ዕብራውያን 5:1-6
ዕብራውያን 5:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኀጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና። እርሱ ራሱም ደካማ ነውና ባለማወቃቸው ከሳቱ ሰዎች ጋር መከራን ሊቀበል ይችላል። በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥዋዕትን ስለ ኀጢአት ማቅረብ ይገባዋል። እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር፥ ማንም ለራሱ ክብርን የሚወስድ የለም። እንዲሁ ክርስቶስም ሊቀ ካህናት ይሆን ዘንድ ራሱን ያከበረ አይደለም፤ ነገር ግን፥ “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔም ዛሬ ወለድሁህ” ያለው እርሱ ራሱ ነው። ዳግመኛም፥ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘለዓለም ካህን አንተ ነህ” ይላል።
ዕብራውያን 5:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት ከሰዎች መካከል ይመረጣል፤ የእግዚአብሔርም በሆነው ነገር ላይ ሰዎችን በመወከል ለኀጢአት የሚሆነውን መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ ይሾማል። እርሱ ራሱ ድካም ያለበት በመሆኑ፣ አላዋቂ ለሆኑትና ለሚባዝኑት ሊራራላቸው ይችላል። ስለ ራሱ ኀጢአትና ስለ ሌሎች ሰዎች ኀጢአት መሥዋዕት ማቅረብ የተገባው በዚሁ ምክንያት ነው። አሮን እንደ ተጠራ በእግዚአብሔር መጠራት አለበት እንጂ፣ ይህን ክብር ለራሱ የሚወስድ ማንም የለም። እንዲሁም ክርስቶስ ሊቀ ካህናት የመሆንን ክብር ለራሱ አልወሰደም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር፣ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ አባት ሆንሁህ” አለው። እንዲሁም በሌላ ስፍራ፣ “እንደ መልከጼዴቅ ሹመት፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ይላል።
ዕብራውያን 5:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤ እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፤ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መስዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል። እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም። እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን፦ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፤ እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ፦ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ይላል።
ዕብራውያን 5:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እያንዳንዱ የካህናት አለቃ ከሰዎች መካከል ተመርጦ ከእግዚአብሔር ጋር በሚያገናኛቸው ጉዳይ በሰዎች ፋንታ ሆኖ መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ ይሾማል። እርሱ ራሱ ድካም ያለበት ስለ ሆነ አላዋቂዎችንና ስሕተተኞችን በርኅራኄ ሊመለከታቸው ይችላል። እርሱ ራሱም በደካማነቱ ምክንያት የኃጢአት ይቅርታን የሚያስገኝ መሥዋዕትን ማቅረብ የሚገባው ለሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ለራሱም ጭምር ነው። እንደ አሮን በእግዚአብሔር የተጠራ ካልሆነ በቀር ማንም ይህን ክብር በገዛ ራሱ አያገኝም። እንዲሁም ክርስቶስ የካህናት አለቃ የመሆንን ክብር በገዛ ራሱ አልወሰደም፤ ነገር ግን እርሱ የካህናት አለቃ የመሆንን ክብር ያገኘው፥ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ” ካለው ከእግዚአብሔር ነው። በሌላም ስፍራ እግዚአብሔር፥ “እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ይላል።
ዕብራውያን 5:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኅጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤ እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚሳሳቱት ሊራራላቸው ይችላል፤ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል። እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ካልተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም። እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም፤ ነገር ግን “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤” ያለው እርሱ ነው፤ እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ “አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ” ይላል።