ዕብራውያን 11:4-7
ዕብራውያን 11:4-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አቤል ከቃኤል ይልቅ የሚበልጥ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፤ በዚህም ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ምስክሩም መሥዋዕቱን በመቀበል እግዚአብሔር ነው። በዚህም ከሞተ በኋላ እንኳ ተናገረ። ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም፤ ሳይወሰድም እግዚአብሔርን ደስ እንደ አሰኘው ተመስክሮለታል። ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው አስቀድሞ እግዚአብሔር እንዳለ፥ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጣቸው ሊያምን ይገባዋል። ኖኅም ስለማይታየው ነገር የነገሩትን ባመነ ጊዜ ፈራ፤ ቤተ ሰቡንም ያድን ዘንድ ክፍል ያላት መርከብን ሠራ፤ በዚህም ዓለምን አስፈረደበት፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።
ዕብራውያን 11:4-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አቤል ከቃየል ይልቅ የበለጠ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ። እግዚአብሔር ስለ ስጦታው በተናገረለት ጊዜ፣ እርሱ በእምነት ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ቢሞትም እንኳ እስከ አሁን በእምነቱ ይናገራል። ሔኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ “እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም”፤ ከመወሰዱም በፊት እግዚአብሔርን ደስ እንዳሠኘ ተመስክሮለታልና። ደግሞም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሠኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት። ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈርቶ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት ሠራ፤ በእምነቱ ዓለምን ኰነነ፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።
ዕብራውያን 11:4-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፥ በዚህም፥ እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል። ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና፤ ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ስዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፥ በዚህም ዓለምን ኵኦነነ፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።
ዕብራውያን 11:4-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አቤል ከቃየል መሥዋዕት የበለጠውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀረበው በእምነት ነው፤ እግዚአብሔር የአቤልን መባ በደስታ በተቀበለ ጊዜ አቤል በእምነቱ ጻድቅ መሆኑ ተመሰከረለት፤ አቤል ቢሞትም እንኳ በእምነቱ አማካይነት አሁንም እየተናገረ ነው። ሔኖክ ሞት እንዳይደርስበት ወደ ላይ የተወሰደው በእምነት ነው፤ እግዚአብሔር ስለ ወሰደውም አልተገኘም፤ ከመወሰዱ በፊት ደግሞ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታል። ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው እግዚአብሔር መኖሩንና እርሱን ለሚፈልጉት ሰዎችም ስጦታን የሚሰጥ መሆኑን ማመን አለበት። ገና በዐይን ስለማይታዩት ነገሮች እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ ኖኅ እግዚአብሔርን በመፍራት ቤተሰቡን ለማዳን መርከብን የሠራው በእምነት ነው፤ በኖኅም እምነት ዓለም ኃጢአተኛ መሆኑ ታውቆ ተፈረደበት፤ ኖኅም በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ ወረሰ።
ዕብራውያን 11:4-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፤ በዚህም እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል። ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ከመወሰዱም በፊት እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታል። ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ እግዚአብሔር እንዳለና ለሚፈልጉትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት። ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ስዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፤ በዚህም ዓለምን ኰነነ፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።