም አልቀስፋችሁም፤ ሁልጊዜም አልቈጣችሁም። ስለ ኀጢአቱ ጥቂት ጊዜ መከራ አመጣሁበት፤ ቀሠፍሁትም፤ ፊቴንም ከእርሱ መለስሁ፤ እርሱም አዘነ። እያዘነም ሄደ። ከዚህም በኋላ መንገዱን አይቻለሁ፤ ፈወስሁትም፤ አጽናናሁት፤ እውነተኛ ደስታንም ሰጠሁት። በሩቅም በቅርብም ላሉ በሰላም ላይ ሰላም ይሁን፤ እፈውሳቸውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
ኢሳይያስ 57:15-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከፍ ከፍ ያለውና ልዕልና ያለው እርሱ፣ ስሙም ቅዱስ የሆነው፣ ለዘላለም የሚኖረው እንዲህ ይላል፤ “የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት፣ ከፍ ባለውና በቅዱሱ ስፍራ እኖራለሁ፤ የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋር እሆናለሁ። የሰው መንፈስ በፊቴ እንዳይዝል፣ የፈጠርሁትም ሰው እስትንፋስ እንዳይቆም፣ ለዘላለም አልወቅሥም፤ ሁልጊዜም አልቈጣም። ኀጢአት ስለ ሞላበት ስግብግብነቱ ተቈጣሁት፤ ቀጣሁት፤ ፊቴንም በቍጣ ከእርሱ ሸሸግሁ፤ ያም ሆኖ በገዛ መንገዱ ገፋበት። መንገዶቹን አይቻለሁ፤ ቢሆንም እፈውሰዋለሁ፤ እመራዋለሁ፤ ለእርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱትም መጽናናትን እመልሳለሁ፤ በእስራኤል አልቃሾች ከንፈር ላይ ምስጋና እፈጥራለሁ። በቅርብና በሩቅ ላሉት ሰላም፣ ሰላም ይሁን፤ እኔ እፈውሳቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።
ኢሳይያስ 57:15-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለዘላለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል፦ የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ። መንፈስም የፈጠርሁትም ነፍስ ከፊቴ እንዳይዝል ለዘላለም አልጣላም፥ ሁልጊዜም አልቈጣም። ስለ ኃጢአቱ ጥቂት ጊዜ ተቆጥቼ ቀሠፍሁት፥ ፊቴን ሰውሬ ተቈጣሁ፥ እርሱም በልቡ መንገድ እያፈገፈገ ሄደ። መንገዱን አይቻለሁ እፈውሰውማለሁ፥ እመራውማለሁ፥ ለእርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱ መጽናናትን እመልሳለሁ። የከንፈሮችን ፍሬ እፈጥራለሁ፥ በሩቅም በቅርብም ላለው ሰላም ሰላም ይሁን፥ እፈውሰውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
ኢሳይያስ 57:15-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከፍተኛውና ከሁሉ የላቀው፥ ለዘለዓለም የሚኖር ቅዱሱ እንዲህ ይላል፦ “እኔ በተቀደሰና በከፍተኛ ቦታ፥ እንዲሁም ልባቸው ከተሰበረና መንፈሳቸው ትሑት ከሆኑት ጋር እኖራለሁ፤ ይኸውም ትሑት መንፈሳቸውንና የተሰበረ ልባቸውን ለማደስ ነው። እኔ ዘወትር ሰውን አልወቅስም፤ ሁልጊዜም አልቈጣም፤ ይህን ባደርግ ኖሮ፥ የፈጠርኳቸው ሰዎች መንፈሳቸው ይዝል ነበር። ክፉ በሆነው ስግብግብነታቸው ምክንያት በእነርሱ ላይ ተቈጥቼ ነበር፤ እንዲሁም እነርሱን ቀጥቼ ተለይቼአቸው ነበር፤ እነርሱም ወደ ራሳቸው መንገድ ተመለሱ። “እኔ ሥራቸውን ሁሉ ተመልክቼአለሁ፤ ይሁን እንጂ እፈውሳቸዋለሁ፤ እመራቸዋለሁ፤ እኔ ለእነርሱና ስለ እነርሱ ለሚያለቅሱት ሙሉ መጽናናትን እሰጣለሁ። በሩቅና በቅርብ ላሉትም ሁሉ ሰላም ይሁን! እኔ ሕዝቤን እፈውሳለሁ፤
ኢሳይያስ 57:15-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ለዘለዓለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል፦ የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ። መንፈስም የፈጠርሁትም ነፍስ ከፊቴ እንዳይዝል ለዘለዓለም አልጣላም፥ ሁልጊዜም አልቈጣም። ኃጢአት ስለ ሞላበት ስግብግብነቱ ተቈጣሁት፤ ቀጣሁት፤ ፊቴንም በቁጣ ከእርሱ ሰወርኩ፤ እርሱ ግን በመንገዱ ገፋበት። መንገዶቹን አይቻለሁ፤ ቢሆንም እፈውሰዋለሁ፤ እመራዋለሁ፤ ለእርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱትም መጽናናትን እሰጣለሁ። የከንፈሮችን ፍሬ እፈጥራለሁ፤ በሩቅም በቅርብም ላለው ሰላም ሰላም ይሁን፥ እፈውሰውማለሁ፥ ይላል ጌታ።