ዕብራውያን 11:4-40
ዕብራውያን 11:4-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አቤል ከቃኤል ይልቅ የሚበልጥ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፤ በዚህም ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ምስክሩም መሥዋዕቱን በመቀበል እግዚአብሔር ነው። በዚህም ከሞተ በኋላ እንኳ ተናገረ። ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም፤ ሳይወሰድም እግዚአብሔርን ደስ እንደ አሰኘው ተመስክሮለታል። ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው አስቀድሞ እግዚአብሔር እንዳለ፥ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጣቸው ሊያምን ይገባዋል። ኖኅም ስለማይታየው ነገር የነገሩትን ባመነ ጊዜ ፈራ፤ ቤተ ሰቡንም ያድን ዘንድ ክፍል ያላት መርከብን ሠራ፤ በዚህም ዓለምን አስፈረደበት፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። አብርሃም በተጠራ ጊዜ ርስት አድርጎ ይወርሰው ዘንድ ወዳለው ሀገር ለመሄድ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚደርስም ሳያውቅ ሄደ። በእምነትም ከሀገሩ ወጥቶ ተስፋ በሰጠው ሀገር እንደ ስደተኛ በድንኳን፥ ተስፋውን ከሚወርሱአት ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ኖረ። መሠረት ያላትን ሠሪዋና ፈጣሪዋ እግዚአብሔር የሆነላትን ከተማ ደጅ ይጠኑ ነበርና። ራስዋ ሳራም መካን ሳለች ባረጀችበት ወራት ዘር ታስገኝ ዘንድ በእምነት ኀይልን አገኘች፤ ተስፋ የሰጣት የታመነ እንደ ሆነ አምናለችና። ስለዚህም ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ፥ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ። እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፤ ተስፋቸውንም አላገኙም፤ ነገር ግን ከሩቅ አይተው እጅ ነሱኣት፤ በምድሪቱም ላይ እነርሱ እንግዶችና መጻተኞች እንደ ሆኑ ዐወቁ። እንዲህ የሚሉ ግን ሀገራቸውን እንደሚሹ ያሳያሉ። ከእርስዋ የወጡባትን ሀገር ቢሹ ኖሮስ፥ ወደ እርስዋ ሊመለሱ በተቻላቸው ነበር። አሁን ግን፥ በሰማያት ያለችውን የምትበልጠውን ሀገር ተስፋ ያደርጉ እንደ ነበር ታወቀ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ይጠራ ዘንድ በእነርሱ አያፍርም፤ ተስፋ ያደረጉአትን ሀገር አዘጋጅቶላቸዋልና። አብርሃምም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ ልጁን ይስሐቅን ይሠዋው ዘንድ በእምነት ወሰደው። “በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል” ብሎ ተስፋ ያናገረለትን አንድ ልጁን አቀረበው። እግዚአብሔር ከሙታን ለይቶ ሊያስነሣው እንደሚችል አምኖአልና፤ ስለዚህም ያው የተሰጠው መታሰቢያ ሆነለት። ያገኙት ዘንድ ስለ አላቸው ነገር ይስሐቅ ያዕቆብንና ኤሳውን በእምነት ባረካቸው። ያዕቆብም በሚሞትበት ጊዜ የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን በእምነት ባረካቸው፤ በበትሩ ጫፍም ሰገደ። ዮሴፍም በሚሞትበት ጊዜ፥ ስለ እስራኤል ልጆች ከግብፅ መውጣት በእምነት ዐሰበ፤ ዐጽሙንም ትተው እንዳይወጡ አዘዘ። ሙሴ በተወለደ ጊዜ በእምነት ሦስት ወር በአባቱ ቤት ሸሸጉት፤ ሕፃኑ መልካም እንደ ሆነ አይተውታልና፤ የንጉሥንም ትእዛዝ አልፈሩም። ሙሴም በአደገ ጊዜ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እንቢ አለ፤ ለጊዜው በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ። የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት ከግብፅ ሀብት ሁሉ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንደሚሆን ዐውቆአልና፥ ዋጋውንም ተመልክቶአልና። የንጉሡንም ቍጣ ሳይፈራ፥ የግብፅን ሀገር በእምነት ተወ፤ ከሚያየው ይልቅ የማይታየውን ሊፈራ ወዶአልና። ቸነፈር በኵራቸውን እንዳያጠፋባቸው በእምነት ፋሲካን አደረገ፤ ደሙንም ረጨ። በደረቅ ምድር እንደ መሄድ የኤርትራን ባሕር በእምነት ተሻገሩአት፤ የግብፅ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ሰጠሙ። ሰባት ቀን ከዞሩአት በኋላ የኢያሪኮ ቅጽር በእምነት ወደቀ። ዘማ ረአብም በእምነት ከከሓዲዎች ጋር አልጠፋችም፤ ጕበኞችን በሰላም ተቀብላ ሰውራቸዋለችና። እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎን፥ ስለ ባርቅ፥ ስለ ሶምሶን፥ ስለ ዮፍታሔ፥ ስለ ዳዊት፥ ስለ ሳሙኤልና ስለ ሌሎች ነቢያት እነግራችሁ ዘንድ ጊዜዬ አጭር ነውና። እነርሱ በእምነት ተጋደሉ፤ ነገሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፤ ተስፋቸውን አገኙ፤ የአናብስትንም አፍ ዘጉ ። የእሳት ኀይልን አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው በረቱ፤ በጦርነት ኀይለኞች ሆኑ፤ የባዕድ ጭፍሮችንም አባረሩ። ሴቶችም እንደ ትንሣኤ ቀን ተነሥተውላቸው ሙታኖቻቸውን ተቀበሉ፤ ተፈርዶባቸው የሞቱም አሉ፤ የምትበልጠውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ ሊድኑ አልወደዱምና። የገረፉአቸው፥ የዘበቱባቸውና ያሠሩአቸው ወደ ወህኒ ያገቡአቸውም አሉ። በመጋዝ የሰነጠቁአቸው፥ በድንጋይ የወገሩአቸው፥ በሰይፍም ስለት የገደሉዋቸው አሉ፤ ማቅ፥ ምንጣፍና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፤ ተቸገሩ፤ መከራ ተቀበሉ፤ ተራቡ፥ ተጠሙም። ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናቸው፤ ዱር ለዱርና ተራራ ለተራራ፥ ዋሻ ለዋሻና ፍርኩታ ለፍርኩታም ዞሩ። እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙም። ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ፥ እግዚአብሔር ስለ እኛ የምትበልጠውን አስቀድሞ በይኖአልና።
ዕብራውያን 11:4-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አቤል ከቃየል ይልቅ የበለጠ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ። እግዚአብሔር ስለ ስጦታው በተናገረለት ጊዜ፣ እርሱ በእምነት ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ቢሞትም እንኳ እስከ አሁን በእምነቱ ይናገራል። ሄኖክ ሞትን እንዳያይ ከዚህ ዓለም በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም፤ ከመወሰዱም በፊት እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና። ደግሞም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት። ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈርቶ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት ሠራ፤ በእምነቱ ዓለምን ኰነነ፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። አብርሃም ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ እንዲሄድ በተጠራ ጊዜ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም፣ እሺ ብሎ ሄደ። በባዕድ አገር እንዳለ መጻተኛ በተስፋዪቱ ምድር በእምነት ተቀመጠ፤ የተስፋውን ቃል አብረውት እንደሚወርሱት እንደ ይስሐቅና እንደ ያዕቆብ በድንኳን ኖረ፤ ምክንያቱም መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር። አብርሃም ምንም እንኳ ዕድሜው ቢገፋም፣ ሣራም ራሷ መካን ብትሆንም፣ ተስፋን የሰጠውን ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረ በእምነት የልጅ አባት ለመሆን በቃ። ስለዚህ እንደ ሞተ ሰው ከሚቈጠር ከዚህ ከአንድ ሰው፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛና እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ተቈጥሮ የማያልቅ ዘር ተገኘ። እነዚህ ሁሉ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል ሳያገኙ እምነታቸውን እንደ ጠበቁ ሞቱ፤ ሆኖም ከሩቅ አይተው ሰላም አሉት፤ በዚህ ምድር ሲኖሩ መጻተኞችና እንግዶች መሆናቸውን ተገንዝበው ነበርና። እንደዚህ የሚሉት ሰዎች የራሳቸው የሆነውን አገር እንደሚጠባበቁ ያሳያሉ። ትተውት የወጡትን አገር ቢያስቡ ኖሮ፣ ወደዚያ የመመለስ ዕድል ነበራቸው። አሁን ግን ከዚህ የሚበልጠውን ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ አላፈረም፤ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና። አብርሃም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ፣ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ በእምነት አቀረበ፤ የተስፋን ቃል የተቀበለው እርሱ፣ አንድ ልጁን ሊሠዋ ዝግጁ ነበር፤ ይህም እግዚአብሔር፣ “ዘርህ በይስሐቅ ይጠራል” ያለለት ነበር። አብርሃም እግዚአብሔር ሙታንን ሊያስነሣ እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር፤ ይስሐቅንም ከሞት የመነሣት አምሳያ ሆኖ አገኘው። ይስሐቅ ወደ ፊት የሚሆነውን ዐስቦ ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው። ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ እያንዳንዳቸውን የዮሴፍን ልጆች በእምነት ባረካቸው፤ በበትሩም ጫፍ ዘንበል ብሎ ሰገደ። ዮሴፍ ሊሞት በተቃረበ ጊዜ፣ ስለ እስራኤል ሕዝብ ከግብፅ መውጣት በእምነት ተናገረ፤ ስለ ዐፅሙም ትእዛዝ ሰጠ። ሙሴ ከተወለደ በኋላ፣ ወላጆቹ መልከ መልካም ሕፃን መሆኑን ስላዩ በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት፤ የንጉሡንም ዐዋጅ አልፈሩም። ሙሴ ካደገ በኋላ፣ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እንቢ አለ። ለጥቂት ጊዜ በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ። ከግብፅ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ፤ ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቷልና። የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ ግብፅን ለቅቆ በእምነት ወጣ፤ የማይታየውንም እንዳየው አድርጎ በመቍጠር በዐሳቡ ጸና። በኵሮች የሆኑትን የሚገድለው ቀሣፊ የእስራኤልን በኵር ልጆች እንዳይገድል ፋሲካን በእምነት አደረገ፤ ደምንም ረጨ። ሕዝቡ በደረቅ መሬት እንደሚኬድ ቀይ ባሕርን በእምነት ተሻገሩ፤ ግብፃውያን ግን እንደዚሁ ለማድረግ ሲሞክሩ ሰጠሙ። ሕዝቡ የኢያሪኮን ግንብ ሰባት ቀን ከዞሩት በኋላ፣ በእምነት ወደቀ። ዝሙት ዐዳሪዋ ረዓብ፣ ሰላዮቹን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙት ጋር ያልጠፋችው በእምነት ነው። እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን ልበል? ስለ ጌዴዎን፣ ስለ ባርቅ፣ ስለ ሳምሶን፣ ስለ ዮፍታሔ፣ ስለ ዳዊት፣ ስለ ሳሙኤል፣ እንዲሁም ስለ ነቢያት እንዳልተርክ ጊዜ የለም። እነዚህ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፤ በቅን ፈረዱ፤ የተሰጠውን የተስፋ ቃል ተቀበሉ፤ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፤ የእሳትን ኀይል አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው በረቱ፤ በጦርነት ኀያል ሆኑ፤ ባዕዳን ወታደሮችን አባረሩ። ሴቶች፣ ሙታናቸው ተነሡላቸው። ሌሎቹ ደግሞ የተሻለውን ትንሣኤ ለማግኘት ሲሉ፣ መትረፍን ንቀው ለሞት ለሚዳርግ ሥቃይ ራሳቸውን ሰጡ፤ ከዚህም ነጻ ለመውጣት አልፈለጉም። አንዳንዶቹ መዘባበቻ ሆኑ፤ ተገረፉ። ሌሎቹ ደግሞ ታስረው ወደ ወህኒ ተጣሉ፤ በድንጋይ ተወገሩ፤ በመጋዝ ለሁለት ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተወግተው ሞቱ፤ እየተጐሳቈሉ፣ እየተሰደዱና እየተንገላቱ የበግና የፍየል ቈዳ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም ለእነርሱ አልተገባቻቸውምና። በየበረሓውና በየተራራው፣ በየዋሻውና በየጕድጓዱ ተንከራተቱ። እነዚህ ሁሉ ስለ እምነታቸው የተመሰከረላቸው ቢሆኑም፣ ከእነርሱ ማንም የተስፋውን ቃል የተቀበለ የለም፤ እግዚአብሔር ለእኛ የሚበልጥ ነገር ስላዘጋጀ፣ ያለ እኛ ፍጹማን ሊሆኑ አልቻሉምና።
ዕብራውያን 11:4-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፥ በዚህም፥ እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል። ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና፤ ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ስዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፥ በዚህም ዓለምን ኵኦነነ፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ። ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና። ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቍኦጠረች፥ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። ስለዚህ ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደማይቍኦጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ። እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፥ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ። እንዲህ የሚሉት ለእነርሱ የሚሆነውን አገር እንዲፈልጉ ያመለክታሉና። ያን የወጡበትን አገር አስበው ቢሆኑ፥ ሊመለሱ ጊዜ በሆነላቸው ነበር፤ አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፥ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና። አብርሃም በተፈተነበት ጊዜ ይስሐቅን በእምነት አቀረበ፥ የተስፋን ቃል የተቀበለው፦ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል የተባለለት እርሱም አንድ ልጁን አቀረበ፤ እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያስነሣው እንዲቻለው አስቦአልና፥ ከዚያም ደግሞ በምሳሌ አገኘው። ይስሐቅ ሊመጣ ስላለው ነገር ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው። ያዕቆብ ሲሞት በእምነት የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸው ባረካቸው፥ በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ። ዮሴፍ ወደ ሞት ቀርቦ ሳለ በእምነት ስለ እስራኤል ልጆች መውጣት አስታወሰ፥ ስለ አጥንቱም አዘዛቸው። ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም። ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና። የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና። አጥፊው የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ። በደረቅ ምድር እንደሚያልፉ በኤርትራ ባሕር በእምነት ተሻገሩ፥ የግብፅ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ተዋጡ። የኢያሪኮ ቅጥር ሰባት ቀን ከዞሩበት በኋላ በእምነት ወደቀ። ጋለሞታይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙ ጋር በእምነት አልጠፋችም። እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።
ዕብራውያን 11:4-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አቤል ከቃየል መሥዋዕት የበለጠውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀረበው በእምነት ነው፤ እግዚአብሔር የአቤልን መባ በደስታ በተቀበለ ጊዜ አቤል በእምነቱ ጻድቅ መሆኑ ተመሰከረለት፤ አቤል ቢሞትም እንኳ በእምነቱ አማካይነት አሁንም እየተናገረ ነው። ሔኖክ ሞት እንዳይደርስበት ወደ ላይ የተወሰደው በእምነት ነው፤ እግዚአብሔር ስለ ወሰደውም አልተገኘም፤ ከመወሰዱ በፊት ደግሞ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታል። ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው እግዚአብሔር መኖሩንና እርሱን ለሚፈልጉት ሰዎችም ስጦታን የሚሰጥ መሆኑን ማመን አለበት። ገና በዐይን ስለማይታዩት ነገሮች እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ ኖኅ እግዚአብሔርን በመፍራት ቤተሰቡን ለማዳን መርከብን የሠራው በእምነት ነው፤ በኖኅም እምነት ዓለም ኃጢአተኛ መሆኑ ታውቆ ተፈረደበት፤ ኖኅም በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ ወረሰ። አብርሃም ወጥቶ ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ እንዲሄድ በተጠራ ጊዜ ምንም እንኳ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም ለመሄድ የታዘዘው በእምነት ነው። ከእርሱ ጋር የተስፋው ቃል ወራሾች ከሆኑት ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር በተስፋይቱ አገር መጻተኛ ሆኖ በድንኳን የኖረው በእምነት ነው። ይህንንም ያደረገው ጽኑ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር ያቀዳትንና የሠራትን ከተማ ይጠባበቅ ስለ ነበር ነው። ሣራም ተስፋ የሰጣት እግዚአብሔር ታማኝ መሆኑን ስላወቀች ምንም እንኳ በዕድሜ በመግፋቷ መውለድ የማትችል ብትሆን የመፅነስን ኀይል ያገኘችው በእምነት ነው። ስለዚህ እንደ ሞተ ሰው ከሚቈጠረው ከአንዱ ከአብርሃም እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛና እንደ ባሕር ዳር አሸዋ የማይቈጠር ዘር ተገኘ። እነዚህ ሁሉ በእምነት እንዳሉ ሞቱ፤ እግዚአብሔር ሊሰጣቸው ቃል የገባላቸውንም ነገር አላገኙም፤ ነገር ግን ከሩቅ አይተው ልክ እንዳገኙት አድርገው በደስታ ተቀበሉት። በምድር ላይ እንግዶችና መጻተኞች መሆናቸውንም ተገነዘቡ። እንዲህ የሚናገሩ ሰዎች የራሳቸው የሚሆነውን አገር እንደሚጠባበቁ በግልጽ ያመለክታሉ። ያንን የወጡበትን አገር አስታውሰውት ቢሆኑ ኖሮ ወደዚያ ለመመለስ በቻሉ ነበር። አሁን ግን የሚበልጠውን፥ በሰማይ ያለውን አገር ይናፍቃሉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ከተማን ስላዘጋጀላቸው “አምላካችን” ብለው ቢጠሩት አያሳፍረውም። አብርሃም በተፈተነበት ጊዜ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው በእምነት ነው፤ ያ የተስፋ ቃል የተቀበለው አብርሃም አንድ ልጁን ሊሠዋው ነበር፤ ታዲያ፥ እግዚአብሔር፥ “በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል” ብሎት ነበር። እግዚአብሔር ከሞት የማስነሣት ችሎታ እንዳለው አብርሃም በማመኑ ልክ ከሞት እንደ ተነሣ ያኽል ይስሐቅን እንደገና አገኘው። ይስሐቅ ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር በማሰብ ያዕቆብንና ዔሳውን የባረካቸው በእምነት ነው። ያዕቆብ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን የባረካቸውና በብትሩ ጫፍ ተደግፎ የሰገደው በእምነት ነው። ዮሴፍም የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ እስራኤላውያን ከግብጽ እንደሚወጡ የተናገረው ስለ ዐፅሙም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ትእዛዝ የሰጠው በእምነት ነው። የሙሴ ወላጆች ሙሴ በተወለደ ጊዜ መልከ መልካም መሆኑን ስላዩ የንጉሡን ትእዛዝ ሳይፈሩ ሦስት ወር የሸሸጉት በእምነት ነው። ሙሴም ካደገ በኋላ “የፈርዖን የልጅ ልጅ” ተብሎ መጠራትን ያልፈቀደው በእምነት ነው፤ ስለዚህም እርሱ በኃጢአት ከሚገኘው ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ። ወደፊትም የሚቀበለውን ዋጋ ስለ ተመለከተ ከግብጽ ሀብት ይልቅ ስለ መሲሑ መዋረድ የበለጠ መሆኑን አሰበ። የንጉሡንም ቊጣ ሳይፈራ ከግብጽ የወጣው በእምነት ነው፤ በዐይን የማይታየውንም አምላክ እንዳየው ያኽል ሆኖ በዓላማው ጸና። የበኲር ልጆችን ለመግደል የታዘዘው መልአክ የእስራኤላውያንን የበኲር ልጆች እንዳይገድል በማለት ሙሴ የፋሲካና የደም መርጨትን ሥርዓት ያደረገው በእምነት ነው። እስራኤላውያን በደረቅ ምድር እንደሚሻገሩ ሆነው ቀይ ባሕርን የተሻገሩት በእምነት ነው፤ ግብጻውያን ግን እንዲሁ ለማድረግ በሞከሩ ጊዜ ሁሉም ሰጠሙ። እስራኤላውያን በኢያሪኮ ቅጽሮች ዙሪያ ሰባት ቀን ከዞሩ በኋላ ቅጽሮቹን ያፈረሱት በእምነት ነው። አመንዝራይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙት ጋር ከመሞት የተረፈችው በእምነት ነው። እንግዲህ ሌላ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎን፥ ስለ ባራቅ፥ ስለ ሶምሶን፥ ስለ ዮፍታሔ፥ ስለ ዳዊት፥ ስለ ሳሙኤል፥ ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥረኛል፤ እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፤ በፍትሕ አስተዳደሩ፤ የተሰጣቸውንም ተስፋ አገኙ፤ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፤ የእሳትን ኀይል አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከደካማነት ወደ ብርቱነት ተለወጡ፤ በጦርነት ኀይለኞች ሆኑ፤ የወራሪ ጠላትን ወታደሮች አባረሩ፤ ሴቶች የሞቱባቸውን ዘመዶቻቸውን ከሞት ተነሥተው አገኘአቸው። ሌሎችም የበለጠ ትንሣኤ ለማግኘት አስበው ልዩ ልዩ ሥቃይ ተቀበሉ፤ ከእስራት ነጻ መሆንንም አልፈቀዱም። ሌሎች መዘባበቻ ሆነው ተገረፉ፤ ሌሎች በእግር ብረት ታስረው ወደ ወህኒ ቤት ተጣሉ፤ በድንጋይ ተወገሩ፤ በመጋዝ ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተገደሉ፤ የበግና የፍየል ቆዳ ለብሰው ተንከራተቱ፤ ድኾችና ስደተኞች ሆነው ተንገላቱ፤ በበረሓ፥ በተራራ፥ በምድር ውስጥ ባሉ ዋሻዎችና ፈፋዎች ዞሩ። በዚህም ዐይነት ዓለም ለእነርሱ ተገቢ ስፍራ ሆና አልተገኘችም። እነዚህ ሁሉ ስለ እምነታቸው የተመሰከረላቸው ቢሆኑም የተሰጣቸውን ተስፋ ገና አላገኙም። እግዚአብሔር ለእኛ የተሻለ ነገር ዐቅዶአልና፤ ስለዚህ እነርሱ ከእኛ ጋር እንጂ ብቻቸውን ፍጹሞች መሆን አይችሉም።
ዕብራውያን 11:4-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፤ በዚህም እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል። ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ከመወሰዱም በፊት እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታል። ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ እግዚአብሔር እንዳለና ለሚፈልጉትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት። ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ስዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፤ በዚህም ዓለምን ኰነነ፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። አብርሃም ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ እንዲሄድ በተጠራ ጊዜ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴትም እንደሚሄድም ሳያውቅ ሄደ። ለባዕድ አገር እያለም በተስፋ ቃል በተሰጠው ምድር፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ወራሾች እንደሆኑት እንደ ይስሐቅና እንደ ያዕቆብ በእምነት በድንኳን ኖረ፤ ምክንያቱም መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበር። ሣራም ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደሆነ ስለ ቈጠረች፥ ምንም እንኳን መካን ብትሆን፥ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። ስለዚህ እንደ ሞተ ሰው ከሚቈጠር ከዚህ ከአንድ ሰው፥ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛና እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ተቈጥሮ የማያልቅ ዘር ተገኘ። እነዚህ ሁሉ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል ሳያገኙ እምነታቸውን እንደ ጠበቁ ሞቱ፤ ሆኖም ከርቀት አይተውት ሰላምታ አቀረቡለት፤ በዚህ ምድር ሲኖሩም እንግዶችና መጻተኞች ለመሆንም ታመኑ። እንደዚህ የሚሉት ሰዎች የራሳቸው የሆነውን አገር እንደሚጠባበቁ ያመለክታሉ። ያን ትተውት የወጡትን አገር አስበው ቢሆን ኖሮ፥ ወደዚያ የመመለስ እድል በነበራቸው ነበር። አሁን ግን የሚበልጠውን ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና አምላካቸው ተብሎ ለመጠራት በእነርሱ አያፍርም። አብርሃም በተፈተነ ጊዜ ይስሐቅን በእምነት አቀረበ፤ የተስፋን ቃል የተቀበለው እርሱም አንድ ልጁን ሊሠዋ ዝግጁ ነበር፤ ስለ እርሱም፥ “ዘርህ በይስሐቅ ይጠራል” ተብሎለት ነበር። እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያስነሣው እንደሚችል አስቦአልና፤ ይስሐቅን እንደ ምሳሌ መልሶ ተቀበለ። ይስሐቅ ስለ መጪው ነገር ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው። ያዕቆብ ሲሞት በእምነት የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን ባረካቸው፤ በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ። ዮሴፍ ወደ ሞት በቀረበ ጊዜ፥ በእምነት ስለ እስራኤል ልጆች መውጣት አስታወሰ፤ ስለ አጥንቱም አዘዛቸው። ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት፤ የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም። ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ ተብሎ ላለመጠራት በእምነት እምቢ አለ፤ በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ፥ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ። ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቶአልና፥ ከግብጽ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ። የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና፥ የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብጽን አገር ትቶ የሄደው በእምነት ነበር። የበኩር ልጆችን የሚያጠፋው እንዳይነካቸው ፋሲካን የጠበቀውና ደምን መርጨትን ያደረገው በእምነት ነበር። በደረቅ ምድር እንደሚያልፉ የኤርትራን ባሕር በእምነት ተሻገሩ፤ የግብጽ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ሰመጡ። የኢያሪኮ ግንብ ሰባት ቀን ከዞሩት በኋላ በእምነት ፈረሰ። ጋለሞታይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው በእምነቷ ምክንያት ከማይታዘዙ ጋር አልጠፋችም። ከዚህ በላይ ምን ልበል? ስለ ጌዴዎን፥ ስለ ባርቅ፥ ስለ ሳምሶን፥ ስለ ዮፍታሔ፥ ስለ ዳዊት፥ ስለ ሳሙኤልና ስለ ነቢያት እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛል። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፤ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፤ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፤ የእሳትን ኃይል አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው ብርቱ ሆኑ፤ በጦርነት ኀይለኞች ሆኑ፤ የባዕድ ወራሪዎችን አባረሩ። ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም የሚታደጓቸውን ሳይሹ የሚበልጠውን ትንሣኤ ለማግኘት እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ መሆንን፥ መገረፍን፥ ከዚህም በላይ እስራትንና ወኅኒን ቻሉ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፤ በመጋዝ ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፤ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ፥ እየተጨነቁ፥ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና፥ በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። እነዚህም ሁሉ ስለ እምነታቸው የተመሰከረላቸው ቢሆኑም የተገባውን የተስፋ ቃል አላገኙም። ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ፥ እግዚአብሔር ለእኛ የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበር።