ዕብራውያን 8:1-10
ዕብራውያን 8:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከተናገርነውም ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን። እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር የተተከለች ናት። ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ያቀርብ ዘንድ ይሾማል፤ ለዚህም ደግሞ የሚያቀርበው አንዳች ነገር ይኖረው ዘንድ ይገባል። በምድር ቢሆን ኖሮ፥ ሊቀ ካህናት ባልሆነም ነበር፤ በኦሪት ሕግ መሥዋዕት የሚያቀርቡ ካህናት በእርስዋ አሉና። እነርሱም ሙሴ ድንኳኒቱን ሲሠራ ሳለ እንደ ተረዳ፥ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ፤ “በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ” ብሎት ነበርና። ዛሬ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የምትበልጠውን አገልግሎት ገንዘብ አደረገ፤ ለታላቂቱ ሥርዐትም መካከለኛ ሆነ፤ የምትበልጠውንም ተስፋ ሠራ። ፊተኛይቱ ያለ ነቀፋ ብትሆን ኖሮ ሁለተኛይቱን ባልፈለገም ነበር። ነገር ግን እነርሱን ነቅፎ እንዲህ አለ፥ “እነሆ፥ ለቤተ እስራኤልና ለቤተ ይሁዳም አዲስ ኪዳን የምሠራበት ዘመን ይመጣል ይላል እግዚአብሔር። እጃቸውን ይዤ ከምድረ ግብፅ ባወጣኋቸው ጊዜ ለአባቶቻቸው እንደ ገባሁት እንደዚያ ያለ ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልኖሩምና፤ እኔም ቸል ብያቸዋለሁና” ይላል እግዚአብሔር። ከእነዚያ ዘመናት በኋላ ለቤተ እስራኤል የምገባው ቃል ይህ ነው፦ ሕጌን በልባቸው አሳድራለሁ፤ በሕሊናቸውም እጽፈዋለሁ፤ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆኑኛል ይላል እግዚአብሔር።
ዕብራውያን 8:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ የምንናገረው ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም በሰው ሳይሆን በጌታ በተተከለችው፣ እውነተኛ ድንኳን በሆነችው ቤተ መቅደስ አገልጋይ ነው። እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት የሚሾመው መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ ነው፤ ስለዚህ ይህኛውም ሊቀ ካህን የሚያቀርበው ነገር ያስፈልገዋል። እርሱ በምድር ቢኖር ኖሮ ካህን ባልሆነም ነበር፤ ምክንያቱም በሕግ በታዘዘው መሠረት መባን የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ። እነርሱ ያገለገሉት በሰማይ ላለችው መቅደስ ምሳሌና ጥላ በሆነችው ውስጥ ነው፤ ሙሴ ድንኳኒቱን ለመሥራት በተነሣ ጊዜ፣ “በተራራው ላይ በተገለጠልህ ምሳሌ መሠረት መሥራትህን ልብ በል” የሚል ትእዛዝ የተሰጠው በዚህ ምክንያት ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ መካከለኛ የሆነበት ኪዳን ከቀድሞው እንደሚበልጥ ሁሉ፣ የተቀበለውም አገልግሎት ከእነርሱ አገልግሎት ይበልጣል፤ ይህም የተመሠረተው በተሻለ የተስፋ ቃል ላይ ነው። የመጀመሪያው ኪዳን ምንም ጕድለት ባይገኝበት ኖሮ፣ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ጕድለት በማግኘቱ እንዲህ ይላቸዋል፤ “ከእስራኤል ቤትና፣ ከይሁዳ ቤት ጋራ፣ አዲስ ኪዳን የምገባበት፣ ጊዜ ይመጣል፤ ይላል ጌታ። ከግብጽ አወጣቸው ዘንድ፣ እጃቸውን ይዤ በመራኋቸው ጊዜ፣ ከአባቶቻቸው ጋራ እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ ምክንያቱም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑም፤ እኔም ከእነርሱ ዘወር አልሁ፤ ይላል ጌታ። ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ ከእስራኤል ቤት ጋራ የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በአእምሯቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።
ዕብራውያን 8:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት። ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና፤ ስለዚህም ለዚህ ደግሞ የሚያቀርበው አንዳች ሊኖረው የግድ ነው። እንግዲህ በምድር ቢኖርስ፥ እንደ ሕግ መባን የሚያቀርቡት ስላሉ፥ ካህን እንኳ ባልሆነም፤ እነርሱም ሙሴ ድንኳኒቱን ሊሠራ ሳለ እንደ ተረዳ፥ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ። በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ ብሎት ነበርና። አሁን ግን በሚሻል ተስፋ ቃል በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ እንደሚሆን በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት አግኝቶአል። ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። እነርሱን እየነቀፈ ይላቸዋልና፦ እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል ይላል ጌታ፤ ከግብፅ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው ይላል ጌታ። ከዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፥ እኔም አምላክ እሆንላቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑልኛል።
ዕብራውያን 8:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ ከምንነጋገርባቸው ነገሮች ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማይ በልዑል እግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ የካህናት አለቃ አለን፤ እርሱ የሚያገለግለው እውነተኛ ድንኳን በሆነችው መቅደስ ነው፤ ይህች ድንኳን የተተከለችው በሰው እጅ ሳይሆን በጌታ ነው። እያንዳንዱ የካህናት አለቃ የሚሾመው መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ ነው፤ ስለዚህ ይህም ካህን የሚያቀርበው አንድ ነገር ሊኖረው ያስፈልጋል። በሕግ መሠረት መባን የሚያቀርቡ ካህናት ስላሉ እርሱ በምድር ቢሆን ኖሮ ካህን ባልሆነም ነበር፤ እነዚህ ካህናት የሚያገለግሉበት ድንኳን በሰማይ ለሚገኘው ምሳሌና ጥላ ብቻ ነው፤ ይህም የሆነው ሙሴ ድንኳኒቱን በሚሠራበት ጊዜ፤ እግዚአብሔር “በተራራው ላይ እንደ ተገለጠልህ ዐይነት ሁሉን ነገር በጥንቃቄ አድርግ” ብሎ ባዘዘው መሠረት ነው። አሁን ግን ኢየሱስ አማካይ አስማሚ የሆነበት ቃል ኪዳን ከአሮጌው ቃል ኪዳን የበለጠና በተሻለ ተስፋ ላይ የተመሠረተ እንደ መሆኑ ለእርሱ የተሰጠው አገልግሎት የበለጠ ነው። የመጀመሪያው ቃል ኪዳን ነቀፋ የሌለው ሆኖ ቢገኝ ኖሮ ሁለተኛው ቃል ኪዳን ባላስፈለገ ነበር። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ነቀፋ መኖሩን በማመልከት እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ ከእስራኤል ሕዝብና ከይሁዳ ሕዝብ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ጊዜ ይመጣል” ይላል ጌታ። ይህም ቃል ኪዳን እጃቸውን ይዤ ከግብጽ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ቃል ኪዳን ያለ አይደለም፤ እነርሱ በቃል ኪዳኔ ስላልጸኑ እኔም ችላ አልኳቸው ይላል ጌታ። “እነሆ፥ ከዚህ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን የሚከተለው ነው ይላል ጌታ፤ እኔ ሕጌን በአእምሮአቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።
ዕብራውያን 8:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ ከተናገርነው ነገር ዋናው ይህ ነው፦ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት። ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና፤ ስለዚህ ይህም ካህን የሚያቀርበው አንድ ነገር ሊኖረው ግድ ነው። እንግዲህ በምድር ቢኖርስ፥ እንደ ሕግ መባን የሚያቀርቡት ስላሉ፥ ካህን እንኳ ባልሆነም፤ ሙሴ ድንኳኒቱን ሊሠራ በነበረ ጊዜ፥ “በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ፤” ብሎት ነበርና፤ እነርሱ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ። አሁን ግን በተሻለ ተስፋ ቃል ስለ ተመሠረተ፥ መካከለኛ የሆነበት ኪዳን የተሻለ እንደሆነ ሁሉ፥ የተቀበለውም አገልግሎት ከእነርሱ አገልግሎት ይበልጣል፥፥ ፊተኛው ኪዳን ጉድለት ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። ጉድለት አግኝቶባቸዋልና እንዲህ ይላቸዋል፦ “እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምመሠርትበት ወራት ይመጣል፥ ይላል ጌታ፤ ከግብጽ ምድር ለማውጣት እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና እኔም ቸል አልኳቸው፤ ይላል ጌታ። ከዚያ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው፥ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆንላቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑልኛል።