የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 40:21-31

ኢሳይያስ 40:21-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አላወቃችሁምን? አልሰማችሁምን? ከጥንት አልተነገራችሁምን? ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን? እርሱ ከምድር ክበብ በላይ በዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ ሕዝቦቿም እንደ አንበጣ ናቸው። ሰማያትን እንደ ድባብ ይዘረጋቸዋል፤ እንደ መኖሪያ ድንኳንም ይተክላቸዋል። አለቆችን ኢምንት፣ የዚህን ዓለም ገዦች እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋል። ተተክለው ምንም ያህል ሳይቈዩ፣ ተዘርተው ምንም ያህል ሳይሰነብቱ፣ ገና ሥር መስደድ ሳይጀምሩ አነፈሰባቸው፤ እነርሱም ደረቁ፤ ዐውሎ ነፋስም እንደ ገለባ ጠራርጎ ወሰዳቸው። ቅዱሱ፣ “ከማን ጋር ታወዳድሩኛላችሁ? የሚስተካከለኝስ ማን አለ?” ይላል። ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው። ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣ አንዳቸውም አይጠፉም። ያዕቆብ ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትላለህ? እስራኤል ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትናገራለህ? “መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች፤ ፍርዴም በአምላኬ ቸል ተብላለች” ለምን ትላለህ? አታውቅምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው። አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም። ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጕልበት ይጨምራል። ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ይታክታሉም፤ ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ። እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።

ኢሳይያስ 40:21-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አላ​ወ​ቃ​ች​ሁ​ምን? ወይስ አል​ሰ​ማ​ች​ሁ​ምን? ከጥ​ን​ትስ አል​ተ​ወ​ራ​ላ​ች​ሁ​ምን? ወይስ ምድር ከተ​መ​ሠ​ረ​ተች ጀምሮ አላ​ስ​ተ​ዋ​ላ​ች​ሁ​ምን? እርሱ የም​ድ​ርን ክበብ ያጸ​ናል፤ በእ​ር​ስ​ዋም የሚ​ኖ​ሩት እንደ አን​በጣ ናቸው፤ ሰማ​ያ​ትን እንደ መጋ​ረጃ የሚ​ዘ​ረ​ጋ​ቸው፥ እንደ ድን​ኳ​ንም ለመ​ኖ​ሪያ የሚ​ዘ​ረ​ጋ​ቸው፤ አለ​ቆ​ች​ንም የሚ​ገ​ዛ​ላ​ቸው እን​ዳ​ይ​ኖር የሚ​ያ​ደ​ርግ ምድ​ር​ንም እንደ ኢም​ንት የሚ​ያ​ደ​ር​ጋት እርሱ ነው። በእ​ር​ሱም ላይ ዛፉ​ንና ሣሩን፥ የማ​ይ​ቈ​ጠር ሌላ​ው​ንም ብዙ ፍጥ​ረት የፈ​ጠረ እርሱ ነው። ነፋ​ስም በነ​ፈ​ሰ​ባ​ቸው ጊዜ ይደ​ር​ቃሉ፤ ዐውሎ ነፋ​ስም እንደ ገለባ ይጠ​ር​ጋ​ቸ​ዋል። እን​ግ​ዲህ እተ​ካ​ከ​ለው ዘንድ በማን መሰ​ላ​ች​ሁኝ? ይላል ቅዱሱ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር። ዐይ​ና​ች​ሁን ወደ ሰማይ አን​ሥ​ታ​ችሁ ተመ​ል​ከቱ፤ ይህን ሁሉ የፈ​ጠረ ማን ነው? ከዋ​ክ​ብ​ት​ንም በሙሉ የሚ​ቈ​ጥ​ራ​ቸው እርሱ ነው፤ በየ​ጊ​ዜ​ያ​ቸው ያመ​ጣ​ቸ​ዋል፤ ሁሉ​ንም በየ​ስ​ማ​ቸው ይጠ​ራ​ቸ​ዋል፤ በክ​ብሩ ብዛ​ትና በች​ሎቱ ብር​ታት አን​ድስ እንኳ አይ​ታ​ጣ​ውም። ያዕ​ቆብ ሆይ፥ እስ​ራ​ኤ​ልም ሆይ፥ መን​ገዴ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ተሰ​ው​ራ​ለች፤ አም​ላ​ኬም ከእኔ ርቋል፤ ፍር​ዴ​ንም ትት​ዋል፤ ለምን ትላ​ለህ? ለም​ንስ እን​ዲህ ትና​ገ​ራ​ለህ? አሁ​ንም አላ​ወ​ቅ​ህ​ምን? አል​ሰ​ማ​ህ​ምን? እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የዘ​ለ​ዓ​ለም አም​ላክ፥ የም​ድ​ር​ንም ዳርቻ የፈ​ጠረ አም​ላክ ነው፤ አይ​ራ​ብም፤ አይ​ጠ​ማም፤ አይ​ደ​ክ​ምም፤ ማስ​ተ​ዋ​ሉም አይ​መ​ረ​መ​ርም። ለደ​ካ​ሞች ኀይ​ልን ይሰ​ጣል፤ መከራ የሚ​ቀ​በ​ሉ​ት​ንም አያ​ሳ​ዝ​ና​ቸ​ውም። ብላ​ቴ​ኖች ይራ​ባሉ፤ ጐል​ማ​ሶች ይታ​ክ​ታሉ፤ ጐበ​ዛ​ዝ​ቱም ፈጽሞ ይዝ​ላሉ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ተስፋ የሚ​ያ​ደ​ር​ጉና የሚ​ታ​ገሡ ግን ኀይ​ላ​ቸ​ውን ያድ​ሳሉ፤ እንደ ንስር ክንፍ ያወ​ጣሉ፤ ይሮ​ጣሉ፤ አይ​ታ​ክ​ቱ​ምም፤ ይሄ​ዳሉ፤ አይ​ራ​ቡ​ምም።

ኢሳይያስ 40:21-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አላወቃችሁምን? ወይስ አልሰማችሁምን? ከጥንትስ አልተወራላችሁምን? ወይስ ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን? እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀምጣል፥ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፥ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው፥ አለቆችንም እንዳልነበሩ፥ የምድርንም ፈራጆች እንደ ከንቱ ነገር የሚያደርጋቸው እርሱ ነው። ገና እንደ ተተከሉና እንደ ተዘሩ፥ በምድርም ሥር ገና እንደ ሰደዱ ወዲያውኑ ነፈሰባቸው፥ እነርሱም ደረቁ፥ ዐውሎ ነፋስም እንደ እብቅ ጠረጋቸው። እንግዲህ እተካከላለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ። ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፥ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፥ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም። ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤል ሆይ፦ መንገድህ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፥ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ለደካማ ኃይልን ይሰጣል ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፥ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፥ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፥ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፥ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም።

ኢሳይያስ 40:21-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከቶ ይህን አታውቁምን? አልሰማችሁምን? ከመጀመሪያው ጀምሮ አልተነገራችሁምን? ምድር ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ አላስተዋላችሁምን? እግዚአብሔር ከምድር ክበብ በላይ ዙፋኑን ዘርግቶ መቀመጡን ሰማይን እንደ መጋረጃ መወጠሩንና፥ እንደ መኖሪያ ድንኳን መዘርጋቱን የምድርም ሕዝቦች እንደ ፌንጣ አነስተኞች መሆናቸውን። እርሱ ልዑላንን ያዋርዳል፤ የዚህ ዓለም ገዢዎችንም እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋል። እነርሱ ገና እንደ በቀለና ሥር እንዳልሰደደ አዲስ ተክል ናቸው፤ እግዚአብሔር ነፋሱን ሲልክ ወዲያውኑ ይደርቃሉ፤ እንደ ገለባም በነው ይጠፋሉ። “ታዲያ፥ እኔን ከማን ጋር ታነጻጽሩኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታመሳስሉኛላችሁ?” ይላል ቅዱስ እግዚአብሔር። ቀና ብላችሁ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ የምታዩአቸውን ከዋክብት የፈጠረ ማን ነው? እርሱ እንደ ጦር ሠራዊት ይመራቸዋል፤ ምን ያኽል እንደ ሆኑም ቊጥራቸውን ያውቃል፤ እያንዳንዱንም በስሙ ይጠራዋል፤ የእርሱ ሥልጣንና ኀይል እጅግ ታላቅ ነው፤ ስለዚህ ከእነርሱ አንዱ እንኳ አይጠፋም። የያዕቆብ ዘር የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! “አካሄዴ ከእግዚአብሔር የተሰወረ ነው፤ መብቴም በእርሱ ዘንድ ችላ ተብሎብኛል፤” ብለህ ለምን ታማርራለህ? ከቶ አታውቅምን? ከቶስ አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘለዓለም አምላክ ነው፤ ዓለምን ሁሉ የፈጠረ እርሱ ነው፤ እርሱ ከቶ አይደክምም ወይም አይታክትም፤ ሐሳቡን መርምሮ ሊደርስበት የሚቻለው የለም። እርሱ ለደከሙት ብርታትን ይሰጣል፤ ለዛሉትም ኀይልን ይጨምራል። ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፥ ይታክታሉም፤ ጐልማሶችም ዝለው ይወድቃሉ፤ በእግዚአብሔር ተማምነው የሚኖሩ ግን ኀይላቸው ይታደስላቸዋል። እንደ ንሥር በክንፍ ይበራሉ፤ ይሮጣሉ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ አይደክሙም።

ኢሳይያስ 40:21-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አላወቃችሁም? ወይስ አልሰማችሁ ይሆን? ከጥንትስ አልተወራላችሁም? ወይስ ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁም? እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀምጣል፥ በእርሷም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፤ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው፥ መስፍኖችንም እንዳልነበሩ፥ የምድርንም ፈራጆች እንደ ከንቱ ነገር የሚያደርጋቸው እርሱ ነው። ገና እንደ ተተከሉና እንደ ተዘሩ፥ በምድርም ሥር ገና እንደ ሰደዱ ወዲያውኑ ነፈሰባቸው፥ እነርሱም ደረቁ፥ ዐውሎ ነፋስም እንደ እብቅ ጠረጋቸው። እንግዲህ የሚስተካከለኝ ማን አለ? ከማንስ ጋር አመሳሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ። ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በክህሎቱ ብርታት አንድ እንኳ አይጎለውም። ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤል ሆይ፦ “መንገዴ ከጌታ ተሰውራለች፥ ፍርዴም በአምላኬ ቸል ተብላለች” ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? አላወቅህም? አልሰማህም? ጌታ የዘለዓለም አምላክ ነው፤ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም አይመረመርም። ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፤ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ብላቴኖች ይደክማሉ፥ ይታክታሉም፤ ጐበዛትም ፈጽሞ ይወድቃሉ። ጌታን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።