ሆሴዕ 6:1-6
ሆሴዕ 6:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በመከራቸው ጊዜ በማለዳ ወደ እኔ ይገሰግሳሉ፤ እንዲህም ይላሉ፥ “ኑ፤ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናልና፥ እርሱም ይጠግነናል። ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፤ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን። እንወቀው፤ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል፤ እንደ ወገግታም ተዘጋጅቶ እናገኘዋለን፤ በምድርም ላይ እንደ መጀመሪያውና እንደ ኋለኛው ዝናብ ወደ እኛ ይመጣል። “ምሕረታችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና ኤፍሬም ሆይ! ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ! ምን ላድርግልህ? ስለዚህ ነቢያቶቻችሁን አጨድኋቸው፤ በአፌም ቃል ገደልኋቸው፤ ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል። ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለሁና።
ሆሴዕ 6:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰባብሮናል፤ እርሱም ይጠግነናል፤ እርሱ አቍስሎናል፤ እርሱም ይፈውሰናል። ከሁለት ቀን በኋላ ያነቃናል፤ በእርሱም ፊት እንድንኖር፣ በሦስተኛው ቀን ያስነሣናል። እግዚአብሔርን እንወቀው፤ የበለጠ እናውቀውም ዘንድ እንትጋ፤ እንደ ንጋት ብርሃን፣ በርግጥ ይገለጣል፤ ምድርን እንደሚያረሰርስ የበልግ ዝናብ፣ እንደ ክረምትም ዝናብ ወደ እኛ ይመጣል።” “ኤፍሬም ሆይ፤ ምን ላድርግህ? ይሁዳ ሆይ፤ ምን ላድርግህ? ፍቅራችሁ እንደ ማለዳ ጉም፣ እንደሚጠፋም የጧት ጤዛ ነው። ስለዚህ በነቢያቴ ቈራረጥኋችሁ፤ በአፌም ቃል ገደልኋችሁ፣ ፍርዴም እንደ መብረቅ በላያችሁ አበራ። ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እሻለሁና።
ሆሴዕ 6:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፥ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፥ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል። ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፥ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፥ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን። እንወቅ፥ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል፥ እንደ ወገግታም ተዘጋጅቶ እናገኘዋለን፥ እንደ ዝናብም ምድርንም እንደሚያጠጣ እንደ መጨረሻ ዝናብ ይመጣል። ምሕረታችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና ኤፍሬም ሆይ፥ ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ፥ ምን ላድርግልህ? ስለዚህ በነቢያት እጅ ቈረጥኋቸው፥ በአፌም ቃል ገደልኋቸው፥ ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል። ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለሁና።
ሆሴዕ 6:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሕዝቡ እንዲህ ይላል፦ “ኑ! ወደ እግዚአብሔር እንመለስ! እርሱ እንደ ሰበረን ይፈውሰናል፤ እርሱ እንዳቈሰለን ቊስላችንን ይጠግናል። በፊቱ በሕይወት እንኖር ዘንድ፥ ከሁለት ቀን በኋላ ያድሰናል፤ በሦስተኛው ቀን ያስነሣናል፤ ኑ፤ እግዚአብሔርን እንወቅ፤ ሳናወላውልም እንከተለው፤ እርሱም እንደ ንጋት ብርሃንና ምድርን እንደሚያረካ የበልግ ዝናም በእርግጥ ወደ እኛ ይመጣል።” እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! እናንተን ምን ላድርጋችሁ? እናንተ ለእኔ ያላችሁ ፍቅር እንደ ማለዳ ጉምና እንደ ጠዋት ጤዛ ፈጥኖ ይጠፋል። በነቢያቴ አማካይነት እንደማጠፋቸው በቃሌም አማካይነት እንደምገድላቸው አስጠነቀቅኋቸው፤ ስለዚህ ፍርዴ እንደ ንጋት ብርሃን ያንጸባርቃል። እኔ ከመሥዋዕት ይልቅ የማይለዋወጥ ፍቅርን እወዳለሁ፤ ከሚቃጠል መሥዋዕት ይልቅ እኔን እግዚአብሔርን ማወቃችሁን እመርጣለሁ።
ሆሴዕ 6:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም ይላሉ፦ “ኑ፥ ወደ ጌታ እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል። ከሁለት ቀን በኋላ ነፍስ ይዘራብናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፥ በፊቱም በሕይወት ያኖረናል። እኛም እንወቅ፤ ጌታን ለማወቅ እንትጋ፤ እንደ ንጋትም መገለጡ እርግጥ ነው፤ እንደ ዝናብ ምድርንም እንደሚያጠጣ እንደ በልግ ዝናብ ወደ እኛ ይመጣል።” ፍቅራችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና ኤፍሬም ሆይ! ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ! ምን ላድርግልህ? ስለዚህ በነቢያት እጅ ቆረጥኋቸው፥ በአፌም ቃላት ገደልኋቸው፤ ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል። ከመሥዋዕት ይልቅ ጽኑ ፍቅርን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወዳለሁና።