ዕብራውያን 13:1-8
ዕብራውያን 13:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የወንድማማች መዋደድ ይኑር። እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና። ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ፥ የተጨነቁትንም ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ። መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፥ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ፦ አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና፤ ስለዚህ በድፍረት፦ ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል? እንላለን። የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።
ዕብራውያን 13:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሁልጊዜ የእርስ በርስ የወንድማማችነት ፍቅር ይኑራችሁ፤ እንግዳ ተቀብሎ ማስተናገድን አትርሱ፤ እንደዚህ እንግዶችን እየተቀበሉ በማስተናገድ አንዳንድ ሰዎች ሳያውቁ መላእክትን ተቀብለው አስተናግደዋል። ከእነርሱ ጋር አብራችሁ እንደ ታሰራችሁ ያኽል ሆናችሁ እስረኞችን አስታውሱ፤ እናንተም እንደ እነርሱ መከራ የምትቀበሉ ያኽል ሆናችሁ መከራ የሚቀበሉትን አስቡ። ጋብቻ በሁሉ ዘንድ የተከበረ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን እግዚአብሔር ስለሚፈርድባቸው ባልና ሚስት ታማኝነትን በማጒደል ጋብቻን አያርክሱ። ከገንዘብ ፍቅር ራቁ፤ ያላችሁ ይብቃችሁ፤ እግዚአብሔር “ከቶ አልጥልህም፤ ፈጽሞም አልተውህም” ብሎአል። ስለዚህ በመተማመን፥ “ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን። የእግዚአብሔርን ቃል በመጀመሪያ የነገሩአችሁን መሪዎቻችሁን አትርሱ፤ የአኗኗራቸውንና የሥራቸውን ውጤት በማስታወስ እምነታቸውን ተከተሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትም ዛሬም ለዘለዓለምም ያው ነው፤ አይለወጥም።
ዕብራውያን 13:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከወንድሞቻችሁ ጋር በፍቅር ኑሩ። እንግዳ መቀበልንም አትርሱ፤ በዚህ ምክንያት ሳያውቁ መላእክትን በእንግድነት ለመቀበል ያታደሉ አሉና። ከእነርሱ ጋር አብራችኋቸው እንደ ታሰራችሁ ሆናችሁ እስረኞችን ዐስቡ፤ መከራ የጸናባቸውንም በሥጋችሁ ከእነሱ ጋር እንዳላችሁ ሆናችሁ ዐስቡ። መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው፥ ለመኝታቸውም ርኵሰት የለውም፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ገንዘብ ሳትወዱ ኑሩ፤ ያላችሁም ይበቃችኋል፤ እርሱ “አልጥልህም፤ ቸልም አልልህም” ብሎአልና። አሁንም አምነን፥ “እግዚአብሔር ይረዳኛል፥ አልፈራም፥ ሰው ምን ያደርገኛል?” እንበል። የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘለዓለም የሚኖር እርሱ ነውና።
ዕብራውያን 13:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች ተዋደዱ። እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ፣ ሳያውቁ መላእክትን አስተናግደዋልና። በእስር ላይ ያሉትን ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰራችሁ ሆናችሁ አስቧቸው፤ እንዲሁም በሰው እጅ የሚንገላቱትን ራሳችሁ መከራ እንደምትቀበሉ አድርጋችሁ አስቧቸው። ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ይከበር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በአመንዝሮችና በሴሰኞች ሁሉ ላይ ይፈርዳል። ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” ብሏል። ስለዚህ በሙሉ ልብ፣ “ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን። የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መሪዎቻችሁን አስቡ፤ የኑሯቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሏቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንት፣ ዛሬም ለዘላለምም ያው ነው።
ዕብራውያን 13:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርስ በርሳችሁ መዋደዳችሁን ቀጥሉ። እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ አንዳንዶች በዚህ ሳቢያ ሳያውቁ መላእክትን በእንግድነት ተቀብለዋል። እስረኞችን አብራችኋቸው እንደታሰረ ሆናችሁ አስቡ፤ እናንተም በሥጋ እንዳለ እያሰባችሁ የተጨነቁትንም እንደራሳችሁ አስቡ። ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፥ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ሕይወታችሁ ከፍቅረ ንዋይ የጸዳ ይሁን፤ ነገር ግን እርሱ ራሱ “አልለቅህም፤ ከቶም አልተውህም፤” ብሎአልና ያላችሁ ይብቃችሁ። ስለዚህ በመተማመን፥ “ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?” እንላለን። የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን መሪዎቻችሁን አስቡ፤ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና፥ ዛሬም ለዘለዓለምም ያው ነው።