የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዕብራውያን 5:1-14

ዕብራውያን 5:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሊቀ ካህ​ናት ሁሉ ስለ ኀጢ​አት መባ​ንና መሥ​ዋ​ዕ​ትን ሊያ​ቀ​ርብ ከሰው ተመ​ርጦ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በሆ​ነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾ​ማ​ልና። እርሱ ራሱም ደካማ ነውና ባለ​ማ​ወ​ቃ​ቸው ከሳቱ ሰዎች ጋር መከ​ራን ሊቀ​በል ይች​ላል። በዚ​ህም ምክ​ን​ያት ስለ ሕዝብ እን​ደ​ሚ​ያ​ቀ​ርብ እን​ዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥ​ዋ​ዕ​ትን ስለ ኀጢ​አት ማቅ​ረብ ይገ​ባ​ዋል። እንደ አሮ​ንም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከተ​ጠራ በቀር፥ ማንም ለራሱ ክብ​ርን የሚ​ወ​ስድ የለም። እን​ዲሁ ክር​ስ​ቶ​ስም ሊቀ ካህ​ናት ይሆን ዘንድ ራሱን ያከ​በረ አይ​ደ​ለም፤ ነገር ግን፥ “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔም ዛሬ ወለ​ድ​ሁህ” ያለው እርሱ ራሱ ነው። ዳግ​መ​ኛም፥ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘ​ለ​ዓ​ለም ካህን አንተ ነህ” ይላል። እር​ሱም ሥጋ ለብሶ በዚህ ዓለም በነ​በ​ረ​በት ጊዜ፥ በታ​ላቅ ጩኸ​ትና እንባ ከሞት ሊያ​ድ​ነው ወደ​ሚ​ች​ለው ጸሎ​ት​ንና ምል​ጃን አቀ​ረበ፤ ጽድ​ቁ​ንም ሰማው። ልጅም ቢሆን መከ​ራን ስለ ተቀ​በለ መታ​ዘ​ዝን ዐወቀ። ከተ​ፈ​ጸ​መም በኋላ ለሚ​ታ​ዘ​ዝ​ለት ሁሉ ሕይ​ወ​ትን የሚ​ሰጥ የዘ​ለ​ዓ​ለም መድ​ኅን ሆነ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘ​ለ​ዓ​ለም ሊቀ ካህ​ናት አለው። ስለ እር​ሱም የም​ን​ና​ገ​ረው ብዙ ነገር አለን፤ ጆሮ​ዎ​ቻ​ች​ሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልን​ተ​ረ​ጕ​መው ጭንቅ ነው። መም​ህ​ራን ልት​ሆኑ ሲገ​ባ​ችሁ፥ ካመ​ና​ችሁ ጀምሮ በት​ም​ህ​ርት ላይ የቈ​ያ​ችሁ ስለ ሆነ፥ እስከ ዛሬም ገና የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን የቃ​ሉን መጀ​መ​ሪያ ትም​ህ​ርት ሊያ​ስ​ተ​ም​ሩ​አ​ችሁ ትወ​ዳ​ላ​ችሁ፤ ወተ​ት​ንም ሊግ​ቱ​አ​ችሁ ትሻ​ላ​ችሁ፤ ጽኑ ምግ​ብ​ንም አይ​ደ​ለም። ወተ​ትን የሚ​ጋት ሁሉ ሕፃን ስለ​ሆነ፥ የጽ​ድ​ቅን ቃል ሊያ​ውቅ አይ​ሻም። ጠን​ካራ ምግብ ግን መል​ካ​ሙ​ንና ክፉ​ዉን ለመ​ለ​የት በሥ​ራ​ቸው የለ​መደ ልቡና ላላ​ቸው ለፍ​ጹ​ማን ሰዎች ነው።

ዕብራውያን 5:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኅጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤ እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚሳሳቱት ሊራራላቸው ይችላል፤ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል። እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ካልተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም። እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም፤ ነገር ግን “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤” ያለው እርሱ ነው፤ እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ “አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ” ይላል። እርሱም ሥጋ ለብሶ በምድር በሚመላለስ ጊዜ፥ ከሞት ሊያድነው ወደሚችል፥ ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤ ስለ ጻድቅ ፍርሃቱም ጸሎቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ፍጹም ሆኖ ከተገኘም በኋላ ለሚታዘዙት ሁሉ ለዘለዓለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው። በእግዚአብሔርም እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ተጠራ። ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፤ ለማድመጥ በድንዛዜ ላይ ስለ ሆናችሁ፥ ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው። እስከ አሁን በነበረው ጊዜ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ እንደገና የእግዚአብሔር ቃላት የመጀመሪያውን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ ሰው ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅም፤ ጠንካራ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ግን መልካሙንና ክፉውን የመለየት ልምድ ያላቸው ብስለት ያላቸው ሰዎች ናቸው።

ዕብራውያን 5:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት ከሰዎች መካከል ይመረጣል፤ የእግዚአብሔርም በሆነው ነገር ላይ ሰዎችን በመወከል ለኀጢአት የሚሆነውን መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ ይሾማል። እርሱ ራሱ ድካም ያለበት በመሆኑ፣ አላዋቂ ለሆኑትና ለሚባዝኑት ሊራራላቸው ይችላል። ስለ ራሱ ኀጢአትና ስለ ሌሎች ሰዎች ኀጢአት መሥዋዕት ማቅረብ የተገባው በዚሁ ምክንያት ነው። አሮን እንደ ተጠራ በእግዚአብሔር መጠራት አለበት እንጂ፣ ይህን ክብር ለራሱ የሚወስድ ማንም የለም። እንዲሁም ክርስቶስ ሊቀ ካህናት የመሆንን ክብር ለራሱ አልወሰደም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር፣ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ አባት ሆንሁህ” አለው። እንዲሁም በሌላ ስፍራ፣ “እንደ መልከጼዴቅ ሹመት፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ይላል። ኢየሱስ በዚህ ምድር በኖረበት ዘመን ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው ጸሎትንና ልመናን ከታላቅ ጩኸትና ከእንባ ጋር አቀረበ፤ ፍጹም ትሑት ሆኖ በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት። የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም እንኳ፣ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ በዚህም ፍጹም ሆኖ ከተገኘ በኋላ፣ እርሱን ለሚታዘዙ ሁሉ የዘላለም ድነት ምክንያት ሆነላቸው፤ እንደ መልከጼዴቅ ሹመትም ሊቀ ካህናት ተብሎ በእግዚአብሔር ተሾመ። ስለዚህ ጕዳይ የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፤ ነገር ግን ለመማር ዳተኛ ስለ ሆናችሁ ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው። በዚህ ጊዜ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፣ ገና የእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያ ትምህርት የሚያስተምራችሁ ሰው ያስፈልጋችኋል፤ የሚያስፈልጋችሁም ጠንካራ ምግብ ሳይሆን ወተት ነው። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለሆነ፣ ከጽድቅ ትምህርት ጋር ገና አልተዋወቀም። ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳቸውን ላስለመዱ፣ ለበሰሉ ሰዎች ነው።

ዕብራውያን 5:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤ እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፤ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መስዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል። እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም። እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን፦ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፤ እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ፦ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ይላል። እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው። ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው። ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።

ዕብራውያን 5:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እያንዳንዱ የካህናት አለቃ ከሰዎች መካከል ተመርጦ ከእግዚአብሔር ጋር በሚያገናኛቸው ጉዳይ በሰዎች ፋንታ ሆኖ መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ ይሾማል። እርሱ ራሱ ድካም ያለበት ስለ ሆነ አላዋቂዎችንና ስሕተተኞችን በርኅራኄ ሊመለከታቸው ይችላል። እርሱ ራሱም በደካማነቱ ምክንያት የኃጢአት ይቅርታን የሚያስገኝ መሥዋዕትን ማቅረብ የሚገባው ለሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ለራሱም ጭምር ነው። እንደ አሮን በእግዚአብሔር የተጠራ ካልሆነ በቀር ማንም ይህን ክብር በገዛ ራሱ አያገኝም። እንዲሁም ክርስቶስ የካህናት አለቃ የመሆንን ክብር በገዛ ራሱ አልወሰደም፤ ነገር ግን እርሱ የካህናት አለቃ የመሆንን ክብር ያገኘው፥ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ” ካለው ከእግዚአብሔር ነው። በሌላም ስፍራ እግዚአብሔር፥ “እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ይላል። ኢየሱስ ሰው ሆኖ በዚህ ምድር በኖረበት ጊዜ ከሞት ሊያድነው ወደሚችል አምላክ በታላቅ ጩኸትና በብዙ እንባ ጸሎትንና ልመናን አቀረበ፤ በትሕትና ራሱን ታዛዥ በማድረጉ እግዚአብሔር ጸሎቱን ሰማው። የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም እንኳ በተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ። ፍጹም ሆኖ ከተገኘም በኋላ ለሚታዘዙት ሁሉ ለዘለዓለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው። ይህም እግዚአብሔር በመልከ ጼዴቅ የክህነት ሹመት ዐይነት የካህናት አለቃ አድርጎ ሾመው። ስለዚህ ጉዳይ የምንናገረው ብዙ ነገር አለ፤ ነገር ግን የማስተዋል ችሎታችሁ አነስተኛ ስለ ሆነ ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው። እስከ አሁን በነበረው ጊዜ እናንተ አስተማሪዎች መሆን በተገባችሁ ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያውን ትምህርት ሌላ ሰው እንደገና እንዲያስተምራችሁ ያስፈልጋል፤ በዚህ ዐይነት የሚያስፈልጋችሁ ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ መልካም ነገርን ከክፉ የመለየት ትምህርት አልተለማመደም። ጠንካራ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ግን መልካሙንና ክፉውን የመለየት ልምድ ያላቸው ትላልቅ ሰዎች ናቸው።