ዕብራውያን 4:1-16
ዕብራውያን 4:1-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ አንፍራ፤ ወደ ዕረፍቱም እንድንገባ ትእዛዙን አንተው፤ ከእናንተም ምንአልባት በተለመደ ስሕተት የሚገኝና የሚጸና ቢኖር ወደ ዕረፍቱ እንዲገባ የሚተዉት አይምሰለው። ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛም የምሥራች ተሰብኮልናል፤ ነገር ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም። ሥራዉ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ቢፈጸም፥ “እንግዲህ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቍጣዬ ማልሁ” እንዳለ እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን። ስለ ሰባተኛውም ቀን፥ “እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ” ብሎአልና። ዳግመኛም፥ “ወደ ዕረፍቴ አይገቡም” ብሎአል። እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ መንገድ ስለ ነበራቸው ቀድሞም የምሥራች የተሰበከላቸው ባለ መታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ፦ “ዛሬ ቃሉን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ፤” በፊት እንደ ተባለ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር፥ “ዛሬ” ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል። ኢያሱ አሳርፎአቸው ቢሆን ኖሮስ፥ ከብዙ ዘመን በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረም ነበር። እንኪያስ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚገቡበት ጸንቶ የሚኖር ዕረፍት እንዳለ ታወቀ። ወደ ዕረፍቱ የገባስ እግዚአብሔር ከሥራው እንደ ዐረፈ፥ እነሆ፥ እርሱ ከሥራው ሁሉ ዐረፈ። እንግዲህ እንደ እነዚያ እንደ ካዱት እንዳንወድቅ፥ ወደ ዕረፍቱ እንገባ ዘንድ እንፋጠን። የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፤ የሚሠራም ሁለት ልሳን ካለው ሰይፍም ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስንም፥ ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፤ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል። እኛን በሚቈጣጠር በእርሱ በዐይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም። እንግዲህ ወደ ሰማያት የወጣ ታላቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን፤ በእርሱ በማመን ጸንተን እንኑር። ሊቀ ካህናታችን ለድካማችን መከራ መቀበልን የማይችል አይደለምና፤ ነገር ግን ከብቻዋ ከኀጢአት በቀር እኛን በመሰለበት ሁሉ የተፈተነ ነው። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል፥ በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፥ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።
ዕብራውያን 4:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት የተሰጠው ተስፋ አሁንም የተጠበቀ ስለሆነ፣ ከእናንተ ማንም ለዚያ ሳይበቃ እንዳይቀር እንጠንቀቅ፤ ለእነዚያ እንደ ተሰበከ ለእኛም ደግሞ የምሥራቹ ቃል ተሰብኮልናልና። ነገር ግን ሰሚዎቹ ቃሉን ከእምነት ጋር ስላላዋሐዱት አልጠቀማቸውም። እኛ ያመንነው ግን ወደዚያ ዕረፍት እንገባለን፤ እግዚአብሔርም፣ “ስለዚህ በቍጣዬ እንዲህ ብዬ ማልሁ፤ ‘ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም’ ” ብሏል። ይሁን እንጂ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የእርሱ ሥራ ተከናውኗል። ስለ ሰባተኛውም ቀን በአንድ ስፍራ፣ “በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ ዐረፈ” ብሏልና። ቀደም ባለው ክፍል ደግሞ፣ “ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም” ይላል። ወደ ዕረፍቱ ገና የሚገቡ አንዳንዶች አሉ፤ ቀድሞ የምሥራቹ ቃል የተሰበከላቸው ባለመታዘዛቸው ምክንያት ወደ ዕረፍት አልገቡም። ስለዚህ እግዚአብሔር፣ “ዛሬ” ብሎ እንደ ገና አንድን ቀን ወሰነ፤ ይህም ከብዙ ዘመን በኋላ በዳዊት በኩል፣ “ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣ ልባችሁን አታደንድኑ” ተብሎ ቀደም ሲል እንደ ተነገረው ነው። ኢያሱ ዕረፍትን ሰጥቷቸው ቢሆን ኖሮ፣ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር። ስለዚህ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ገና ቀርቶለታል፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት የሚገባ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፣ እርሱም ደግሞ ከሥራው ያርፋል። እንግዲህ ማንም የእነዚያን አለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ፣ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ። የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል። ከእግዚአብሔር ዐይን የተሰወረ ምንም ፍጥረት የለም፤ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት በሚገባን በእርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው። እንግዲህ ወደ ሰማያት ያረገ ታላቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፣ እምነታችንን አጥብቀን እንያዝ። በድካማችን የማይራራልን ሊቀ ካህናት የለንምና፤ ነገር ግን እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአት አልሠራም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።
ዕብራውያን 4:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት ተስፋ ገና ቀርቶልን ከሆነ፥ ምናልባት ከእናንተ ማንም የማይበቃ መስሎ እንዳይታይ እንፍራ። ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም። ሥራው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ቢፈጸም፦ እንዲህ፦ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቁጣዬ ማልሁ እንዳለ፥ እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን። ስለ ሰባተኛው ቀን በአንድ ስፍራ፦ እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ ብሎአልና፤ በዚህ ስፍራም ደግሞ፦ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም። እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ ስለ ቀሩ፥ ቀድሞም የምስራች የተሰበከላቸው ባለመታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ፦ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ በፊት እንደ ተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር፦ ዛሬ ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል። ኢያሱ አሳርፎአቸው ኖሮ ቢሆንስ፥ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር። እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል። ወደ ዕረፍቱ የገባ፥ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፥ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና። እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ። የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም። እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።
ዕብራውያን 4:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ እርሱ ወደሚሰጠን የዕረፍት ቦታ ለመግባት የተቀበልነው ተስፋ ገና የጸና ስለ ሆነ ከእናንተ ማንም ወደዚህ የዕረፍት ቦታ የመግባት ዕድል ሳያገኝ እንዳይቀር ሁላችንም እንጠንቀቅ። መልካሙን ዜና እነርሱ እንደ ሰሙት እኛም ሰምተነዋል፤ ነገር ግን እነርሱ የሰሙትን ቃል በእምነት ስላልተቀበሉት አልጠቀማቸውም። የእርሱ ሥራ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተጠናቀቀ ቢሆንም እንኳ፦ “እኔ ወደምሰጣቸው የዕረፍት ቦታ ከቶ አይገቡም ብዬ በቊጣዬ ምዬአለሁ” እንዳለው አሁንም እኛ የምናምነው ወደዚያ እግዚአብሔር ወደሚሰጠን የዕረፍት ቦታ እንገባለን፤ ስለ ሰባተኛው ቀን በአንድ ስፍራ “እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ” ተብሎ ተጽፎአል። እንዲሁም በዚሁ ስፍራ ላይ እንደገና “እኔ ወደምሰጣቸው የዕረፍት ቦታ ከቶ አይገቡም” ይላል። እነዚያ መልካሙን ዜና በመጀመሪያ የሰሙት ባለመታዘዛቸው እግዚአብሔር ወደሚሰጣቸው የዕረፍት ቦታ አልገቡም፤ ሆኖም ወደዚያ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው አንዳንዶች ነበሩ። ይህም አስቀድሞ እንደተባለው “ዛሬ ድምፁን ስትሰሙ፥ ልባችሁን እምቢተኛ አታድርጉ።” ሲል እግዚአብሔር ከብዙ ዘመን በኋላ በዳዊት አማካይነት በተናገረው ቃል “ዛሬ” ተብሎ የተጠራው ቀን በመወሰኑ ተረጋግጦአል። ኢያሱ የዕረፍትን ቦታ ሰጥቶአቸው ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር እንደገና “ዛሬ” በማለት ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር። እንግዲህ ለእግዚአብሔር ሕዝብ የሰንበትን ዕረፍት የመሰለ ዕረፍት ገና ይቀረዋል፤ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ እንዲሁም እግዚአብሔር ወደሚሰጠው ዕረፍት የሚገባ ከሥራው ያርፋል። ስለዚህ ማንም የእነዚያን ሰዎች አለመታዘዝ ተከትሎ እንዳይወድቅ ወደ እግዚአብሔር የዕረፍት ቦታ ለመግባት እንትጋ። የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው፤ ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፥ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ የሚቈራርጥ ነው፤ በልብ ውስጥ የተሰወረውንም ሐሳብና ምኞት መርምሮ የሚፈርድ ነው። ከእግዚአብሔር ፊት የሚሰወር ምንም ፍጥረት የለም፤ በእርሱ ዐይን ፊት ሁሉ ነገር ግልጥና ዕርቃኑን ሆኖ የሚታይ ነው፤ እኛም መልስ መስጠት የሚገባን በእርሱ ፊት ነው። እንግዲህ ሰማያትን ዘልቆ ወደ ላይ ወደ ሰማይ የወጣ ታላቅ የካህናት አለቃ ስላለን እምነታችንን አጥብቀን እንያዝ፤ የካህናት አለቃውም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ነው። እኛ ያለን የካህናት አለቃ በድካማችን ሊራራልን የሚችል ነው፤ እርሱ በሁሉ ነገር እንደ እኛ ተፈተነ፤ ሆኖም ምንም ኃጢአት አልሠራም። እንግዲህ ምሕረት እንድንቀበልና ርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ጸጋ እንድናገኝ ጸጋው ወደሚገኝበት ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ያለ አንዳች ፍርሀት እንቅረብ።
ዕብራውያን 4:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት ገና ተስፋ ቀርቶልን ከሆነ፥ ከእናንተ ማንም የማይበቃ መስሎ እንዳይታይ እንጠንቀቅ። የምሥራቹ ዜና ለእነርሱም እንደ ተነገረ ለእኛ ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም። ሥራው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ቢፈጸም “እንዲህ ‘ወደ ዕረፍቴ አይገቡም፤’ ብዬ በቁጣዬ ማልሁ፤” እንዳለ፥ እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን። ስለ ሰባተኛው ቀን በአንድ ስፍራ፥ “እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ፤” ብሎአልና፤ በዚህ ስፍራም ደግሞ “ወደ ዕረፍቴ አይገቡም፤” ይላል፥፥ ቀደም ብሎ የምሥራች የተሰበከላቸው ባለመታዘዝ ምክንያት ስላልገቡ፥ እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ ተጠብቆላቸዋል፥ ይህም አስቀድሞ እንደተባለው፥ “ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ፤” በፊት እንደተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር “ዛሬ” ብሎ አንድ ቀን እንደገና ይቀጥራል። ኢያሱ አሳርፎአቸው ኖሮ ቢሆንስ፥ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር። እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል። ወደ ዕረፍቱ የገባ፥ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና። እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ። የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፤ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም አሳብና ትኩረት ይመረምራል፤ በፊቱም የሚሰወር ምንም ፍጥረት የለም፤ እኛ መልስ መስጠት በሚገባን ከእርሱ ፊት ሁሉ ነገር ግልጥና ዕርቃኑን ሆኖ የሚታይ ነው። እንግዲህ በሰማያት የወጣ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። እኛ ያለን ሊቀ ካህናት በድካማችን ሊራራልን የሚችል ነው፤ እርሱ በሁሉ ነገር እንደ እኛ ተፈተነ፤ ሆኖም ምንም ኃጢአት አልሠራም። እንግዲህ ምሕረት እንድንቀበልና ርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ጸጋ እንድናገኝ፥ ጸጋው ወደሚገኝበት በመታመን እንቅረብ።